1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ፌስቡክ የሚሸጥልን መልሶ የሚገድለን ላለመሆኑ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል»

ዓርብ፣ ሰኔ 17 2014

ፌስቡክ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ንግግሮችን በአግባቡ ባለመቆጣጠር ብሔር ተኮር ጥቃቶች እንዲስፋፉ አስተዋፅዕ እያደረገ እንደሆነ በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት አመላክቷል። ትልቁ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ይህን ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ምን መደረግ ይኖርበታል? የተጠቃሚው ሚናስ ምን ሊሆን ይገባል?

https://p.dw.com/p/4DAOx
ምስል imago images/Steinach

«ፌስቡክ የሚሸጥልን መልሶ የሚገድለን ላለመሆኑ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል»

ከቅርብ አመታት ወዲህ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ውጪ በሌሎች የተለያዩ ቋንቋዎች በኦንላይ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችን መለየት የተመራማሪዎችን ቀልብ ስሷል።  ስትራቴጂክ ዲያሎግ የተባለ ተቋም ለሁለት ዓመት ያህል ጥናት ካደረገ በኋላ ባለፈው ሳምንት ይፋ እንዳደረገው ፌስቡክ እስላማዊ መንግሥት ወይም ISIS የተባለውን እና  የሶማሊያ የሚገኘዉን የአልሸባብ ቡድንን ስም በግልፅ እየጠሩ የሚደግፉ እና የአመፅ ጥሪ በአረብኛ ፣ ስዋሂሊ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎች የተጠለፉ መልዕክትቶ በስፋት እንዲጋሩ ፈቅዷል።
እንዲሁ ግሎባል ዊትነስ እና ፎክስ ግሎቭ የተባሉ ሁለት የብሪታንያ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቅርቡ በአማርኛ ቋንቋ በፌስቡክ የተሰራጩ መልዕክቶችን ፈትሸው ይፋ እንዳደረጉት ፌስ ቡክ ግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ንግግሮችን በአግባቡ እየተቆጣጠረ አይደለም።  ድርጅቶቹ ይህንንም የፈተሹት በአማራ፣ በትግሬ እና በኦሮሞ  ብሔሮች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግሮችን ወደ ፌስቡክ በመላክ ነበር። ከድርጅቶቹ ጋር አብረው የሰሩት የመረጃ ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ዳግም አፍወርቅ ፌስቡክ እንዴት በቀላሉ ፍተሻውን እንደወደቀ ለብራስልሱ የዶይቸ ቬለ ወኪል ገበያው ንጉሴ አብራርተዋል። « በጣም የከፉ፣ ሰዎች እንዲገደሉ የሚቀሰቅሱ ፣ በጣም አፀያፊ የብሔር ስድቦችን ያካተቱ 12 የጥላቻ ንግግሮችን ነበር ይመረጥነው እና ለፌስቡክ ያሳለፍነው። ፌስቡክ ገምግሞ የተከፈለውን የማስታወቂያ ክፍያ ተቀብሎ አሳለፋቸው።» መልዕክቶቹ ግን ግልፅ የሆኑ እና ለትርጉምም የማያሻሙ የጥላቻ ንግግሮች እንደነበሩም ተገልጿል።
ድርጅቶቹ የጥላቻ ንግግሮቹን በማስታወቂያ መልክ ፌስ ቡክ ላይ ለመለጠፍ የፈለጉት በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ አቶ ዳግም ይናገራሉ። አንዱ ምክንያት በማስታወቂያ መልክ የሚላኩ መልዕክቶች የበለጠ ትኩረት እንደሚያገኙ እና በቅድሚያ ፌስቡክ ከፈተሻቸው በኋላ ለመለጠፍ ፍቃድ ስለሚያገኙ ሲሆን ሌላው ደግሞ መልዕክቶቹ ወደፊት የሚለጠፉበትን ቀን መምረጥ ስለሚያስችል ፤ እና መልዕክቶቹ ሌሎች ተጠቃሚዎች ጋር ከመድረሱ በፊት መልሶ መሰረዝ ስለሚያስችላቸው ነበር። ይሁንና ፌስቡክ ፈተናውን ወዲያው ወድቋል። መልዕክቶቹም ዞረው እንደነመስፍን ያሉ ተጠቃሚዎች ጋር ይደርሳል።« እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ። ጭፍጨፋ ያለባቸውን ነገሮች የማየው በፌስ ቡክ ነው። የሚታየው ነገር ፅንፍ የረገጠ ነው። መፍትሔ ለመስጠት ሳይሆን ሀገሪቷ እንድትፈራርስ የሚያደርጉ መልዕክቶች ናቸው የሚተላለፉት» መስፍን የተለጠፉት አስተያየቶች ግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ንግግሮች እንደሆኑ ለፌስቡክ በማሳወቅ ጫናውን ማጠናከር ይቻላል ይላል። በርግጥ መፍትሔ ነው ወይ? ሌላው ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያን በሚመለከት ጥናት ያካሄዱትም ግሎባል ዊትነስ እና ፎክስ ግሎቭ ድርጅቶች ፌስቡክ ኃላፊነቱን ለምን እንዳልተወጣ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀው ነበር።  ድርጅቱ ስህተቱን ተቀብሎ ማሳለፍ እንዳልነበረበት አምኗል። ይሁንና ይቅርታ ከጠየቀም በኋላ የተላኩ መልዕክቶችን ማስቆም አልቻለም። 
ሌላው ኢትዮጵያዊ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ድንቁም የታዘበው ይህን ነው።  እሱ እንደሚለው ፌስቡክ አንዳንዴ መልዕክቶቹን የማይሰርዘው ገለልተኛ የሆኑ ተቀጣሪዎች ስለሌሉት ነው። ለዚህም የውስጥ አዋቂ መረጃ አለኝ ይላል። « በተለያዩ ቋንቋዎች የተቀጠሩት የፌስቡክ ሙያተኞች ቋንቋውን እንኳን በደንብ የሚችሉ አይደሉም። ሲቀጥል ደግሞ አንዳንዶቹ ተቆጣጣሪዎች ገለልተኛ አይደሉም። እንዲህ እናደርጋለን ብለው እዛ የነገሩኝ ሰዎች ስለነገሩኝ ነው።»
የጥላቻ ንግግርን በነፃ እና በፍጥነት ከማሰራጨት አንፃር እንደ ዘመን አመጣሹ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያክል ነገር የለም። ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ህዝብ 10 በመቶ ያህሉ ብቻ ቢሆንም የፌስቡክ ተጠቃሚ የሆነው መረጃው ግን በፍጥነት ለሌሎች ይሰራጫል። ስትራቴጂክ ዲያሎግ የተባለ ተቋምም በጥናት የደረሰበትን ውጤት ለፌስቡክ ገልፆ ምላሽ ጠይቆ ነበር። የሽብር ቡድኖችን ከሚደግፉ እና የአመፅ ጥሪዎችን ከሚያበረታቱ 445 የግለሰብ ገፆች መካከል የተወሰኑትን ገፆች ፌስቡክ አግዷል። ለጥናት ተቋሙ በፁሁፍ በሰጠውም ምላሽ ስም ሳይጠቅስ« አሸባሪ ቡድኖች ፌስቡክን እንዲጠቀሙ አንፈቅድም። እነዚህን ድርጅቶች የሚያወድሱ ወይም የሚደግፉ ይዘቶችንም እናስወግዳለን። ይህንንም የሚያደርጉ ልዩ ቡድኖች አሉን።» ማለቱን አስታውቋል። ተቺዎች የፌስቡክ የይዘት ቁጥጥር ስጋት አለማቀፋዊ ችግር ነው ይላሉ። የኬንያ አስተዳደር፣ የሰላም አማካሪ የሆኑት ሊያ ኪማቲ  ተጠቃሚዎች ሁሉ ሚና መጫወት እንደሚችሉ እያሳሰቡ «ፌስቡክ ነጋዴ ነው፤ የሚሸጥልን ነገር ግን እኛን መልሶ የሚገድለን ላለመሆኑ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል» ይላሉ።
የግሎባል ዊትነስ እና ፎክስ ግሎብ ጥናትስ የመፍሔ ሀሳብ ምን ይሆን?  አቶ ዳግም በርካታ ነጥቦችን ያነሳሉ« ጥናቱ በዋናነት እንደ መፍትሔ ሀሳብ ያስቀመጠው ፌስቡክ ተጨማሪ ሰዎች መቅጠር እንዳለበት፣ በሌሎችም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጭምር ቴክኖሎጂውን አዳብሮ ዘር ተኮር መልዕክቶች እንዲጠፉ እንዲያደርግ ነው። ፌስ ቡክ ትንሽ ጫና ይፈልጋል።  አለም አቀፍ ተቋሟት ጫና ማድረግ አባቸው። » ከዚህም ሌላ ፖለቲካው ላይ እና የሀገሪቱ ሰላም ላይ መስራት መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

Symbolbild I Facebook
ምስል Beata Zawrzel/NurPhoto/imago images
Illustration Fäuste mit Smartphone zum Protest
ምስል oxinoxi - stock.adobe.com

ልደት አበበ 

ነጋሽ መሀመድ