1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጾምና ፈተናው በተፈናቃዮች መጠለያ

ሰኞ፣ መጋቢት 23 2016

ከተለያዩ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች አስፈላጊውን የምግብ ግብዓት ማግኘት ባለመቻላቸው አሁን በክርስቲያኑም ሆነ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ያለውን ጾም ከባድ እንደሆነባቸው ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/4eJog
የተፈናቃዮች መጠለያ
ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያምስል Zinabu Melese/DW

 

በዚህ ዓመት ታላላቆቹ የዐቢይ እና የሮመዳን አጽዋማት መጋቢት መጀመሪያ ላይ በተመሳሳይ ቀን ተጀምረዋል። የዓቢይ ጾም በዋናነት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለ55 ቀናት የሚጾም ረጂሙ የጾም ጊዜ ነው።  የሮመዳን ጾም ደግሞ ለ30 ቀናት የሚዘልቅና በእስልምና እምነት ተከታዮች  ዘንድ ይጾማል።

ከጾም በኋላ በስግደትና በጸሎት ደክሞ የዋለን ሰውነት የየእምነቱ ተከታዮች እምነቱ በሚፈቅድላቸው ሰዓት ምግብ እንዲወስዱ ይደረጋል። የዚህን ዓመት ጾም በተመለከተ በነበሩ ግጭቶች ከኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን አነጋገረናል።

ቤተክርስቲያን
ተፈናቃዮቹ ኑሮው ከጾሙ ጋር ከብዷቸዋል። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ተፈናቃይ ከጾም በኋላ ያለው ነገር በጣም ከባድ ነው፣ በቤታችን እንደለመድነው አይደለም ብለዋል።

«... በጣም ይከብዳል፣ ጾም ለተፈናቃይ ከባድ ነው ከዚሀ ባገኘሀት በደረቅ ነገር እያፈጠርክ የለመድከው ነገር መቼም አይገኝም፣ በደረቅ ምግብም ቢሆንም እየጾምን ነው። ያለንበት በረሀ በመሆኑ ውሀ ጥም አለው፣ ፀሐይ አለው፣ እንደገና ጾም ውለህ ማታ የምታፈጥርበት ደረቅ ነገር ነው» ሲሉ ገልጠዋል።

በመጠለያ ጣቢያው የእስልምናም ሆነ የክርስትና ተከታዮች ከድንኳን የተሰሩ መስኪዶችና ቤተክርስቲያኖች ቢኖሩም ከጾም፣ ከስግደትና ከአገልግሎት በኋላ የሚበላ ነገር የለም ያሉን ደግሞ አንድ የክርስትና እምነት ተከታይ አባት ናቸው። መጠነኛ የሆኑ ቤተ እምነቶች በመጠለያ ጣቢያው እንደሚገኙ ጠቅሰው ሙስሊም ወነደሞችና እህቶች  ሲፆሙ ውለው የሚያፈጥሩበት ነገር የላቸውም ነው ያሉት፣ ክርስቲያኑም ቢሆን ከቤተክርስቲያን በኋላ እንደነገሩ ደረቅ ነገር ነው ከመጠለያ “ቤቱ” የሚጠብቀው ነው ያሉት፡፡

ዘንድሮ ከተፈናቃዩብዛት አንፃርም ይሁን እርዳታ ሰጪዎቹ ከመሰላቸታቸው አይታወቅም፣ ማፍጠሪያም ሆነ መግደፊያ  የሚባል ነገር የለም ሲሉ ሌላ የጃራ ተፈናቃይ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኝ እንደሆኑ የነገሩን በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ የተፈናዮች ጣቢያ የሚገኙ አባትም አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

መስጊድ
ተፈናቃዮቹ በጾም ወቅት ማፍጠሪያ እንደወትሮው አላገኙም። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

«ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ጾማችን አንድ ቀን ገባ፣ ጾሙን ለመቀበል ስጋ ሳንበላ፣ በውሀ ተቀብለነዋል፣ ሙስሊሙ ሲጾም ውሎ ማፍጠሪያ አጥቶ፣ ክርስቲያኖች በ9 ሰዓት ከቤተክርስቲያን ስንመለስ፣ ሲቀድሱ፣ ሲወድሱ  ውለው ካህኖች ሲወጡ የቅዳሴ ማብረጃ የላቸውም፣ ጾማቸውን ነው የሚወጡ፣ እኛም ከቤተክርስቲያን ተመልሰን ያገኘናትን ጥሬም አገኘን ውኃ በዚያች ነው የምንገድፍ፣ የቤታችን ማዕረግ ድሮ ቀርቷል።»

በዚሁ በሐይቅ የተፈናቃዮች ጣቢያ የሚገኙ ሌላ ተፈናቃይ ችግሩ በጣም ከባድ መሆኑን አመልክተው ሆኖም ሰሞኑን የአካባቢው ነዋሪዎችና አዲስ አበባ የሚገኙ ወገኖች የእርድ እንስሳትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል።

በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በነበሩ ግጭቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ይገኛሉ። በቅርቡ የአማራና የሮሚያ ክልል መንግስታትና ሌለች አካላት በደረሱበት ስምምነት መሰረት የተወሰኑ ተፈናቃዮች ወደ ኦሮሚያ መመለሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ