1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፎን ደር ላየን አፍሪካ እና አውሮፓ እንዲተባበሩ ጥሪ አቀረቡ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 27 2012

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን ስደትን ለመሰሉ የአፍሪካ እና የአውሮፓ የጋራ ጉዳዮች መፍትሔ ለመፈለግ የሁለቱ አኅጉሮች መሪዎች በጋራ መስራት እንዳባቸው አሳሰቡ። ፎን ደር ላየን ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የአፍሪካ ጉብኝት የአውሮፓ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ 170 ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ ሊሰጥ ስምምነት ተፈርሟል።

https://p.dw.com/p/3UOJM
Ursula von der Leyen, EU-Kommissionspräsidentin (li.) und die Staatspräsidentin von Äthiopien Sahle Worke Zewde beim Empfang im Präsidentenpalast in Addis Abeba
ምስል DW/B. Riegert

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሙሳ ፋኪ ማኅማት ተገናኝተዋል

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን ከአፍሪካ ጥብቅ ትብብር መፍጠር የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ዋና ግብ እንደሆነ አስታወቁ። ጸጥታ እና ስደትን የመሳሰሉ ጉዳዮች በአፍሪካ እና በአውሮፓ መሪዎች የጋራ መፍትሔ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ርዕሰ-ብሔር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፤ ከጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት ተገናኝተው ተወያይተዋል። ከአፍሪካ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀዳሚ ግብ መሆኑንም ፎን ደር ላይን ከሙሳ ፋኪ ማኅማት ጋር በመሆኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

«ከአውሮፓ ውጪ በመጀመሪያ ጉብኝቴ አፍሪካን መርጬ መጥቻለሁ። በአፍሪካ ኅብረት መገኘቴ ጠንካራ ፖለቲካዊ መልዕክት ያስተላልፋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ» ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት የተወያዩት ጀርመናዊቷ ፖለቲከኛ «የአፍሪካ አኅጉር እና የአፍሪካ ኅብረት ለአውሮፓ ኅብረት እና ለአውሮፓ ኮሚሽን ትልቅ ፋይዳ አላቸው። በውይይታችን በአውሮፓ እና በአፍሪካ መካከል ባለው ግንኙነት መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ተመልክተናል» ሲሉ ተደምጠዋል።

ኡርሱላ «እውነቱን ለመናገር ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔው የለኝም። ነገር ግን በአንድነት መልሶች ማግኘት እንችላለን የሚል ዕምነት አለኝ።  በጋራ ለአፍሪካም ሆነ ለአውሮፓ ችግሮች መፍትሔ ማበጀት እንችላለን» ሲሉ የሁለቱ አኅጉሮች ፖለቲከኞች በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

Äthiopien Ursula von der Leyen  Addis Ababa
ምስል Reuters/T. Negeri

ፎን ደር ላይን በሥልጣን በሚቆዩባቸው አመታት ከሥልታዊ ትብብር በተጨማሪ ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ለሚደረገው ስደት መፍትሔ መፈለግ ዋንኛ ትኩረታቸው እንደሚሆን ይጠበቃል። በአፍሪካ አገሮች መዋዕለ-ንዋይን በማበረታታት የአኅጉሪቱን ዜጎች ዕድል ማሻሻል እና የድንበር ቁጥጥሩን ማጥበቅ የአውሮፓ ኮሚሽን ስደትን ለመቀነስ ከመረጣቸው ቀዳሚ ሥልቶች መካከል ናቸው።

በዛሬው ዕለት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን ባሉበት ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኮሚሽን የ170 ሚሊዮን ዩሮ የእርዳታ ስምምነት ተፈራርመዋል። ገንዘቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለማጠናከር እንዲሁም የጤና፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የመዋዕለ-ንዋይ ዘርፎችን ለመደገፍ ይውላል ተብሏል።

ስምምነቱ የተፈረመው የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ላይን በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን በጀመሩበት ወቅት ነው። ፎን ደር ላይን የኮሚሽኑን ፕሬዝዳንትነት ከተረከቡ በኋላ ከአውሮፓ ውጪ ያደረጉት የመጀመሪያ ጉዞ ነው።

ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ

እሸቴ በቀለ