1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፖለቲከኞቹ ውጥረቱን ያረግቡ ይኾን?

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 8 2012

የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦችን ወደ መለያየት እና መቃቃር ያደርሳል ተብሎ የሚፈራዉን የፖለቲካ ትኩሳት ለማርገብ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ለሁለቱ ሕዝቦች ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታውቁ።

https://p.dw.com/p/3V2QD
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

ፖለቲከኞቹ ውጥረቱን ያረግቡ ይኾን?

የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦችን ወደ መለያየት እና መቃቃር ያደርሳል ተብሎ የሚፈራዉን የፖለቲካ ትኩሳት ለማርገብ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ለሁለቱ ሕዝቦች ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታውቁ። በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የፕረስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸዉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር የሚታዩትን ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭትና ጠቦችን ለመቅረፍ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለበርካቶች የሕይወት ሕልፈት ፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት፣  ከመኖሪያ አካባቢ እና ከትምህርት ገበታ መፈናቀልን ስላስከተለዉ ግጭት ተወያዮቹ ብዙ ማለታቸው ተገልጿል።

Deutschland Äthiopiens Oromo federalist congress |  Merera Gudina
ምስል Eshete Bekele Tekele/DW

በመንግስት አስተባባሪነት ላለፉትን ኹለት ቀናት አዲስ አበባ ዉስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው ውይይት፣ ብሔርተኝነታቸው አይሎ ይታያል የሚባልላቸውን እና በኦሮሞ እና አማራ ብሔሮች ስም የተደራጁትን የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመብት አቀንቃኞች ነን የሚሉትን ጨምሮ ማሳተፉም ተሰምቷል።

የሁለቱ ሕዝቦች የፖለቲካ ኃይሎች ፊት ለፊት ተገናኝተው በወቅታዊ የሰላም ችግር ላይ መነጋገራቸው፣ ችግሮቹን ከመሰረቱ መቅረፍ ባያስችል እንኳ እንዳይስፋፋ ለማድረግ እንደሚያግዝ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረንስ ኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ውስጥ እየታዩ ካሉ አሳሳቢ ችግሮች ዋነኛው እና በከፍተና የትምህርት ተቋማት አካባቢ እየታየ ያለውን ደም አፋሳሽ ግጭት ለማስቆም ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ከየደጋፊዎቻቸው ጋር እንዲሰሩ ውይይቱ መንገድ መክፈቱን የገለጹት ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሣለኝ ጫኔ ናቸው።

National Movement of Amhara visit to Paris
ምስል Haimanot Tiruneh

ውይይቱን ከውጭ ሆነው የታዘቡት የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ደግሞ የኹለቱ ብሔሮች ፖለቲከኞች እና ሊህቃን በአንድ መድረክ መወያየታቸው ችግሩን ከመሰረቱ ይፈታዋል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ችግሩ ያለው የመንግስት አካልጋ በመኾኑ ለመፍትኼውም ቁርጠኛ አቋም መያዝ ያለበት መንግሥት ነው።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በተለይም ብሔርን መሰረት አድርገው የሚፈጠሩ ግጭቶች ከተቋማቱ ውጪ በሚፈጠሩ የፖለቲካ አመለካከቶች ተጽዕኖ ውጤት በመኾኑ የፖለቲከኞች እና የመብት አቀንቃኞች በሀሣብ በማመን ወደ ውይይት መምጣት ለችግሩ እልባት ለማበጀት መነሻ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ናቸው።

Äthiopien Diskussion Medien und Demokratie in Addis Abeba | Nigussu Tilahun
ምስል DW/Y. Gebregziabher

የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመብት ተሟጋቾች በሀገሪቱ ውስጥ በሚካሄድ እና በሁለት ወገን በሚለጠጥ የፖለቲካ ሂደት፤« በለውጥም በነውጥም» ስማቸው አብሮ እንደሚነሳ ሲነገር ይሰማል። ሀገሪቱ ልታካሄድ ያሰበችውን ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የእነዚሁ ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም የፖለቲካ ተንታኞች ሲያሳስቡ ይሰማል። 

መንግስት በበኩሉ ፖለቲከኞች እና የመብት አቀንቃኞች ለሃሳብ ቅድሚያ መስጠት ለሁለገብ ችግር መፍትሄ መሰረት እንደመጣል እንደሚቆጠር እንደሚያምን አቶ ንጉሡ ጥላሁን ያስረዳሉ።
ትናንት የተጠናቀቀው የኦሮሞ እና አማራ ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ውይይት ተሳታፊዎች ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አዉጥተዋል።ሌላ ጊዜ ለመገናኘት መስማማታቸዉም ተነግሯል።ፖለቲከኞቹ እንዳሉት ቁርጠኛ አቋም ይዘው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆኑ ተሰባጥሮ የሚኖረው ህዝብ ሰላሙ በቶሎ ተመልሶ ይረጋጋ ይሆን? 

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ