1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥንታዊው የኡጋንዳ ዩንቨርስቲ ቃጠሎ

ቅዳሜ፣ መስከረም 16 2013

በአፍሪቃ እጅግ ጥንታዊ ከሚባሉት ዩንቨርሲቲዎች አንዱ  የሆነው የኡጋንዳው ማካሬሬ  ዩንቨርሲቲ ያለፈው ዕሁድ የእሳት ቃጠሎ ደርሶበታል።በቃጠሎው በዩንቨርሲቲው ዋና ህንፃ የፋይናንስ መምሪና  የመዝገብ ቤቱ የወደመ ሲሆን  በ1940ውቹ በዩኒቨርሲቲው ግቢ  የቆመው «አይቮሪ ታወር» ተብሎ የሚጠራዉ  ታዋቂ ማማም አብሮ በቃጠሎው ተጎድቷል።

https://p.dw.com/p/3j2bb
Uganda Kampala | Makerere Fire | Emmanuel Lugeba
ምስል Emmanuel Lugeba/DW

ጥንታዊው የዑጋንዳ ዩኒቨርሲቲ ተመልሶ ይጠገን ይኾን ?

ጥንታዊው የኡጋንዳ ዩንቨርስቲ ቃጠሎ

በአፍሪቃ እጅግ ጥንታዊ ከሚባሉት ዩንቨርሲቲዎች አንዱ  የሆነው የኡጋንዳው ማካሬሬ  ዩንቨርሲቲ ያለፈው ዕሁድ የእሳት ቃጠሎ ደርሶበታል።በቃጠሎው በዩንቨርሲቲው ዋና ህንፃ የፋይናንስ መምሪና  የመዝገብ ቤቱ የወደመ ሲሆን  በ1940ውቹ በዩኒቨርሲቲው ግቢ  የቆመው «አይቮሪ ታወር» ተብሎ የሚጠራዉ  ታዋቂ ማማም አብሮ በቃጠሎው ተጎድቷል። የዚህ ታዋቂ ዩንቨርሲቲ ቃጠሎ ብዙዎችን አሳዝኗል። የቃጠሎው መነሻ እንዲጣራና በፍጥነት እንዲገነባ የሚጠይቁም ብዙዎች ናቸው።የዚሁ ዩንቨርስቲ ተማሪ የሆነው መረዲ አንካንኩንዳ ከነዚህ መካከል አንዱ ነው።

«እስካሁን ጥሩ ስሜት አይሰማኝም ። ይህ  የተከበረ ህንፃ በእሳት መጋየቱ ጥሩ አይደለም።በእርግጠኝነት የሚመለከታቸውን ሁሉ የምጠይቀው  የቃጠሎውን መነሻ  ለማጣራት በሚደረገው ምርመራ ከፍተኛ ጥረት  እንዲያደርጉ ነው።በተጨማሪም ህንፃውን  በፍጥነት መልሶ ለመገንባት ጠንክረው እንዲሰሩም እጠይቃለሁ።»

በዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ የሚገኘው የመከሬሬ ዩንቨርሲቲ 79 ዓመታትን  ያስቆጠረ አንጋፋ ዩንቨርሲቲ ሲሆን ፤ለብዙ ዩጋንዳዉያን  ተማሪዎች የመማሪያ ቦታ ብቻ ሳይሆን እንደ ቅርስም ኩራት ነው። 

«የመጀመሪያ ተምሳሌት ነበር። የሆነ ወቅት መከሬሬ ዩንቨርሲቲ ነበርኩ ወይም በአንድ ወቅት መከሬሬ ዩንቨርሲቲን ጎብኝቻለሁ ብለህ  ለሰው የምታሳየው።»

የዚህ ታሪካዊ  ዩንቨርሲቲ መውደም ታዲያ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን ብዙ ዩጋንዳውያንንም አሳዝኗል።ከጎርጎሪያኑ  1970 ዓ/ም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲውን የሚያውቁት  የታሪክ ተመራማሪው ሲሞን ሳጋላ ሙሊንድዋ ስለ ህንፃው ሲገልፁ «ያ ህንፃ  ያለ ምንም ቃል ታሪክ ይናገራል» ይላሉ።ስለሆነም ይህ የተለዬ የሥነ-ህንፃ ውበት የሚንፀባረቅበት ዩኒቨርሲቲ በእሳት ሲጋይ  በእንባ መመልከታቸውን ገልፀዋል። በዩጋንዳ ፓርላማ የተቃዋሚ መሪ የሆኑት ቤቲ አዮልም ተመሳሳይ ስሜት አላቸው።

 «ታውቃለህ ስላልተጣራ ወሬ መናገር  አልችልም።ማለት የምችለው ምርመራ እናድርግ ማለት ብቻ ነው።በሌላ በኩል እኛ በምናለቅስበት ጊዜ መንግስት ቢያንስ  ህንፃውን መልሶ ለመገንባት መዘጋጀት አለበት።ምክንያቱም ኩራታችን ነው።»

ይህንን ተከትሎ የዩንቨርሲቲው ምክትል ሃላፊ በርናባስ ናዋንግዌ ትናንት በሰጡት መግለጫ ዩንቨርሲቲውን መልሶ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።  በዩኒቨርሲቲ የወደሙት አብዛኛው  ሰነዶችም በዲጂታል ፋይል ሆነው የተቀመጡ  በመሆናቸው  መልሶ ማግኘት እንደሚቻል ሀላፊው ተናግረዋል። እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ በ 20 ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ የሕንፃ ጥበብ አምሳያ የተገነባው ይህ ታሪካዊ ዩኒቨርሲቲ፤ ዱሮ ወደ በነበረበት ሁኔታ መመለሱን ብዙዎች ይጠራጠራሉ።

በጎርጎሪያኑ  1922 ዓ/ም በቴክኒክና ሙያ  ትምህርት የተጀመረው ማኬሬሬ ዩንቨርሲቲ በአፍሪቃ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው  ሲሆን በ2018 ብቻ 14ሺህ ተማሪዎችን አስመርቋል።በየዓመቱም ከ35,000 በላይ ተማሪዎችን ይቀበላል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በርካታ ታዋቂ አፍሪቃውያንን ያፈራ ሲሆን ፤ከነዚህም መካከል የታንዛኒያው የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ ፣የቀድሞው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ኬኒያዊው  ደራሲ ንጉጊዋ ቲዮንጎ እንዲሁም የወቅቱ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዋና ተቀናቃኝ የሆኑት ቦቢ ዋይኒ ይገኙበታል። 

ጸሐይ ጫኔ

ታምራት ዲንሳ