1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፌቼ ጫምባላላ-የሲዳማ ህዝብ የአንድነት ምልክት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 19 2015

ሲዳማ ክልል ህዳር 14 ቀን 2012 ዓ.ም በይፋ ከተመሰረተ ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመቱን ይዝዋል። የሲዳማ ህዝብ ዘንድሮ የዘመን መለወጫዉን «ፊቼ ጨንበላላ» በተለይ በድምቀት አክብሯል። ህዝቡ ክልሉን ካገኘ ወዲህ ሁሉ ነገር ሆኖለታል፤ ተሳክቶለታል ማለት አይደለም፤ ቢሆንም ግን ህዝቡ በዓሉን በሰላማዊ መንገድ ማክበሩ ትልቅ ነገር ነዉ።

https://p.dw.com/p/4Qbwv
Äthiopien Fichee-Chambalaalla, Neujahrsfest des Volkes der Sidama
የሲዳማ ማህበረሰብ እና ባህሉምስል Dejene Welde Amanuel

የሲዳማ ማህበረሰብ እና ባህሉ

«ሲዳማ ክልል ህዳር 14 ቀን 2012 ዓ.ም በይፋ ከተመሰረተ ዘንድሮ ሆለተኛ ዓመቱን ይዝዋል። የሲዳማ ህዝብ ዘንድሮ የዘመን መለወጫዉን «ፊቼ ጨንበላላ» በተለይ በድምቀት አክብሯል። ህዝቡ ክልሉን ካገኘ ወዲህ ሁሉ ነገር ሆኖለታል፤ ተሳክቶለታል ማለት አይደለም፤ ቢሆንም ግን ህዝቡ በዓሉን በሰላማዊ መንገድ ማክበሩ ትልቅ ነገር ነዉ።»  አቶ ደጀኔ ወልደ አማኑኤል ዱባለ

ከብት የማይታረድበት፤  ዛፍ የማይቆረጥበት፤  ያጠፉ ይቅር የሚባሉበት በዓል ነዉ።  የሲዳማ የዘመን መለወጫ ፍቼ ጨብበላላ። የሲዳማ አባቶች የጨረቃና የከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት ማህበረሰቡ የዘመን መለወጫ በዓልን የሚያከብርበትን እለት ይፋ ያደርጋሉ።  ጤናይ ስጥልኝ አድማጮች እንደምን ሰነበታችሁ፤ በመግብያችን ላይ ስለሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ በዓል አከባበር እና ስለ ሲዳማ ህዝብ ቋንቋ እና ባህል የነገሩን በዓሉን ለማክበር ከስዊዘርላንድ ወደ ሲዳማ ክልል የተጓዙት አቶ ደጀኔ ወልደ አማኑኤል ዱባለ ናቸዉ።

Äthiopien Sidama New Year Fichee-Chambalaalla
የሲዳማ ማህበረሰብ እና ባህሉምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሲዳማ ማህበረሰብ  በተለይ በቄጣላ ባህላዊ ጭፈራው እጅግ ይታወቃል፡፡ ማህበረሰቡ አንድነቱን ከሚያሳይባቸው ኪነ-ጥበባዊ ክንዉኖች መካከል አንዱ ቄጣላ ነው፡፡ ትከሻ ለትከሻ ሆኖ በጋራ ዜማ የሚከናወነዉ  ጭፈራ፤ በመሪ ዳንሰኞች የሚኃየዉ የዉዝዋዜ  ትወና እና እንቅስቃሴ ተመልካችን ያስደምማል። የማህበረሰቡ አዋቂዎች እንደሚናገሩት በዳንሱ በዜማዉ  ሠላም ፤ አንድነት ይሰበካል፤ አዲሱ ዘመን መልካም ይሆን ዘንድ ምኞት ይገለጽበታል፣ ፈጣሪም ይመሰግነበታል፤ ወቅታዊ ጉዳዮች እና መልክቶች ለማህበረሰቡ ይተላለፉበታል።  ለሲዳማ ህዝብ ነጻነት ለዓመታት በትግል ላይ እንደነበሩ የነገሩን አቶ ደጀኔ ወልደ አማኑኤል ዱባለ፤ የሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ ፌቼ ጨንበላላን ለማክበር ለብዙ ዓመታት ከሚኖሩባት ከስዊዘርላን ወደ አዋሳ ከተማ ተጉዘዋል።

የሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ ፌቼ ጨንበላላላን ለማክበር ቀደም ብሎ ከፍተኛ ዝግጅትን ያደርጋል።  አከባበሩ ከዋዜማ ጀምሮ ይደምቃል፡፡ ጎረቤት ይሰበሰባል፤ ከእንሰት የሚዘጋጀውን ቡርሳሜ ተብሎ የሚጠራ ምግብን ያዘጋጃል፤  በወተት ይመገባል። ስጋ የሚባል ነገር ከቤት ይወጣል። ሲዳማ ከአንድ ዓመት ወደሌላው የሚሸጋገርበት ሂደት ሁሉቃ ይባላል። ሁሉቃ ማለት ከሸምበቆና ከአርጥብ ቅጠል ተሠርቶ የሚቆም ነገር ነው። በዚህ እለት ሰዎች በዚህ በተሰራ በኩል ያልፋሉ። በእለቱ በሲዳማ ከብቶች ሳይቀሩ ደስ ብሏቸዉ እንዲዉሉ ይደረጋል፡፡ ቀድም ብሎ በተዘጋጀላቸው ግጦሽ ቦታም ይሰማራሉ፣ በእለቱ እንስሳት አይመቱም፣ አይታረዱም፣ ዛፍ አይቆረጥም፤ ያጠፉም ይቅር የሚባሉበት እለት ነዉ  ሲሉ አቶ ደጀኔ  ወልደ አማኑኤል ዱባለ በሲዳማ በዓል ዋዜማ የሚከናወነዉ የአከባበር ሂደት አስረድተዋል።

Äthiopien Fichee-Chambalaalla, Neujahrsfest des Volkes der Sidama
የሲዳማ ማህበረሰብ እና ባህሉምስል Dejene Welde Amanuel

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በቅርስነት የመዘገበው የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፌቼ ጨንበላላ ክብረ በዓል  መቼ እንደሚዉል  የሲዳማ ሽማግሌዎች ማለትም አያንቶች በኮከብ ቆጠራ እለቱን አዉቀዉ በአያንቱዎች አዋጅ መሰረት በዓሉ በየዓመቱ የሚከበርበት ቀን ይቆረጣል። ቀኑ የሚገለጸው በላላዋ ነው።  ላላዋ በሲዳማ የመረጃ መለዋወጫ ስልት ነዉ። ጨምባላላ ከመድረሱ አንድ ሳምንት ቀድም ብሎ  የዘመን መለወጫዉ እለት በዚህ  ቀን ይውላል የሚለው መረጃ በየገበያው ይገለጻል፡፡ አቶ ደጀኔ ወልደ አማኑኤል ዱባለ፤ ጨመንበላላ መከበር የጀመረዉ መቼ እንደሆን እስካሁን በጥናት የተገለፀ ነገር ባይኖርም ፤ ፊቼ ጨንበላላ የሲዳማ ጥንታዊ በዓል ነዉ፤ ሲሉ ተናግረዋል።

የሲዳማ ዘመን መለወጫ የሲዳማ ማህበረሰብ ጋር የተያያዘ እና ጥንታዊ ነዉ ያሉን ሌላዉ በአዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና የሲዳማ ባህል ዘርፍ ዳይይሬክተር አቶ ተፈራ ሌዳሞ ናቸዉ።

የራሱን ክልል ከመሰረት ሁለት የሆነ የሲዳማ ህዝብ ለሲዳማ ህዝብ ዘንድሮ ፌቼ ጨንበላላን ሲያከብር ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ። ያሉን የሲዳማ ህዝብ መብት ተቆርሪ አቶ ደጀኔ ወልደ አማኑኤል ህዝቡ ክልልሉን ካገኘ ወዲህ የፈለገዉ ነገር ተሟልቶለታል ማለት አይደለም ቢሆንም በዓሉን በሰላማዊ መንገድ አክብሯል ብለዋል።

Äthiopien Fichee-Chambalaalla, Neujahrsfest des Volkes der Sidama
የሲዳማ ማህበረሰብ እና ባህሉምስል Dejene Welde Amanuel

በሲዳማ ክልል በገጠር ትምህርት ቤቶች እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ትምህርት የሚሰጠዉ በሲዳመኛ ቋንቋ ነዉ ያሉን የሲዳማ ክልል የባህል ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሌዳሞ፤ ከስምንተና ክፍል በኋላ ተማሪዎች እንደምርጫቸዉ አማርና ኢንጊሊዘኛን ጨምሮ ሌሎች ቋንቋዎችን ይማራሉ።

አድማጮች በዚሁ ቃለ ምልልስ የሰጡንን የሲዳማ ህዝብ መብት ተቆርቋሬ አቶ ደጀኔ ወልደ አማኑኤል ዱባለን እና የሲዳማ ባህል ዘርፍ ዳይይሬክተር አቶ ተፈራ ሌዳሞን በማመስገን፤ ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ   

ነጋሽ መሐመድ