1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ከ50 በላይ ተፈናቃዮች ከርሀብ ጋር ሕይወታቸው ማለፉ

ረቡዕ፣ ኅዳር 19 2016

ከአንድ ዓመት በፊት ከምሥራቅ ወለጋ ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ቻግኒ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ወገኖች ከእርዳታ እጦት ጋር በተያያዘ የበርካቶች ሕይወት ማለፉን አመለከቱ። የከተማ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት እርዳታ ለተፈናቃዮቹ እየደረሰ አይደለም ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4ZaVS
ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች
ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ምስል Alemenw Mekonnen/DW

ተፈናቃዮች ለረሀብ መጋለጣቸው

 

በተለያዩ የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ክልሎች ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች በተለይም ከ2008 ዓ ም ጀምሮ ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ብዙዎቹ ሕይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች ደግሞ የተወለዱበትንና የአደጉበትን አካባቢ እየለቀቁ ተፈቅለዋል፡፡ በ2015 ኅዳር ወር ላይ ከምሥራቅ ወለጋ ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ቻግኒ ከተማ ከሚገኙ መካከል አንዳንዶቹ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ግንቦት ወር ላይ ከተሰጣቸው 15 ኪሎ ቦቆሎ ውጪ እስካሁን እርዳታ አላገኙም፣ በዚህም ምክንያት ከርሀብ ጋር በተያያዘ ከ50 በላይ ሕጻናትና አዛውንቶች ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል፡፡

የከተማው ኅብረተሰብ እስካሁን ይረዳቸው እንደነበር የሚናገሩት ተፈናቃዮችወደ ነበሩበት ለመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም በወለጋ አሁን ያለው ሁኔታ ብዙም የተለወጠ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት «በከፍተኛ ርሀብና በሽታ ላይ በመሆናችን መንግሥት ይድረስልን» ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የቻግኒ ከተማ አስተዳደር ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ የሱፍ ሁሴን ተጠይቀው ተፈናቃዮቹ በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሆኑና እርዳታ እንዲደርስ ለሚመለከተው ማመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡ የሚኖሩበት አካባቢም በፈራረሱና በጅምር ቤቶች ውስጥ በመሆኑ ርሀብና በሽታ እያጠቃቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና መርሃግብር ማስተባበሪያ ኮሚሽን
የአማራ ክልል የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና መርሃግብር ማስተባበሪያ ኮሚሽንምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ አረፈው በቀለ በክልሉ ባለው የሰላም መደፍረስ መንገዶች በመዘጋጋታቸው እርዳታ ማድረስ እንዳልተቻለ በመግለጽ፤ ከርሀብ ጋር በተያያዘ የ55 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እንደሚያውቁም አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ «የዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያዎች በሚጠይቁት መሰረት እርዳታ ይላካል» ብለዋል፡፡ ሆኖም ዞኖች ወደ ተፈለገው አካባቢ እርዳታ ለማድረስ የመንገዶች መዘጋጋት እንቅፋት ሊሆባቸው እንደሚችል አመልክተዋል። በአማራ ክልል ከ600 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ሲገኙ ከ300 ሺህ በላይ ደግሞ ባሉበት ቀየ የሚረዱ ናቸው፡፡

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ