1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍትህ ለጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች

ማክሰኞ፣ ኅዳር 20 2015

በየዓመቱ በኅዳር ወር አጋማሽ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ስለማስቆም ይወሳል። የተመድ ከቀናት በፊት ይፋ እንዳደረገው ባለፉት 12 ወራት ከ10 ሴቶች መካከል ከአንድ በላይ ሴቶች ለጾታዊ ወይም ለአካላዊ ጥቃት ያውም የቅርብ በሚሉት ሰው ደርሶባቸዋል።

https://p.dw.com/p/4KFoY
Äthiopien I Konflikt in Tigray
ምስል Nariman El-Mofty/AP/picture allianc

የጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች ጉዳይ

ላለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለጾታዊ ጥቃት የተጋለጡ ወገኖች ጉዳይ ከሞላ ጎደል ይፋ ወጥቷል። በጦርነቱ የተሳተፉ ኃይሎች በአማራ እና በአፋር ክልሎች እንዲሁም በትግራይ ክልል፤ ጾታዊ ጥቃትን እንደጦር መሣሪያ ተጠቅመዋል የሚለውን መረጃ የሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት በአደባባይ ተናግረዋል። ጦርነት ውጊያው በሰላም ስምምነት የሰከነ በሚመስልበት በዚህ ወቅት ለጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች ፍትህ እየተጠየቀ ነው። አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ውስጥ በሚገኝ አካባቢ የምትኖረው እና ባለፈው መስከረም ወር የጥቃት ሰለባ ከሆኑት አንዷ እህት በወቅቱ የደረሰባትን ለዶቼ ቬለ እንዲህ ነው የገለጸችው።

«መስከረም አንድ ቀን ነው ጥቃት የደረሰብኝ፤ አንደኛው ጠባቂ ሲሆን አንደኛው ተግባሩን ፈጻሚ ነው» ትላለች። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ ካለው ጭና ቀበሌ ከሚኖሩ እና የጥቃት ሰለባ ከሆኑት አዳጊ ሴቶች የአንዷ እናት በበኩላቸው የተፈጸመውን በማስታወስ ስለልጃቸውና የድርጊቱ ሰለባዎች ሁኔታ ሲናገሩ፤ «የሚሊሺያ ልጆች ናችሁ በሚል ከእጃችን ወስደው ነው ለጥቃት የዳረጓቸው» በማለት ነው የገለጹት። ምንም እንኳን አሁን ልጆቹ ወደትምህርት ቤት ቢመለሱም የስነልቡና ችግር ላይ መሆናቸውንም አመላክተዋል።  

ጦርነቱ ሁለት ዓመት ያስቆጠረ እንደመሆኑ ቀደም ሲል የውጊያ ቀጣና በነበሩ አካባቢዎች ለጾታዊ ጥቃት የተጋለጡት ቁጥራቸው በርካታ መሆኑን ሲገጽ ቆይቷል። አማራ ክልል ሰሜን ወሎ አካባቢ ተገድደው ከተደፈሩ ወገኖች የስነልቡናም ሆነ የአካላዊ ጤና ድጋፍ እና ክትትል እያገኙ ቢሆንም አንዳንዶች ግን የደረሰባቸው የአካል እና መንፈስ ስብራት ሳያንስ ለሌላ ማኅበራዊ ችግር ተጋልጠዋል ይላሉ በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የሴቶች እና ሕጻናት ጥቃትን የሚከታተለው ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት ሲሰተር መዲና ወርቅነህ ።የተባባሰው የሴቶች ጥቃት

«አሁን እየወለዱ ልጅ እየያዙ እየመጡ ነው» ያሉት ሲስተር መዲና ተገድደው መደፈራቸው እንዳለ ሆኖ ኅብረተሰቡ ሊቀበላቸው እንዳልቻለም ነው የገለጹት። 

በሰሜን ወሎ አካባቢዎች የሚገኙትን ሰለባዎች በቅርበት በሙያቸው ከሚረዱና ሁኔታቸውን የሚከታተሉት ሲስተር መዲና የተፈጸመው ጥቃት ተመዝግቦ መያዙን እርግጠኛ ቢሆኑም ከፍትህ አኳያ ምን እየተደረገ ነው ለሚለው ከእነሱ ውጪ መሆኑን ነው የገለጹልን።

Symbolbild Tigray-Konflikt | Massaker
የጦርነት ትርፍ የሆነው ጥይት እና ጉዳት ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

እንዲህ ያለው ጾታዊ ጥቃት አፋር ክልል ውስጥም ተፈጽሟል። ሆኖም በዚህ ረገድ እስካሁን የተደረገላቸው እርዳታ እንደሌለ ነው ለአፋር ማኅበረሰብ ሰብአዊ መብት የሚሟገተው ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ገአስ አህመድ የሚናገሩት። እሳቸው እንደሚሉት ምንም እንኳን ብዙዎች የጥቃት ሰለባ ቢሆኑም በይፋ አልወጡም፤ በዚህ ረገድም እርዳታም እያገኙ አይደለም። 

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ሊቆሙ የሚችሉት ተጠያቂነት ሲሰፍን መሆኑን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ኃይለ ማርያም አጽንኦት ይሰጣሉ።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረቡ ጉዳይ ተጠናክሮ መሠራት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። ሰለባዎቹ እንደሚናገሩት አንዳንዱ ጥቃት በቡድን የተፈጸመ ነው፤ ጦርነት እንደመሆኑም ጥቃት አድራሾች በሕይወት ላይገኙም ይችላሉ ቢኖሩም በድንጋጤም ይሁን ሌላ ምክንያት የድርጊቱ ፈጻሚዎችን ለይቶ ማውጣቱ ሊከብድ ይችላል። እንዲህ ባለው አጋጣሚ ፍትህ እንዴት ይሆን የሚገኘው? «በተለይ በጦርነት ጊዜ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ወታደሮች ከቦታ ቦታ ስለሚንቀሳቀሱ አጣርቶ በትክክል እነማን ነበሩ እዚያ ቦታ ላይ ተሳታፊዎች የሚለውን ለይቶ አጥፊዎቹን ለፍርድ የማምጣቱ ነገር በፍትህ ሂደት ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ነው።» ያሉት የመብት ተሟጋቹ ያሬድ ኃይለማርያም በወቅቱ በአካባቢው የነበረውን ጦር የሚመራው አካልን መለየት እንደሚቀልም አመላክተዋል። 

Logo von Amnesty International
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አርማ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለጾታዊ ጥቃት ለተጋለጡት ፍትህ ጠይቋል። ድርጅቱ አክሎም ጦርነቱ እንዲቆም የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ያስቻለው የአፍሪቃ ሕብረት የተፈጸሙት ጾታዊ ጥቃቶች ምርመራ እንዲካሄድባቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርግም ተማጽኗል።  አምነስቲ ከመግለጫው በተጨማሪም ለድምጽ አልባዎቹ ሰለባዎች ድምጽ ለመሆን ጉዳቱን የሚያስታውስ አውደርዕይ በተለያዩ ሃገራት በሚገኝ ጽህፈት ቤቱም ከፍቷል። የአፋር ሰብዓዊ መብት ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ገአስ አህመድ ምንም እንኳን ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ያነሳው የፍትህ ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም ሚዛናዊነት ግን ይጎድለዋል ይላሉ።አምነስቲ፤ በኢትዮጵያ ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸዉ ፍትህ 

በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን አቆጣጠር ከ1981 ዓም ጀምሮ ነው በየዓመቱ ኅዳር 25 ቀን በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች እንዲያቆሙ ዓለም አቀፍ የግንዛቤ መፍጠሪያ ዕለት ሆኖ የሚታሰበው። ለ16 ቀናትም ድርጊቱን ይፋ አውጥቶ በማውገዝ የማስቆም ቅስቀሳም ይካሄዳል። ከተጠቀሰው ጊዜ አንስቶም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ትርጉም ያለው ስኬት በተለያዩ አካባቢዎች መመዝገቡ እውነት ቢሆንም፤ የመሻሻሉ ሂደት አንድ ወደፊት እየተራመደ ሁለት ወደ ኋላ መመለሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያነጋገረ ነው። በተለይ ደግሞ ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ሕይወት ለማትረፍ ከሚደረገው ትግል ጎን ለጎን እንዲህ ላለው ጥቃት የሚጋለጡ አዋቂ እና ሕጻናት ሴቶች ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱም ሌላው የብዙሃንን ትኩረት የሳበ ሆኗል።

 ሸዋዬ ለገሠ 

እሸቴ በቀለ