1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጾታዊ ጥቃትን የመከላከል ዘመቻ በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ ኅዳር 24 2014

በሴቶች እና ልጃ ገረዶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ናቸው።ጥቃቱን በመቃወም በመላዉ ዓለም በየዓመቱ ለ 16 ቀናት የሚዘልቅ ዘመቻ ይካሄዳል።የዘንድሮዉ ዘመቻ ከተጀመረ ዛሬ  9ኛ ቀኑ ነዉ።በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅታችን በኢትዮጵያ በሚደረገው ዘመቻ ላይ እናተኩራለን።

https://p.dw.com/p/43mh0
Äthiopien Gender Gewalt Aktivismus
ምስል B.Yergalem

ጾታዊ ጥቃትን የመከላከል ዘመቻ በኢትዮጵያ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዲስ ባወጣዉ ጥናት በተለይ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ልጃ ገረዶች ቁጥር ከፍ ብሏል። ወረርሽኙ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በ 13 ሀገራት ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ከሶስት ሴቶች ሁለቱ ወይ በራሳቸው ወይም በሚያውቋት ሴት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ይናገራሉ። ኢትዮጵያዎቷ ተማሪ ሜሮንን ይህ አሀዝ ብዙም አያስደንቃትም።  ገጠመኟን ስትናገር አንድ ወደድኩሽ የሚላት ልጅ ትምህርት ቤት ስትሄድ ይከታተላት እና ያስፈራራት ነበር። « ይሄ ነገር ሲበዛ ለእናቴ ነገርኳት እና እሷ አስቆመችልኝ» የምትለው ሜሮን ከእናቷ ጋር በግልፅ ማውራቷ ጠቅሟታል። የሜሮን ጓደኛ የሆነችው ዳግማዊትም ብትሆን መንገድ ላይ አላሳልፍ የሚሉ ወንዶች ገጥሟት ያውቃል። 
«እንደ መብት ቆጥረውት በመንገድ ላይ ስንሄድ ይለክፉናል። እህቴን እንደውም ሱቅ ሄዳ በሳይክል ከበዋት መፈናፈኛ አሳጧት እና ድንጋይ አንስታ ነው ራሷን የተከላከለችው»
መብትን የሚጋፈጡ ወንዶች ሲመጡ መጋፈጥ እና አለመፍራት ያስፈልጋል እያለች ሌሎች ሴቶችን የምታበረታታው ዳግማዊት ጥቃት ቢደርስባት ግን ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄዷን ትጠራጠራለች። « ለፖሊስ ብናገር ዋስትና አለኝ ብዬ አላስብም።  ቀጣይ ለኔ ከለላ ይደረግልኛል? ብቻ ተመልሶ ጥቃት የሚደርስብኝ ይመስለኛል።»ይህ የዳግማዊት ስጋት ብቻ አይደለም።

Äthiopien 16 Tage Aktivismus gegen geschlechtsspezifische Gewalt
የጣምራ ለማህበራዊ ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ብሩክ ይርጋለምምስል B. Yergalem

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት ከ 10 ሴቶች አንድ ሴት ብቻ ናት ደፍራ ፖሊስ ዘንድ ሄዳ የምታመለክተው። ስለሆነም በተለይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ያሻል።ይህ በወጣት ሴቶች ዘንድ ያለው ስጋት እንዲቀረፍ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ይሰራሉ። ከእነዚህ አንዱ ጣምራ ለማህበራዊ ልማት ድርጅት ሲሆን ይህም ግብረ ሰናይ ድርጅት ሰሞኑን በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት በየዓመቱ ለ16 ቀናት በጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን ለመከላከል በሚያካሂደው ዘመቻ  ተካፍሎ ነበር። የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ብሩክ ይርጋለም ተሷትፎዋቸው ምን ይመስል እንደነበር ያስረዳል። « ያንን አስመልክቶ አዲስ አበባ ከተማ ላይ አንድ ትምህርት ቤት ላይ ዘመቻውን አስጀምረናል። በዕለቱ ዕለት ኖቬምበር 25 አስጀምረናል።» በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ጥቃት የሚፈፀሙባቸው ተብለው አዲስ አበባ ውስጥ ከተለዩ አካባቢዎች አንዱ በሆነው አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሚገኝ የካቲት 13 ትምህርት ቤት ውስጥ በተዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ ተማሪዎች  ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ማቅረብ የቻሉበትና ስለሚታዘቡት ፆታዊ  ጥቃቶች የገለፁበት አጋጣሚ ተፈጥሯል ይላል ብሩክ፤ ምሳሌዎችን እየጠቀሰ፤ «  የሚደርስባቸውን መለከፍ፣ መመታት ከዛም አልፎ እስከ መደፈር አባብሎ ያላልተገባ ነገር የማድረግ ነገር እንዳለ አንስተዋል። አላስፈላጊ አካሎቻቸውን መነካካት እንደሚደርስባቸው አንስተዋል።»ገና የ8ኛ ክፍል ተማሪ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ እየሰራ የሚገኘው ብሩክ  ከሁለት አመት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ስር ወንድ ሆነው ለሴቶች መልካም ነገር ለሚሰሩ ሰዎች የሚሰጠውን እውቅና ሊያገኝ ችሏል።በሴቶች እና ልጃ ገረዶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን ለማስቆምም የወንዶች ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ይናገራል። በዋናነትም ቤተሰብ፣ የእዕምነት ተቋማት እና ትምህርት ቤቶችን ይጠቅሳል።
ወይዘሮ አበባ ዘውዴ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ  የስርዓተ ፆታ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ናቸው። እሳቸው የሚሰሩበትም መሥሪያ ቤት በዓለም ዙሪያ በሴቶች እና ልጃ ገረዶች ላይ ስለሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሚደረገው ዘመቻ ላይ ተካፍሏል። « ጸረ ጾታዊ ጥቃትን ከህዳር 16 እስከ 30 ድረስ (እኢአ) እያከበርን ነው። ያለፈው ዓመት የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ነው ያከበርነው። ዘንድሮ ደግሞ የወንዶች ትምህርት ቤት እያከበርን ነው።»  የሚሉት ወይዘሮ አበባ በየትምህርት ቤቱ የሥርዓተ ጾታ ክበብ ተጠሪ እንዳላቸው እና ስልጠና እንደሚሰጥ ይናገራሉ።  ከዚህም ባሻገር «ቅዳሜ ቅዳሜ የስርዓተ ፆታ ትምህርት በራዲዮ እናስተላልፋለን» የሚሉት ወይዘሮ አበባ ስልጠና በሚሰጥበት ጊዜም መልዕክቱ ለወላጅ በሚደርስበት መልኩ ስለሆነ ስለ ፆታዊ ጥቃት በወላጅ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ከፍ ብሏል ይላሉ።  የስርዓተ ፆታ ዳሬክተሯ ለዶይቸ ቬለ እንደገለፁትም ጉዳዮን ህግ ጋር የሚያደርሱት ሴቶች ቁጥር ጨምሯል። 

Äthiopien HeForShe UN Woman Botschafter Biruk Yergalem
ምስል B. Yergalem

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ