1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጫማ ጠራጊው መሀንዲስ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 1 2013

በኢትዮጵያ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም፤ በዚያው ልክ ግን ተመርቀው ያለስራ ሚቀመጡ ወጣቶች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ይነገራል። ከነዚህም ውስጥ ወጣት ይኄይስ ቻሌ አንዱ ነው። ወጣቱ ክጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ በዉሃ ምህንድስና በጥሩ ውጤት የተመረቀ ቢሆንም፤በሙያው ስራ ባለማግኘቱ ጫማ በመጥረግ ነው የሚተዳደረው።

https://p.dw.com/p/3rl9N
Äthiopien Bahirdar | Yiheyis Chale, Ingenieuer als Schuhreiniger
ምስል privat

ጫማ ጠራጊው መሀንዲስ


በኢትዮጵያ የስራ አጥነት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል።በዚህ የተነሳ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶች ያለስራ አመታትን ማስቆጠር እየተለመደ መጥቷል። ከነዚህም ውስጥ ወጣት ይሄይስ ቻሌ አንዱ ነው። ወጣቱ ከሁለት ዓመት በፊት በጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ በዉሃ ምህንድስና በጥሩ ውጤት የተመረቀ ቢሆንም፤በተማረበት ሙያ ስራ ማግኘት ግን አልቻለም። 
«የዚያን ሰዓት የነበረኝ ስሜት በተመረኩበት የትምህርተ ዘርፍ ተቀጥሬ እሰራለሁ። ስራ ይዛለሁ የሚል ነበር ።ከተመረቅን በኋላ ያው የሀገሪቱ ያለመረጋጋት ሁኔታ ቅጥር በየቦታው እንደዱሮው  የለም። በማንኛውም ክልል ተንቀሳቅሰን ተቀጥረን ለመስራት አልቻልንም ።በክልላችን ም ብዙ ስራ እየወጣ አይደለም። »ነው ያለው።
ወጣቱ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ከትውልድ ቀየው ደቡብ  ጎንደር አስተዳደር አንዳቤት ወረዳ  ስራ ፍለጋ ወደ ባህርዳር ከተማ ቢያመራም፤ በየማስታወቂያ ሰሌዳው የሚለጠፉ ጥቂት የስራ ቅጥር ማስታወቂያዎች ለእንደሱ አይነት ጀማሪ መሀንዲሶች ሳይሆን የስራ ልምድ ላላቸው ነበር።
« በአብዛኛው የስራ ቅጥር ማስታወቂያ የሚወጣው ልምድ ላላቸው ነው። «ፍሬሽ» ወይም ልምድ ለሌለው፣ ከአሁን ቀደም ስራ ላልጀመረው  የወጣ አይደለም። ለሙያው የስራ ልምድ ያለው ነው የሚሉት። በአሁኑ ሰዓት በእኔ ብቻ አይደለም። ከሀገሪቱ ሁኔታ አንፃር በብዛት ነው የስራ አጥነት ችግር ያለው። ተመርቆ ስራ ማጣት የብዙዎች ችግር ነው። «በተለይ በኢንጂነሪንግ» ዘርፍ የተመረቀ ተማሪ 90 በመቶ በላይ ስራ ፍለጋ ላይ ነው ያለው። ያለ ስራ ተቀምጦ ነው ያለው። የሚወጡትም «ፊክስድ»ና ጥቂት ናቸው።ያንን ተስፋ ስናደርግ የስራ ልምድ ይጠየቃል። ስለዚህ ዜሮ አመት የስራ ልምድ ያለው ተማሪ የመሳተፍ እድሉ የሞተ ነው። በአሁኑ ሰዓት ብዙው ተማሪ ተስፋ ቁርጡን ያለው።»ብሏል ወጣት ይኄይስ።
እናም ያለ አባት ጥሪታቸውን አሟጠው ያስተማሩትን የድሃ እናቱን ውለታ መክፈል ሲገባው እንደገና ተመልሶ የእናቱን ዕጅ ማየቱ ዕረፍት ስለነሳው ፤ከሙያው ውጭም  ቢሆን  በማንኛውም ስራ ለመሰማራት ወሰነ።ያም ቢሆን  የሚሳካ አልሆነም።በመጨረሻ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት  ያገኘው ክፍት የስራ ቦታ ጫማ መጥረግ ብቻ ነበር።ከዚያም ለስራ መፈለጊያ ከወላጅ እናቱ ይዞት የመጣው ጥቂት ገንዘብ ከማለቁ በፊት የጫማ ቡርሽና ቀለም ገዝቶ በባህርዳር ከተማ የጫማ መጥረግ  ስራዉን ጀመረ።
«የጀመርኩት  ጥር አካባቢ ነው። ያሰብኩት እንግዲህ መቼም ሰው ተምሮ የቤተሰብን ዕጅ ማየት ይከብዳል። ደካማ እናት ነው ያለችኝ ።እስከመጨረሻ ድረስ አስተምራኛለች። ከዚያ  በኋላ የደካማ እናቴን ያለ ስራ ተመልሸ ማየት እሷን መለመን «ሼም»ስለያዘኝ ከብዶኝ ነው ይህንን ስራ የጀመርኩት።ለማፈላለጊያ ቢሆነኝ ብዬ ነው።ይደብራቸዋል ብዬ ከቤተሰብ ርቄ ተደብቄ ነው የምሰራው።እና ስለ ስራው እውቅና የላቸውም።እራሴ ነኝ ተሰምቶኝ የጀመርኩት።ቤተሰቦቼ ምን እንደምሰራ አያውቁም።»ሲል ነበር የተናገረው።
ይሄይስ እንደሚለው ተወልዶ ባደገባት ጉልቶይበይ የገጠር ቀበሌ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ  በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጃራ ገዶ ወደ ተባለ ቦታ ስንቅ ቋጥሮና በእግሩ ተመላልሶ ነበር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው።በ2007 የትምህርት ዘመን ታዲያ ጥረቱ ሰምሮ ፤የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ማጠቃለያ ፈተናን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ የከፍተኛ ተቋም ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ አመራ። በዩነቨርሲቲው የአምስት አመታት ቆይታው ቀላል ባይሆንም ከተመረቀ በኋላ ያለውን ተስፋ እያሰበ በርትቶ በመስራት በጥሩ ውጤት በ2011 ዓ/ም የመጀመሪያ ዲግሪውን በውሃ ምህንድስና ያዘ።ወጣቱ የውሃ ምህንድስናን የመረጠበትም ምክንያት ነበረው።
«ጅግጅጋ ዩንቨርስቲ ስሄድ በመጀመሪያ የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ተብሎ ነበር ምርጫ የሚሰጠው። ከዛ በኋላ «ጀነራል» ትምህርት ወሰድን።የመጀመርያ  ትምህርት ከወሰድን በኋላ  ውጤታችንም ሁለተኛ  ሴምስተር ላይ የመጀመሪያ ውጤታችን ታይቶ ከዛ በኋላ ነው ምርጫ ያደርግን ማለት ነው። የውኃ ምህንድስናን የመረጥኩት ያው ዞሮዞሮ  ሀገራችን በውሃ ሀገራችን በተፈጥሮ ሃብት እንደምትታዋቅ ይታወቃል።ከዚያ አንፃር በሀገራችን ከዚህ በፊት የውሀ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ልምድ የለም። ወደፊት እቅድ እንዳለ ያው የታወቀ ነው። ይህንን የማዘመን« ሲስተም» ወደፊት ይፈጥራል በሚል ነው ትምህርቱን  የመረጥኩት ።»ብሏል።
ይሄይስ፤ለወጣቱ የስራ አጥነት ችግር  የሀገሪቱ የፖለቲካ አካሄድ አንዱ መንስኤ ነው ብሎ ያምናል።
«በተለይ ከፍተኛ ችግር ገጥሞት ያለ በሀገራችን ሁሉም ተመራቂ እንደ ኢትዮጵያዊነቱ በሀገራችን ህገ መንግስት መሰረት በማንኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት የመቀጠር ና በማንኛውም ቦታ የመስራት ዕድል እንዳለሁ ነው።  ባሁኑ ሰዓት ግን ይህንን ለማድረግ በጣም ከባድ ሆኗል። ያሉትም እራሱ ውሰደው ርቀው  የሚሰሩትም ለቀው ወደ ትውልድ ቦታቸው እየመጡ ነው።የብሄር ፖለቲካ የሚባለው ነገር አስቸጋሪ  ነው።የብሄር ፖለቲካ የሚባለው ነገር ካልተወገደ ለወደፊቱም በጣም አስቸጋሪ ነው። እንኳን ስራ ለመፈለግ ይቅርና ማለት ነው።»በማለት ገልጿል።
ለቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ፤ ከአራት እህትና ወንድሞቹ መካከል በትምህርቱ የገፋ እሱ ብቻ በመሆኑ ፤ታናናሾቹን የማስተማርና እናቱን የመርዳት ጉጉት ነበረው።
በሃያዎቹ አጋማሽ  ዕድሜ ላይ የሚገኘው ወጣት ይኄይስ ፤ጫማ ጠርጎ የሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ ለዕለት ጉርሱ ብትሆነውም የቤት ኪራይ መክፈል ግን አሁንም ያልተሻገረው ፈተና ነው።ያም ሆኖ ነገ የተሻለ  ይሆናል ብሎ ተስፋ ያደርጋል።

Äthiopien Bahirdar Covid19
ምስል DW/A. Mekonnen
Äthiopien Bahirdar | Yiheyis Chale, Ingenieuer als Schuhreiniger
ምስል privat

« ተስፋ የማደርገው ያሁኑ ሀገሪቱ ሁኔታ ተሻሽሎ ጥሩ ጊዜ ሊመጣ ይችላል የሚል የሚል ተስፋ አለኝ። በዚያን ጊዜ የመሳተፍ ዕድል ይኖረኛል ብዬ አስፋ አደርጋለሁ።ወደፊት በተማርኩበት ሙያ ልሰራ እችላለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ዞሮዞሮ ያለ ሙያ መስራት ውጤት  ስለማያመጣ በሙያዬ ሀገሬን የማገልገል ፍላጎትና ምኞት አለኝ።»

እስከዚያ  ድረስ ግን የችግር ጊዜን ለማለፍ የተገኘውን ስራ መስራትን  ወጣቶች ሊማሩ ይገባል ባይ ነው።«ማንኛውም ሰው ተመርቆ ከወጣ በኋላ የቤተሰብ እጅ ማየት የለበትም። ምክንያቱም «ሳይኮሎጂን» ይጎዳል። ቤተሰብም የሚጠብቀው ልጅ ተመርቆ ወደ ስራ ይገባል ብሎ ነው የሚያስብ።ግን ደግሞ ቶሎ ሊሳካ ስለማይችል በማንኛውም የስራ ዘርፍ መስራት።የስራ ትንሽ ትልቅ የለውም የገቢ መጠን ይለያይ  እንጂ። እና በማንኛውም ስራ ተሰማርተው ሳይንቁ ተሰማርተው ማንኛውም ተመራቂ አካል ትንሽ ትልቅ ሳይል ስራዉን ይቀጥል ነው የኔ አስተያየት።»

ከግማሽ በላይ ህዝቧ ወጣት የሆኑባት ኢትዮጵያ በመጭው ግንቦት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነች።መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሀገሪቱ ልክ እንደ ይኄይስ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ስራ ማግኘት ያልቻሉ ወጣቶች በርካቶች ናቸው። እናም የፖለቲካ  ሰዎች ስለምርጫ ሲያስቡ የነዚህን ወጣቶች ችግር መፍታት ልብ ሊሉት የሚገባ ጉዳይ ይመስላል።

ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ