1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጦርነት በተማሪዎች ላይ ያሳደረዉ ጫና

ማክሰኞ፣ መስከረም 17 2015

'ፓይለት' ወይም 'አውሮፕላን አብራሪ' መሆን እፈልጋለሁ ያለን የ7 ዓመቱ ህፃን ናኦድ አረጋይ፣ በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ውጭ ከሆኑ 2 ነጥብ 3 ሚልዮን የትግራይ ተማሪዎች መካከል ነው። "ለመማር፣ የጀመርኩት ለመቀጠል እፈልጋለሁ። እንደድሮው ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ነው የምሻው። መንግስት ትምህርት ያስጀምረን"

https://p.dw.com/p/4HQ2S
Äthiopien | Schüler in der Tigray-Region
ምስል Million Hailesilassie/DW

ትግራይ ዉስጥ 88 በመቶ ትምህርት ቤቶች ተጎድተዋል

 

ትግራይ ዉስጥ ጦርነት ባሳደረዉ ተፅዕኖ ምክንያት በዘንድሮዉ የትምሕርት ዘመን ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚበልጡ የክልሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸዉ ተነገረ።የክልሉ ትምሕርት ቢሮ፣ ተማሪዎች፣እና አስተማሪዎች እንደሚሉት ጦርነቱ የተማሪዎችን የመማር ዕድል እያደናቀፈ፣የወደፊት ተስፋና ሕልማቸዉንም እያከሸፈ ነዉ።ባለፈው ዓመት በከፊል እና በተወሰነ አካባቢ ተጀምሮ የነበረዉ ትምህርት በቅርቡ ጦርነቱ  በማገርሸቱ ተቋርጧል።

በ2012 ዓመተምህረት በኮረና ቫይረስ ወረርሺኝ ስጋት ምክንያት በትግራይ የተቋረጠ የትምህርት ሂደት፣ ጦርነቱ ተከትሎበት ላለፊት 3 የትምህርት ዘመናት የትግራይ ህፃናት፣ ታዲጊዎችና ወጣቶች ወደ መደበኛ የትምህርት ሂደት ሊመለሱ አልቻሉም። እንደ ትግራይ ትምህርት ቢሮ መረጃ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በትግራይ በተለያዩ ደረጃዎች ትምህርት ሊጀመሩ ይጠበቁ የነበሩ 2 ነጥብ 3 ሚልዮን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ አልተመለሱም። ባለፈው ዓመት በከፊል እና በተወሰነ አካባቢ ተጀምሮ የነበረ የቅድመ መደበኛ እና ከአንደኛ አስከ ስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ትምህርት ደግሞ ጦርነቱ ዳግም ማገርሸቱ ተከትሎ ሊቀጥል እንዳልተቻለ ተገልጿል። የትግራይ ትምህርት ቢሮ ኮምኒኬሽን ሐላፊ አቶ ዳኘው አይጠገብ ለዶቼቬለ እንዳሉት "ጦርነቱ የትምህርት ሂደቱ ማስተጓጎሉ ተከትሎ ተማሪዎች በተገቢው ዕድሜያቸው ሊያገኙት ይገባ የነበረ ትምህርት ሳያገኙ እየቀሩ ነው፣ ሕልማቸው እየተደናቀፈ ነው" ይላሉ። 
በመቐለ ያነጋገርናት ምልእተ ገብረዮሐንስ በ2012 ዓመተምህረት በትግራይ ትምህርት ሲቋረጥ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። አሁን የ17 ዓመት ታዳጊ የሆነችው ምልእተ ለሶስት ተከታታይ ዓመታ ከትምህርት እንደራቀች ትገልፃለች። ምልእተ እንደ ዘንድሮ ሳይሆን "ክረምት ተለያይተን፣ መስከረም ዳግም ትምህርት ሲጀምር የተለየ ስሜት የሚፈጥር ነበር። በአዲስ ዩኒፎርም፣ ደብተርና የትምህርት መንፈስ ወደ ትምህርት ቤታችን እንመለስ ነበር። አሁን ይሄ የለም" በማለት ቁጭቷ ትገልጻለች። "አሁን 12 ክፍል እሆን ነበረ" የምትለዋ ምልእተ፥ ያለፈው አብቅቶ፣ ሰላም ወርዶ ዳግም ትምህርቷ የምትቀጥልበት ቀን ትናፍቃለች።
'ፓይለት' ወይም 'አውሮፕላን አብራሪ' መሆን እፈልጋለሁ ያለን የ7 ዓመቱ ህፃን ናኦድ አረጋይ፣ በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ውጭ ከሆኑ 2 ነጥብ 3 ሚልዮን የትግራይ ተማሪዎች መካከል ነው። "ለመማር፣ የጀመርኩት ለመቀጠል እፈልጋለሁ። እንደድሮው ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ነው የምሻው። መንግስት ትምህርት ያስጀምረን" በማለት ናኦድ በህፃን አንደበቱ ጥሪውን ያቀርባል። 
መቋጫ ባለገኘው ጦርነት ምክንያት በትግራይ መደበኛ የትምህርት ሂደት ከተደናቀፈ ሶስት ዓመት ሆንዋል። በክልሉ ካለው ማሕበራዊ ችግር በተጨማሪ በትምህርት መሰረተ ልማቱ ላይም በደረሰ ውድመት ምክንያት በትግራይ ትምህርት ማስቀጠል ፈተና መሆኑ ይገለፃል። በጦርነቱ ምክንያት 88 በመቶ በትግራይ የነበሩ ትምህርት ቤቶች በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ውድመት እንደደረሰባቸው የትግራይ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

ሚሊዮን ኃይለ ስላሴ 

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ