1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፆም በወጣቶች ዘንድ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 22 2013

የዘንድሮዉ የሚያዚያ ወር ኢትዮጵያ ውስጥ ትላልቅ የሚባሉት የክርስትና እና የእስልምና ሐይማኖት ፆሞች የገጠሙበት ወር ነው። ህፃናት እና ወጣቶችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይፆማሉ። በወጣቶች ዓለም ዝግጅት ያነጋገርናቸው የእምነቶቹ ተከታዮች እንደገለፁልን፤  ወጣቱ ከመቼውም በላይ ፊቱን ወደ ፈጣሪው ያዞረ ይመስላል። ምክንያቱንም ነግረውናል።

https://p.dw.com/p/3slKD
Symbolbild Religion Islam Christentum Religiöse Symbole auf Kirchtürmen und Minaretten in Beirut, libanon
ምስል AP

ፆም በወጣቶች ዘንድ

ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ  የሚፆመው የአቢይ ፆም ሊፈታ የአንድ ቀን እድሜ ያህል ቀርቶታል። በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ደግሞ ታላቁ ፆም የሆነው የረመዳን ፆም ተጋምሷል። ታድያ ይህ የሚያዚያ ወር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የፆም እና የፀሎት ወቅት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለመሆኑ ወጣቱ እንዴት እየፆመ ይገኛል? ጀማል ሙስጦፋ በራያ ቆቦ የሚኖር ወጣት ነው። « ፆም ማለት ለኔ ጥሩ ነገር መስራት ነው። » ይላል።  ትዕግስት ከበደ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ናት። ለእሷ ፆም ማለት ስጋን ማድከም፣ ራስን ለፀሎት ማዘጋጀት ነው።  የዘንድሮውን ፆም ተረጋግተን መፆም አልቻልንም የምትለው ትዕግስት በሰሜን ሸዋ ፤ ሸዋ ሮቢት ነዋሪ ናት። « እኛ አካባቢ ነው ችግሩ ያለው። » ለፀሎት ወደ ቤተ ክርስትያን ለመሄድ እንኳን የሚያስፈራ ሁኔታ ነው ያለው ትላለች። ጀማልም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት በፆም ፀሎቱ ላይ ጫና መፍጠሩን ነው የነገረን። እሱም በሚኖርበት አካባቢ አለመረጋጋት አለ። « ራያ ቆቦ የትግራይ ክልል ተብሎ የከለሉት አካባቢ ነው። አልፎ አልፎ መብራት ሲጠፋ ጥይትም ይተኮሳል። እና ስናፈጥር ጥሩ ያልሆነ ስሜት አለው።» ጀማል ብዙውን ጊዜ መብራት የሚጠፋው ዝናብ ሲዘንብ እንደሆነ ገልፆልናል።  ሌላው ጀማል ዘንድሮ በአካባቢው የታዘበው ነገር ሁሉም ወጣት እየፆመ መሆኑን ነው። « ከሁለት ሶስት ዓመት በፊት ሙስሊም ሆነው የማይፆሙ ወጣቶች አይ ነበር። ዘንድሮ ግን ሁሉም ይፆማል።» ይህ ብቻ አይደለም። ለማፍጠሪያ ወይም ሱውር ማድረጊያ ምግብ የሌላቸው እና መጠለያ የሌላቸው የሚፆሙ ወጣቶች ጀማልን ገጥመውታል።  ትዕግስትም ብትሆን ዘንድሮ ከወትሮው የተለየ የሚፆሙ ወጣቶች እና ህፃናትን ታዝቤያለሁ ትላለች። « ጦርነቱም፣ ኮቪዲም የፈጠሩት ነገር ይመስለኛል። ሰው መፍትሄው ወደ አምላክ መጮሁ ብቻ አማራጭ እንደሆነ አድርጎ ስላመነ ይመስለኛል።»

ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል አለሙ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የስነ ምግብ ተመራማሪ እና መምህር ነው። የ 34 ዓመቱ ወጣት መምህር ፆምን የሚያየው ከሌሎቹ ወጣቶች በተለየ በሁለት አይነት መንገድ ነው።  አንደኛው ከእምነት አንፃር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሳይንስ አንፃር ነው። « በፆም ወቅት የምንመገባቸው ምግቦች ለጤንነት የተሻሉ ምግቦች ናቸው።» ዳንኤል ከልጅነቱ ጀምሮ ይፆማል።  ልክ እንደሱ የሚፆሙ የክርስትና እና የእስልምና ዕምነት ተከታይ ወጣቶች የሚያስተምርበት ክፍል ውስጥ ይገጥሙታል። ታድያ ይህ የፆም ወቅት በወጣቶች ላይ የተለየ ድክመት ወይም ለውጥ ፈጥሮ ይሆን? ዳንኤል ምንም ያስተዋልኩት ነገር የለም ይላል። « በፍቃደኝነት፣ በረከት አገኝበታለሁ ብለው የሚያደርጉት ነገር ስለሆነ እንደሆነ ደስ ነው የሚለው። ድካምም ተሰምቶኝ አያውቅም።»ጀማል እና ትዕግስት በዚህ በፆም ወቅት እንደየእምነታቸው ወደ ቤተ እምነቶች  በመሄድ ይጸልያሉ። አለም አቀፍ ወረርሽኙ ኮቪድ 19 እነሱንም ሆነ የአካባቢያቸውን ነዋሪዎች ከዚህ የልገደባቸውም። 

Äthiopien Feierlichkeiten Ramadan
የረመዳን አከባበር በአዲስ አበባ 2007 ዓ ም ምስል DW/G. Tedla
Äthiopien Orthodoxes Weihnachtsfest in Addis Abeba
በርካታ ወጣቶች ጊዜያቸውን በፆም እና በፀሎት ያሳልፋሉ። ፎቶ 2010 ዓም አዲስ አበባምስል picture-alliance/abaca/M. W. Hailu

ጀማል የእንጨት ስራ ባለሙያ ነው። በረመዳን ፆም ምክንያት ግማሽ ቀን ይሰራል፣ ግማሽ ቀኑን ደግሞ በመተኛት ያሳልፋል። ወጣቱ ቀደም ሲል እንደገለፀልን በዚህ የፆም ወቅት በተለይ ለሌሎች በጎ ነገር የያደርጋል። እሱ ግን « ሰደቃ አይነገርም» በሚል ለሌሎች ስለሚያደርገው ድጋፍ ዝርዝር ውስጥ ባይገባ ይመርጣል። መፆም ለግል ብቻ ሳይሆን ለህዝቡም ጥሩ ነገር እንደሚፈጥር ዳንኤልም ያምናል። በተለይ በዚህ በፆም ወቅት ሁሉም እንደየእምነቱ ፆም እና ፀሎቱን ቢያጠናክር ጥሩ ነው የሚል እምነት አለው። « በፆም ወቅት ሰዎች ከመጥፎ ነገር የሚቆጠቡበት ወቅት ነው። ሰዎች ሁሉ ቢፆሙ ፣ በያሉበት ሀይማኖት ቢጠነክሩ አሁን የምናያቸው አይነት ችግሮች የመፈጠራቸው እድላቸው በጣም አነስተኛ ነው።»
ዳንኤል በሚኖርበት ሐሮማያ አካባቢ በተለይ የሁለቱ ትላልቅ ሐይማኖት ፆሞች በአንድ ወቅት መግጠማቸው ፤ አንዳቸው ለሌላቸው ይበልጥ እንዲተሳሰቡ እንዳደረጋቸው ይናገራል። ይህም ነገር አስደስቶታል። « አንዱ አንዱን እያከበረ ያሳለፍንበት ሁኔታ ነው።»
ትዕግስት በምትኖርበት ሸዋ ሮቢት በዚህ የፆም ወቅት እንኳን በብሔር ማንነት ላይ መሠረት ያደረገው ጥቃት ጋብ አለማለቱ ያሳስባታል። በዚህም የተነሳ የበዓል ድባቡ የለም ትላለች።ይልቁንስ የሚታየው « ሰዎች እቃ ጭነው ወደ ሌላ ቦታ ሲያጓጉዙ ነው» 

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ