1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥር 16 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 16 2014

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግስጋሴውን ቀጥሏል። በመልስ ጨዋታው ካሸነፈ ወደ መጨረሻው የጥሎ ማለፍ ፍጻሜ ያልፋል። በአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ ያልተጠበቁ ክስተቶች ተመዝግበዋል። ውድድሩ ቀጥሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።

https://p.dw.com/p/4604r
FBL-AFR-AFCON-2021-2022-MLI-MTN
ምስል AFP via Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግስጋሴውን ቀጥሏል። በመልስ ጨዋታው ካሸነፈ ወደ መጨረሻው የጥሎ ማለፍ ፍጻሜ ያልፋል። በአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ ያልተጠበቁ ክስተቶች ተመዝግበዋል። በአፍሪቃ እግር ኳስ ቦታ ያልነበራቸው ቡድኖች አንጋፋዎቹን ጉድ አድርገዋል። ውድድሩ ቀጥሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። በርካታ ታዳሚያን የተሳተፉበት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ትናንት ተከናውኗል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የማንቸስተር ሲቲ ነጥብ መጣል የሊቨርፑል ተስፋ እንዲያንሰራራ አድርጓል። በጀርመን ቡድንደስ ሊጋ መሪው ባየርን ሙይሽንሽን በሰፋ የግብ ልዩነት ማሸነፉን ቀጥሏል።  

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ የ4ኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታውን ትናንት ጥር 15 ቀን፣ 2014 ዓ.ም አከናውኗል። ቡድኑ ዛንዚባር አማን ስታዲየም ውስጥ ባከናወነው ግጥሚያ በጠበበ የግብ ልዩነት 1 ለ0 ተሸንፏል። ለታንዛኒያ የማሸነፊያዋን ግብ በ64ኛው ደቂቃ ክሪሳ ጆን ባራ አስቆጥራለች። 

FIFA Logo
ምስል APTN

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል የሚመራው ቡድን ባለፉት ጊዜያት ባሳየው ድንቅ ጨዋታ እና ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድል ይኖረዋል የሚል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን የፊታችን አርብ አንድ ሳምንት በሜዳው ያከናውናል።

በኮስታሪካ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የ2022 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ቡድን የተሸነፈው በታንዛኒያ ብቻ ነው። ባለፉት ግጥሚያዎች፦ የሩዋንዳ ቡድንን በሜዳውም ከሜዳው ውጪም 4 ለ0፤ በድምሩ 8 ለ0 አደባይቶታል። ቦትስዋናን በሜዳዋ 3 ለ1 አሸንፎ፤ በሀገር ቤት በሜዳው ባደረገው ግጥሚያ ደግሞ 5 ለ1፤ በድምሩ 8 ለ1 አንኮታኩቷል። በቀጣይ ጨዋታ ታንዛኒያን ካሸነፈ ወደ መጨረሻው እና አምስተኛ ዙር የጥሎ ማለፍ ውድድር ይገባል። በመጨረሻው ዙር የሚሳተፉ ቡድኖች አራት ብቻ ናቸው። ከአራቱ ሁለቱ ለዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።

የፌኔክ ቀበሮዎቹን ዘንድሮ ምን ነካቸው?

በአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር (AFCON) በርካታ ያልተጠበቁ ክስተቶች ታይተዋል። የፌኔክ ቀበሮዎች የሚል ስያሜ ያለው የአልጀሪያ ቡድን ያለፈውን ዋንጫ በእጁ ሲያስገባ ኃያልነቱን አስመስክሮ ነበር። በያኔው ውድድር በምድቡ አንዳችም ግብ አልተቆጠረበትም። በጥሎ ማለፉ ደግሞ የግብ ክልል መረቡ የተደፈረው ለሁለት ጊዜያት ብቻ ነው። በፍጻሜውም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1990 ከተቀዳጁት የዋንጫ ድል በኋላ ሁለተኛቸው በሆነው ፉክክር  ሴኔጋልን 1 ለ0 ረትተው ዋንጫውን ወደ አልጀርስ ይዘው ተፈትለከዋል። ዘንድሮ በሦስተኛ ዓመታቸው ግን ከአፍሪቃ ዋንጫ የምድብ ግጥሚያ አንድም ቡድን ማሸነፍ ተስኗቸው ነው የተሰናበቱት። የፌኔክ ቀበሮዎቹን ምን ነካቸው?

AFCON Algerien vs Elfenbeinküste
ምስል Thaier Al-Sudani/REUTERS

የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ካሜሩን ባዘጋጀችው የአፍሪቃ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ብቅ ያለው በፊፋ የአረብ ዋንጫ ውድድር ካታር ውስጥ ድል የመቀዳጀቱ ዝና ሳይከስም ገና በሳምንቱ በልዩ ሞገስ ነበር። ከአራት ዓመታት አንስቶም ቡድኑ አንዳችም ሳይሸነፍ በመዝለቅ ነበር ያውንዴ የገባው። ሌላው ቢቀር የዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ከመጀመሩ ከአንድ ሳምንት በፊት ይኸው ቡድን የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ውስጥ ጋናን ለወዳጅነት ገጥሞ 3 ለ0 ኩም አድርጎ ነበር የሸኘው። እናም የአልጄሪያ ቡድን ከመፈራቱ የተነሳ በምድብ ድልድሉ እንዳይደርሰው ያልፈራ ቡድን ነበር ማለት ይከብዳል። በካሜሩን የአፍሪቃ ዋንጫ ግን ዝነኛው እና ብርቱው የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ እንኳን ማለፍ ተስኖት ነው የተሰናበተው።  እናስ የፌኔክ ቀበሮዎቹን ዘንድሮ ምን ነካቸው?    

ያለፈው ዋንጫ ባለድሉ የአልጄሪያ ቡድን ከኤኳቶሪያል ጊኒ ቡድን ጋር በምድቡ ሁለተኛ ግጥሚያውን ሲያደርግ በሰፋ የግብ ልዩነት ሁሉ ያሸንፋል ተብሎ ተገምቶ ነበር። በፊፋ መስፈርት 114ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውና ንዛላንጋ ናሲዮናል የሚሰኘው የኤኳቶሪያል ጊኒ ቡድን ግን አስፈሪውን ቡድን 1 ለ0 ድል አድርጎ ጉድ አድርጎታል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ቡድን አጥቂ ሪያድ ማኅሬዝን የመሰሉ ተጨዋቾችን ያካተተው የአልጄሪያ ቡድን በስተመጨረሻ አንዲት ብቸኛ ግብ አስቆጥሮ ነው ከአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር የተሰናበተው።

Fußball | Africa Cup of Nations | Algerien - Äquatorialguinea
ምስል Charly Triballeau/AFP/Getty Images

አልጄሪያ፦ ሪያድ ማኅሬዝ ፍጹም ቅጣት ምት በሳተበት በምድቡ ሦስተኛ እና የመጨረሻ ግጥሚያው ሐሙስ ዕለት በአይቮሪ ኮስት ቡድን የ3 ለ1 ብርቱ ሽንፈት የተቀጣው።

የንዑሷ ኮሞሮስ ያልታሰበ እድል

እነ አልጀሪያ እና ጋና በተሰናበቱበት የአፍሪቃ ዋንጫ 850,000 ነዋሪ ያላት ትንሿ ኮሞሮስ በአንጻሩ ባልተጠበቀ መልኩ ዕድል ገጥሟታል። ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ በአፍሪቃ ዋንጫ ላይ ብቅ ማለት የቻለችው ንዑሷ ኮሞሮስ ወደ 16 ቡድኖች የጥሎ ማለፍ ምድብ አልፋለች። ኮሞሮሶች ምንም እንኳን 2 የግብ እዳ ቢኖራቸውም የሌሎች ግጥሚያ ውጤት ግን የእድል በራቸውን ወለል አድርጎ ከፍቷል። በምድቡ አይቮሪ ኮስት አልጀሪያን 3 ለ1 ማሸነፏ ለኮሞሮስ ተዓምር ነው የኾነላት። ኮሞሮስ በምድቧ በጋቡን 1 ለ0 እንዲሁም በሞሮኮ 2 ለ0 ብትሸነፍም፤ ጥቋቁር ከዋክብትን ግን 3 ለ2 ነበር ያሸነፈችው። በ25ኛው ደቂቃ ላይ አንድሪው አዩን በቀይ ካርድ ያጣችው ጋና በኮሞሮስ የመሸነፍን ያህል ብርቱ ቅጣት ገጥሟት ዐያውቅም። ኮሞሮስ ሦስተኛ ጥሩ ቡድን በመሆን ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች። ዛሬ ማታ ግን ዳግም እድል ይገጥማታል ማለት እጅግ ይከብዳል። ምክንያቱም ኮሞሮስ ዛሬ ማታ የምትገጥመው አዘጋጇ ካሜሩንን ነውና።

Africa Cup of Nations Ghana vs Komoren
ምስል Daniel Beloumou Olomo/Getty Images/AFP

የኮሞሮስ እና ካሜሩን የምሽቱ ጨዋታ ከጊኒ እና ጋምቢያ ግጥሚያ ቀጥሎ ነው።  ነገ ምሽት ደግሞ ሴኔጋል ከኬፕቬርዴ የሚያደርጉት ጨዋታ ይቀድማል። ከዚያም ምሽቱን የሞሮኮ እና ማላዊ ፍልሚያ ይከተላል። የረቡዕ ዕለት ጨዋታዎች አይቮሪኮስት ከግብጽ በሚያደርጉት ጀምሮ ነው ምሽቱን በኤኳቶሪያል ጊኒ እና ማሊ የሚጠናቀቀው። ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ወደ ሩብ ፍጻሜ ያለፉት ቡርኪናፋሶ እና ቱኒዝያ ይጫወታሉ። በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ እኩል የተለያየችው ቡርኪና ፋሶ ጋቦንን ልብ ሰቃይ በሆነ የፍፁም ቅጣት ምት መለያ 7 ለ6 አሸንፋ፤ ቱኒዝያ ናይጀሪያን 1 ለ0 ድል አድርጋ ነው ወደ ሩብ ፍጻሜው ያለፉት።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ቸልሲ ቶትንሀምን 2 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 47 አድርሷል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ ከቀረው ሊቨርፑል ቀጥሎም በደረጃው ሦስተኛ ላይ ይገኛል። 48 ነጥብ በመሰብሰብ የሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ትናንት ክሪስታል ፓላስን 3 ለ1 ድል አድርጓል። በትናንቱ ጨዋታ ለሊቨርፑል ቀዳሚዋን ግብ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ተከላካዩ ቪርጂል ቫን ጂክ ነው። አሌክስ ኦክስሌድ-ቻምበርላይን በ32 እንዲሁም ፋቢንሆ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ግቦችን አስቆጥረዋል። ክሪስታል ፓላስ ብቸኛዋን ግብ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘው በኦድሶኔ ኤዱዋርድ ነው።

RB Leipzig - Manchester City
ምስል Jan Woitas/dpa/picture alliance

ትናንት በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች፦ አርሰናል በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ 20ኛ ላይ ከሚገኘው በርንሌይ ጋር ተጋጥሞ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ላይስተር ሲቲ እና ብራይተን አንድ እኩል ተለያይተዋል። ቅዳሜ ዕለት መሪው ማንቸስተር ሲቲ ከሳውዝሀምፕተን ጋር ተጋጥሞ አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። አጋጣሚው ለተከታዩ ሊቨርፑል እጅግ አስደሳች ነው። ሊቨርፑል በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ በቀጣዩ ጨዋታ ላይስተር ሲቲን ካሸነፈ 57 ነጥብ ካለው ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ልዩነቱ የ6 ነጥብ ብቻ ይሆናል። ዎልቨርሀምፕተን ብሬንትፎርድን 2 ለ1 አሸንፏል። በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ላይ የሚገገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ እንደ ሊቨርፑል ሁሉ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 38 ነጥብ ሰብስቧል። ቅዳሜ ዕለት ዌስትሀም ዩናይትድን 1 ለ0 ረትቷል።  

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታዎች፦ መሪው ባየርን ሙይንሽን እንደለመደው በሰፊ የግብ ልዩነት ተጋጣሚውን ድል አድርጓል። ነጥቡንም 49 አድርሷል። በትናንቱ ግጥሚያ ባየርን ሙይንሽን ኼርታ ቤርሊንን ያሸነፈው 4 ለ1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ነው። ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት ሆፈንሃይምን ገጥሞ 3 ለ2 በማሸነፉ ነጥቡን ወደ 43 ከፍ አድርጓል።  በ35 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባዬርን ሌቨርኩሰን በቅዳሜ ግጥሚያው አውግስቡርግን 5 ለ1 ነው ድባቅ የመታው። ትናንት ላይፕትሲሽ ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 ማሸነፍ ችሏል። ኾኖም በ31 ነጥቡ የ6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከበላዩ በ2 ነጥብ የሚበልጠው ፍራይቡርግ እና በ3 ነጥብ የሚርቀው ዑኒዮን ቤርሊን ይገኛሉ።

Fußball Bundesliga | VfL Bochum - 1. FC Köln | Tor (1:2)
ምስል Maik Hölter/Team 2/imago images

ዑኒዬን ቤርሊን ቅዳሜ ዕለት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ1 ድል አድርጎ ቡድኑ የገባበትን ቀውስ አባብሷል። ቦኹም ከኮሎኝ ሁለት እኩል ተለያይተዋል። ወደ ወራጅ ቃጣናው ላለመሽቆልቆል የተፋለመው አርሚኒያ ቢሌፌልድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ተፎካካሪነት ያለመው አይንትራክኅት ፍራንክፉርትን በገዛ ሜዳው ጉድ አድርጎታል። በሚገርም ሁኔታ በማጥቃት የተጫወቱት አርሚኒያ ቢሌፌልዶች የማታ ማታ 2 ለ0 ድል አድርገው ነጥባቸውን 21 አድርሰዋል። ተመሳሳይ ነጥብ ያለው ቮልፍስቡርግ በግብ ክፍያ ተበልጦ ወራጅ ቀጠናው ጠርዝ ላይ ይገኛል። ከስሩ አውግስቡርግ፣ ሽቱትጋርት እና ግሮይተር ፊዩርትስ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ተደርድረዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ

Äthiopien | Great Run 2022
ምስል Seyoum Getu/DW

አዲስ አበባ መስቀል አደባባይን መነሻ እና መድረሻው አድርጎ ትናንት በተካሄደው 21ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው በከፍተኛ የአየር ንብረት የ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ፈጣኑን የተባለውን ሰአት በማስመዝገብ ለድል በቅታለች። በሴቶች ፉክክር አትሌት ያለምዘርፍ ያሸነፈችው 30 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ በመሮጥ ነው።  በወንዶች ውድድር አትሌት ገመቹ ዲዳ አሸናፊ ኾኗል። አትሌት ጌታነህ ሞላ እና አትሌት ቦኪ ድሪባ 2ኛ እና 3ኛ በመኾን ተከታትለው ገብተዋል። ከጎረቤት አገራት የመጡ አትሌቶች ጭምር በተሳተፉበት ውድድር በሴቶች አትሌት ግርማዊት ገ/እግዚአብሔር 2ኛ እንዲሁም መልክናት ውዱ 3ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ