1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አምነስቲ፤ በኢትዮጵያ ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸዉ ፍትህ

ዓርብ፣ ኅዳር 16 2015

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትላንት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሁለት አመታት በዘለቀው ጦርነት ሴቶችን አስገድደዉ የደፈሩና የበደሉ በሙሉ በሕግ መጠየቅ አለባቸዉ ጥሪ አቅርቧል።ተፋላሚዎችን የሚሸመግሉ ወገኖች ጦርነቱን ለማስቆም ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ተገቢውን ፍትህ ያገኙ ዘንድ እንዲጥሩም አሳስቧል።

https://p.dw.com/p/4K5IS
Äthiopien I Konflikt in Tigray
ምስል Nariman El-Mofty/AP/picture allianc

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትላንት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሁለት አመታት በዘለቀው ጦርነት ሴቶችን አስገድደዉ የደፈሩና የበደሉ በሙሉ  በሕግ መጠየቅ አለባቸዉ ጥሪ አቅርቧል።ተፋላሚዎችን  የሚሸመግሉ ወገኖች ጦርነቱን ለማስቆም ከሚያደርጉት  ጥረት ጎን ለጎን ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ተገቢውን ፍትህ ያገኙ ዘንድ እንዲጥሩም አሳስቧል። አምነስቲ አክሎም የአፍሪቃ ኅብረት የሰብአዊ መብቶችን ይዞታ በተመለከተ ሰለባዎች ተገቢዉን ፍትህ ማግኘት እንዲችሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአካባቢውም ሆነ ለዓለም አቀፍ ምርመራዎች ሙሉ ትብብር እንዲያደርግ ግፊት እንዲያደርግም ጠይቋል።

በጦርነቱ ወቅት በተለይ በትግራይ፣ በአማራና  በአፈር ክልሎች በበርካታ ሴቶች ላይ  ጾታዊ  ጥቃቶች እንደደረሱ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተለያየ ግዜ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። የተፋላሚ ኃይላት ባለስልጣናትም አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለመወንጀል ቢያዉሉትም ጥቃቱ መድረሱን  በየጊዜዉ አስታዉቀዋል።

ጥቃት የተፈፀመባቸውን የሴቶች ብዛትና የግፉን ዓይነት በግልጽ የሚያመለክት ጥናትና መረጃ ግን እስካሁን የለም።

በኢትዮጵያ ለጾታዊ ጥቃት ለተጋለጡ ሴቶች ከለላ፣ምክርና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጠዉ የሴቶች ማረፊያ እና ልማት ማህበር መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር እንደሚሉት ግን እስካሁን ካገኙት መረጃ መሰረት የተፈፀመዉ ጥቃት «በጣም የሚያሳፍር ነዉ» ይላሉ። ድርጅታቸው ጦርነቱ ሲካሄድባቸው በነበሩ በአማራ ክልል በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። የሴቶችን ጥቃት በቃ ማለት አለብን ይላሉ።

«ጦርነቱ ከተጀመረ በየትኛውም አካባቢ እንዲ ያለ ድርጊት ይፈፀማል። ይህን የሚያደርጉት ህብረተሰቡን ለመጉዳት አንገት ለማስደፋት ሲፈለግ ሌላው ወገን ሴቶችን ነው ሚደፍረው» ያሉት ወይዘሮ ማሪያ በጦርነት ቦታዎች ሴቶችን መድፈርን እንደመሳሪያ ይጠቀሙበታል ብለዋል። «በአገራችን የተፈፀመው በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ነው የተፈፀመው» ብለዋል 

ገነት (የተለወጠ ስም ነዉ) በሀያዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ የራያ አካባቢ ነዋሪ ናት። መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ ም ወደ መኖሪያ ቤትዋ የመጡ ሁለት የህወሓት ወታደሮች ወደሌላ አካበቢ እንደ ወስደዋት እና በአንዱ መደፈርዋን ለዶቼ ቬሌ ተናግራለች። ጥቃቱ ከደረሰባት ሁለት ወራት ቢያልፍም  ባገባደድ ነዉ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ላይ ህክምና አግኝታለች ስለሁኔታው ስትናገር እርስዋ በምትኖርበት አካባቢ በርካታ ሴቶች ላይ የፆዊ ጥቃቱ እንደተፈፀመ የተናገረች ሲሆን የተደፈሩ ሴቶች  ምርመራ ባደረጉበት ወቅት HIV የተያዙ እንዳሉ ተናግራለች። «ከመንግስት ምንም ድጋፍ አላገኘንም። በጣም የተጎዱም አሉ መንግስት ይሄንን ቢያይልን ጥሩ ነው» ትላለች። 

ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር ድርጅታቸው በሰሜኑ ጦርነት ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ድጋፍ ያደርጋል «የህክምና የስነልቦና ድጋፍ እንዲሁም አቅም ግንባታ ድጋፍ እናደርጋለን ምክንያቱም እነዚ ሴቶች ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ናቸው ስለዚህ ከጤናቸው አገግመው ሲሄዱ ቤተሰባቸውን ሚያስተዳድሩበት ገቢ ያስፈልጋል » ያሉት ወይዘሮ ማሪያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ መኖሪያቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

በአፋር ክልል በጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።የመቀሌው ዘጋቢያችን ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ትግራይ ክልል ውስጥ ፆታዊ ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች ለከፋ የጤና፣ ማሕበራዊ እና የኢኮኖሚ ችግር እየተጋለጡ እንደሆነ ከዚ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የዛሬ ታስቦ የዋለዉን ዓለም አቀፍ የፆታዊ ጥቃት ማስወገጃ ዕለትን ምክንያት በማድረግ ናይሮቢ ኬንያ ዉስጥ አዉደ-ትርዒት አዘጋጅቷል።በትርዒቱ ላይ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸዉ ኢትዮጵያዉያን ፍትሕ እንዲያገኙ የሚያጠይቁበት ዘጋቢ ፊልም ይቀርባል።አዉደ ርዕዩ በመጪዉ ሰኞና ማክሰኞ ለንደን፣ ብሪታንያ ዉስጥም ለተመልካች እንደሚቀርብ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት አስታዉቋል።

ማህሌትፋሲል 

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ