1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ ከዲፕሎማቶች ጋር ያደረገው ውይይት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 14 2014

የፖለቲካ ድርጅቶቹ ተወካዮች ኢትዮጵያውያን ሊስማሙባቸው ባልቻሉባቸው ጉዳይ ላይ ገለልተኛ የዓለማቀፍ ማህበረሰብ ጣልቃ ገብቶ የማደራደር ሚና እንዲጫወት መጋበዝ የአገር ሉዓላዊነትን የሚጥስ አይደለም ብለዋልም፡፡

https://p.dw.com/p/4ETCY
Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
ምስል Seyoum Getu/DW

ፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ ከዲፕሎማቶች ጋር ያደረገው ውይይት

ዓለማቀፍ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይላት መካከል ገብቶ የማሸማገል ሚናውቸውን እንዲወጣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካዉከስ ጠየቀ፡፡ በቅርቡ በኮከስ የተሰባሰቡት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ዓረና ትግራይ፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ እና የኦጋደን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ትናንት ከተለያዩ ኤምባሲዎች ከተውጣጡ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት ለብሔራዊ ውይይት አማራጭ ያሉት ሃሳብ ላይ መክረዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት ተሳታፊ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ተወካዮች ኢትዮጵያውያን ሊስማሙባቸው ባልቻሉባቸው ጉዳዮች ላይ ገለልተኛ የዓለማቀፍ ማህበረሰብ ጣልቃ ገብቶ የማደራደርሚና እንዲጫወት መጋበዝ የአገር ሉዓላዊነትን የሚጥስ አይደለም ብለዋልም፡፡
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ አዲስ አበባ በብሪቲሽ ካውንስል በተዘጋጀው መድረክ በቅርቡ በኮከስ የተደራጁት የፖለቲካ ድርጅቶች ከብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ አውስትራሊያ እና ሌሎችም
አገራት ከተወከሉ ድፖሎማቶች ጋር ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና የፖለቲካ አውዱ የይሆናል ሁኔታ መክረዋል ነው የተባለው፡፡  የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በውይይት መድረኩ ከተሳተፉት አንዱ ናቸው፡፡ ስለኢትዮጵያ አሁናዊ የሰላም ሁኔታ እና የብሔራዊ ውይይት ሂደቱ ዋነኛ የውይይቱ ትኩረት እንደነበርም ነግረውናል፡፡ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ከሚስተዋለው የፀጥታ ሁኔታ አንጻር ሊከሰቱ ስለሚችሉ ተገማች ሁኔታ እና መፍትሄዎቻቸው የሃሳብ ልውውጥ ተደርጓል ነው ያሉን፡፡ የውይይት መድረኩ በማን እንደተዘጋጀ የተጠየቁት የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ለመያዝ ያዘጋጁት ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የጅማሮ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የብሔራዊ ንግግር ሂደት ስጋት እና ተግዳሮቱ ያሏቸው ነጥቦች ላይ በጥልቀት ስለመወያየታቸው እና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የተለያዩ ድጋፎችን በተሳትፎ ጭምር እንዲያረጋግጥ ጥያቄ መቅረቡም ነው የተነገረው፡፡ ስለ ውይይቱ እና ሊደረጉ ስለታሰቡት ድጋፎች ተሳትፈዋል ከተባሉት ኤምባሲዎች ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡ አቶ ሙሳ አደምም በዚሁ ላይ ባከሉት አስተያየታቸው፤ “ኢትዮጵያ የዓለም አንድ አካል እንደመሆና ከተለያዩ አገራትና ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ በጎ ልምዶችን ከአገር ጥቅም ጋር በማይጋጭ አኳኃን ብትቀበል የችግሮቿ መፍቿ አንዱ እርምጃ ሊሆን ይችላል” ይላሉ፡፡

ሥዩም ጌቱ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር

ነጋሽ መሐመድ