1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፖሊስ «ጦላይ የሚገኙት 1204 ሰዎች ሃሙስ ይለቀቃሉ» 

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6 2011

«ለሃገሪቱም ሆነ ለአዲስ አበባ ከተማ ዘላቂ ሰላም ይሄ ቢደረግ ይሻላል ተብሎ ወደ ጦላይ እንዲሄዱና ለአንድ ወር መረሃ-ግብር ተሰቶአቸዉ ተልከዉ ነበር አሁን አንድ ወሩ አልቆአል። የሎጂስቲክ ችግር አጋጥሞን ካልዘገየ በስተቀር ሃሙስ እንደሚፈቱ ተስፋ እናደርጋለን። ሃሙስ ይወጣሉ ብለን እንገምታለን።»  

https://p.dw.com/p/36eBm
Äthiopien Zeynu Jemal
ምስል DW/T. Getachew

«ታሳሪዎች አይደሉም፤ የሕግ የበላይ ነት እንዲያዉቁ ገለፃ ለማድረግ ነዉ የተያዙት»

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ኢትዮጵያዉያን ትናንት የጀመሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች ይፈቱ ዘንድ የሚጠይቅ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ ዛሬም ቀጥሎ ነዉ የዋለዉ። በዘመቻዉ «በግፍ የተያዙ የአዲስ አበባ ወጣቶች ይፈቱ»፤ «ጫት መቃምና፤ ሃሺሽ ማጤስ፤ በሕግ አልተከለከለም»፤ «ፍትህ በገፍ ለታሰሩት አዲስ አበቤዎች» የሚሉ ጽሑፎችን በብዛት ተራጭቷል።  የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መስከረም 19 ባወጣዉ መግለጫ  በቁጥጥር  ሥር ያዋልናቸዉን  «ለሕንጸት » ወደ ጦላይ ልከናቸዋል ሲል ገልፆ ነበር። ይሁንና ታሳሪዎቹ ወጣቶች እስካሁን ምን እየተደረገላቸዉ እንደሆነ የተገለፀ ነገር የለም።  የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ አበበባ ዉስጥ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን በጅምላ ማሰሩን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል «መንግሥት ሕግ ለማስከበር ሕገ-ወጥ መሆን የለበትም» ሲል የመንግሥትን ርምጃ አዉግዞ ነበር። የመገናኛ ብዙሃን የአዲስ አበባን የፖሊስ ኮሚሽን ጠቅሰው የታሰሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች ሐሙስ እንደሚለቀቁ ዘግበዋል። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ዛሬ «DW» በሰጡት ቃለ ምልልስ የተያዙት ወጣቶች ብቻ አይደሉም፤ ታሳሪዎችም አይደሉም፤ የሎጂስቲክ ችግር እስካላጋጠመን እስከ ፊታችን ሃሙስ ይለቀቃሉ።  
«የታሰሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች የሚለዉ ዘገባ ትክክል አይደለም። ከመስከረም ሁለት እስከ መስከረም ስምንት ድረስ አዲስ አበባ ዉስጥ በተፈጠረዉ ኹከትና ብጥብጥ የተሳተፉ የተለያዩ ዜጎች« ወጣቶች ብቻ አይደሉም» በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ያላቸዉ ፤ ከነዛ ዉስጥ ግድያና የአካል የመሰለ ወንጀል የፈፀሙ ወንጀለኞች አሉ። ሌሎች ደግሞ 1204 የሚሆኑበብጥብጡ ከፍተኛ ሚና የነበራቸዉ ምን ቢደረጉ ይሻላል የሚል ዉይይት ከተደረገ በኋላ ይህን ሁሉ ዜጋ አስሮ ክስ ከመመስረት ለተወሰነ ጊዜ የሕግ የበላይነትን እንዲያዉቁ ፤ በፈፀሙት ወንጀል በተመለከተ ራሳቸዉን እንዲገልፁ ጊዜ ተሰጥቶአቸዉ ወደ ኅብረተሰቡ ቢገቡ ይሻላል በሚል ወስነን ወደ ጦላይ ተልከዋል። በምክክራችን ለሃገሪቱም ሆነ ለአዲስ አበባ ከተማ ዘላቂ ሰላም ይሄ ቢደረግ ይሻላል ተብሎ ወደ ጦላይ እንዲሄዱና ለአንድ ወር መረሃ-ግብር ተሰቶአቸዉ ተልከዉ ነበር አሁን አንድ ወሩ አልቆአል። የሎጂስቲክ ችግር አጋጥሞን ካልዘገየ በስተቀር ሃሙስ እንደሚፈቱ ተስፋ እናደርጋለን ሃሙስ ይወጣሉ ብለን እንገምታለን።»  


አዜብ ታደሰ 
ሸዋዬ ለገሠ