1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች የታሰሩበትን ኢትዮጵያ እንድታሳውቅ አምነስቲ ጠየቀ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 11 2012

“ዛሬ ጠዋት እርጉዝ ነኝ ብዬ ለምኜ ፖሊስ በርቀት እንዳየው ፈቅዶልኛል። በኮሮና ሥጋት ምክንያት ምግብ እንድሰጠው ፖሊስ አልፈቀደልኝም። ዛሬም ፖሊስ ፍርድ ቤት ካቀረበው ብዬ እየጠበኩ ነው” የአቶ ደጀኔ ጣፋ ባለቤት ባለፈው ሐምሌ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ከተናገሩት

https://p.dw.com/p/3fWzE
Deutschland Äthiopiens Oromo federalist congress |  Dejene Taffa
አቶ ደጀኔ ጣፋምስል Eshete Bekele Tekele/DW

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ከድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ የታሰሩ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች  ያሉበትን እንዲያሳውቁ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

“በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ ፖሊስ በትንሹ 5,000 ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውሏል” ያለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አብዛኞቹ ከሰዎች መገናኘት እንደማይችሉ እና ያሉበትም እንደማይታወቅ ገልጿል።

ከሐጫሉ ግድያ በኋላ ከታሰሩት መካከል የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፤ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች እና ጋዜጠኞች ይገኙበታል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮሴ ሙቼና “የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የታሰሩበትን ይፋ ባለማድረጋቸው ለቤተሰቦቻቸው ጭንቀት እየፈጠሩ ነው። በአፋጣኝ እያንዳንዳቸው የታሰሩበትን መግለጽ፣ በሚታወቅ ወንጀል መክሰስ አሊያም በአፋጣኝ መልቀቅ አለባቸው” ብለዋል።

አምነስቲ እንደሚለው የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ንጽሕናቸው ባልተጠበቀ እና በተጨናነቀ ሁኔታ በመታሰራቸው ቤተሰቦቻቸው ተጨንቀዋል።

ከሐጫሉ ግድያ በኋላ ባሉ የተለያዩ ቀናት የታሰሩ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች ሚካኤል ቦረን፣ ሽጉጥ ገለታ፣ ለሚ ቤኛ ፣ ኬኔሳ አያና እና ኮሎኔል ገመቹ አያና ያሉበትን ጠበቆቻቸው ማወቅ እንዳልቻሉ ዛሬ ይፋ የሆነው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ ይጠቁማል። በሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ መግለጫ መሠረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ባለሥልጣናት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች በጣቢያዎቻቸው እንደማይገኙ ለጠበቆቻቸው ተናግረዋል።

ዴፕሮሴ ሙቼና “ቅድመ-እስር የሚፈቀደው ፖሊስ በታሰሩት ላይ ለሚያቀርበው ክስ ጠንካራ ማስረጃ ሲኖረው ነው። ፖሊስ ያሰረበትን ለማስረዳት ማስረጃ ሲፈልግ ማንም የነፃነት መብቱ ሊከለከል አይገባም” ብለዋል።

Kombobild Eskinder Nega und Jawar Mohammed
አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ጃዋር መሐመድ

አምነስቲ በመግለጫው አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ መጀመሪያ ከታሰሩበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ ሜክሲኮ አካባቢ ከፌድራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት አጠገብ ወደሚገኝ እስር ቤት መዘዋወራቸውን ገልጿል። ሌሎች የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አባላት ከታሰሩበት በአዲስ አበባ ወደሚገኝ ትምህርት ቤት መዘዋወራቸውንም ገልጿል። 

ከኦፌኮ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን፤ ክስም እንዳልተመሰረተባቸው መግለጫው ይጠቁማል። አምነስቲ እንዳለው ነፍሰ ጡር ባለቤታቸው አቶ ደጀኔን ለማየት ከፍርድ ቤት ደጃፍ ለቀናት ይጠባበቁ ነበር።

“ዛሬ ጠዋት እርጉዝ ነኝ ብዬ ለምኜ ፖሊስ በርቀት እንዳየው ፈቅዶልኛል። በኮሮና ሥጋት ምክንያት ምግብ እንደሰጠው ፖሊስ አልፈቀደልኝም። ዛሬም ፖሊስ ፍርድ ቤት ካቀረበው ብዬ እየጠበኩ ነው” ሲሉ የአቶ ደጀኔ ባለቤት ባለፈው ሐምሌ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ለአምነስቲ ተናግረዋል።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር እስክንድር ነጋ እና ምክትላቸው ስንታየሁ ቸኮል “የአዲስ አበባ ወጣቶችን ለኹከት አደራጅተዋል” በሚል ጥርጣሬ የታሰሩት ሐጫሉ ሁንዴሳ በተገደለ በማግሥቱ ነበር።

አቶ እስክንድር በእስር ቤት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤት ተናግረዋል። ፍርድ ቤት ጉዳዩ እንዲመረመር ትዕዛዝ ቢሰጥም ፖሊስ የተባለውን እንዳልፈጸመ የአቶ እስክንድር ጠበቃ ለአምነስቲ ተናግረዋል።

ድምፃዊው ከተገደለ ከሶስት ቀናት በኋላ ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) አርታዒ መለሰ ድሪብሳ ጨምሮ ሁለት ጋዜጠኞች እና የቴክኒክ ባለሙያ መታሰራቸውን የገለጸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ከማንም እንዲገናኙ አልተፈቀደላቸውም ብሏል። ድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን ለመጨረሻ ጊዜ ቃለ መጠይቅ ያደረገለት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኛ ጉዮ ዋርዮ እና የቴሌቭዥን ጣቢያው የካሜራ ባለሙያም ከታሰሩ መካከል ይገኙበታል።

“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ወደተለመደ የጭቆና መንገድ የመመለስን ግፊት መቋቋም አለባቸው” ያሉት ዴፕሮሴ ሙቼና  የዜጎችን የመቃወም መብት ሊያከብሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

“የፍርድ ሒደትን ማክበር፤ የታሰሩ ከቤተሰቦቻቸው እና ከጠበቆቻቸው እንዲገናኙ መፍቀድ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ እና መስፈርት የጠበቀ ፍትኃዊ ዳኝነት ማረጋገጥ አለባቸው” ሲሉም አክለዋል።

የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ ማኅበረሰባዊ ኹከት በመሸጋገሩ እንዲሁም የጸጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት እርምጃ በትንሹ 177 ሰዎች መገደላቸውን እና በመቶዎች መቁሰላቸውን አምነስቲ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውሷል።

እሸቴ በቀለ