1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓሪስ፥ የሉሲ ቅጂ ለዩኔስኮ ተሰጠ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 19 2013

ፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በሚገኘው የዩኔስኮ መቀመጫ በተካኼደ ልዩ ሥነ ሥርዓት የቅሪተ አካሏ ቅጂ ርክክብ ተፈጽሟል።በፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ሆሊ ሲ እና ሞናኮ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ኄኖክ ተፈራ ሻውል የሉሲን ቅሪተ አካል ቅጂ ለዩኔስኮ ዋና ኃላፊ ኦውድሬ አዞላይ አስረክበዋል

https://p.dw.com/p/3vav1
Paris Übergabezeremonie von Denkenesh -Lucys Replik bei der UNESCO
ምስል Haimanot Tiruneh/DW

ጥንታዊቷ ቅሪተ አካል ድንቅነሽ ወይም ሉሲ ቅጂ ለተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት በምህጻሩ(UNESCO)ተሰጠ። ትናንት ፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በሚገኘው የዩኔስኮ ዋና መቀመጫ መሥሪያ ቤት በተካኼደ ልዩ ሥነ ሥርዓት የቅሪተ አካሏ ቅጂ ርክክብ ተፈጽሟል። በፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ሆሊ ሲ እና ሞናኮ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እንዲሁም የዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ኄኖክ ተፈራ ሻውል የድንቅነሽን ቅሪተ አካል ቅጂ ለዩኔስኮ ዋና ኃላፊ ኦውድሬ አዞላይ አስረክበዋል። አምባሰደር ኄኖክ ስለርክክቡ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ «የእኛ የሰው ልጆች የጋራ ተምሳሌት የኾነችው ሉሲ ወይንም ድንቅነሽ ቅሪተ አካል ቅጂን በማስረከቤ እጅግ ደስታ ይሰማኛል» ብለዋል። 

ዩኔስኮን ከመሰረቱ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በሚዳሰሱም ሆነ በማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ያስመዘገበችው በርካታ ቅርሶች ቢኖራትም፤ በድርጅቱ ጽ/ቤት ውስጥ ግን የሚዳሰስ አንዳችም ወካይ ቅርስ አልነበራትም። ድንቅነሽን ልዩ ሴት ሲሉ የገለጿት የዩኔስኮ ዋና ኃላፊ ኦውድሬ አዞላይ ድርጅታቸው ይህን ቅርስ ለመያዝ በመቻሉ መደሰታቸውን እና ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስትም ምስጋና ማቅረባቸውን በሥነስርዓቱ ላይ የተገኘችው የፓሪሷ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ የላከችልን ዜና ይጠቁማል። በዛሬው የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1974 በአፋር ክልል ሐዳር በተሰኘ አካባቢ የድንቅነሽን (ሉሲ) ቅሪተ አካል በቊፋሮ ካገኙት የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች መካከል አንዱ  ፈረንሳዊው ኢቪ ኮፓን ጨምሮ የመስኩ ተመራማሪዎች ሉሲ በሳይንሱ ዓለም ስላላት ጉልኅ ሚና ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

ሃይማኖት ጥሩነህ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ