1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠጅና አጣጣሉ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 27 2014

የጠጅን ቢጫ ቀለም ለማምጣት አንዳንዶች እርድን ሲጠቀሙ አንዳንዶች ደግሞ ስኳርን አመስ አመስ በማድረግ ይጠቀማሉ። አቶ ካሱ ግን የጌሾ እንጫቱን በብረት ምጣድ በማቁላላት ቢሰራ ትክክለኛ ቀለሙን ከማምጣቱም በላይ የጠጁን ጣእምና ጥንካሬ ላይም ወሳኝ ነው ብለውናል።

https://p.dw.com/p/4AmPn
Äthiopien | Lokales Bier Tej | Bierbrauer Kasu Seboka
ምስል Privat

በአገራችን የክብር ባሕላዊ መጠጥ አንዱ ጠጅ ነው።

                                                                                                                                                                                                                                

ለሰርግ ለአመት በአልና ለመሳሰሉት ዝግጅቶች ከሚቀርቡ ባሕላዊ መጠጦች አንዱ ጠጅ ነው። ጠጅ እንዴት ይሰራል? ጠጅ ቀናተኛ ነው ይባላል ለምን? እና በጠጅ ጠመቃ ሊወሰዱ ስለሚገባችው ጥንቃቄዎች መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን ውድ የባሕል መድረክ ታዳሚዎች።  በአገራችን የክብር ተብለው ከሚዘወተሩ ባሕላዊ መጠጦች አንዱ ጠጅ ነው። ጠጅ እንደየደረጃው ለስለስ ያለ መካከለኛና ደረቅ ተብሎ የሚለይ ሲሁን ምንም አይነት  ጌሾ ካልገባበት ደግሞ ብርዝ ይሆናል። አቶ ካሱ ሰቦቃ የምግብ ዝግጅት ባለሙያ ሲሁኑ አሁን ደግሞ ጠጅን ጥለው እስከ ጎረቤት ሃገራት መላክ እንደቻሉ ገልጸውልናል። በዛሬው ዝግጅታችን ከሳቸው ጋ ቆይታ አድርገናል።

Äthiopien | Lokales Bier Tej | Bierbrauer Kasu Seboka
ምስል Privat

በውሃ የተበረዘው ማር ከጌሾ ጋ ተቀላቅሎ እንደየዝግጅታችን የጊዜ ሰሌዳና ጠጁ እንዲሆንልን እንደምንፈልገው ልስላሴ ወይም ደረቅነት በመጀመሪያው በርሜል ወይም ባልዲ ለተወሰኑ ቀናት  ከቆየ ቦኋላ ወደሌላ አዲስ በወይራ በጌሾ አንዳንዴም በበርበሬ ወደታጠነ በርሜል ይገለበጣል። 

ጠጅ በሚጣልበት ጊዜ የጌሾ ቅጠል እንጨቱ በብርዝ የሚቀቀልበት ሁኔታ አለ። እንደየአካባቢው ልማድ ለብ ባለ ውሃ አሸት አሸት ተደርጎ የሚገባበት ሁኔታም አለ። 

የጠጅን ቢጫ ቀለም ለማምጣት አንዳንዶች እርድን ሲጠቀሙ አንዳንዶች ደግሞ ስኳርን አመስ አመስ በማድረግ ይጠቀማሉ። አቶ ካሱ ግን የጌሾ እንጫቱን በብረት ምጣድ በማቁላላት ቢሰራ ትክክለኛ ቀለሙን ከማምጣቱም በላይ የጠጁን ጣእምና ጥንካሬ ላይም ወሳኝ ነው ብለውናል።

ጠጅ ከሌሎች ባሕላዊ መጠጦች በተለየ መልኩ በሂደቱ ልዩ ጥንቃቄን ይፈልጋል። ጠጅ በተጣለበት ቤት አጠገቡ እጣን ወይም ሰንደል ቢጨስ ወደ ቤቱ ሽቶ ተቀብተን ብንገባ ልፋታችን ከንቱ ይሆናል።

Äthiopien | Lokales Bier Tej | Bierbrauer Kasu Seboka
ምስል Privat

 

ከጠመቃ የሚጀምረው የጠጅ ቅናት ሲጠጣም ቅናተኛ ነው እየተባለ ይነገርለታል። ጠጅን የሚያዘወትሩ አባቶች በተለምዶ ንጉሱ የማሩን ፈጣሪ አውራ ንብን ለማለት ነው ንጉሱ ወደ ሰውነት ሲገባ ከታች ጉዝጓዝ አንጥፉልኝ ከላይ ጥላ ያዙልኝ አይልም ይላሉ። ይህም ማለት ከጠጅ በፊትና ቦኋላ ምንም አይነት  ሌላ ባሕላዊም ይሁን ዘመናዊ መጠጥ መውሰድ አይፈልግም ይሉታል። አቶ ካሱም ይህን ይጋራሉ። ይህ ባሕላዊ መጠጥ በአላት ከማድመቅ በዘለለ ወደ ፋብሪካ ገብቶ ዳጎስ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ወደሚያድግበት ደረጃ አለምድረሱ እንደሚቆጫቸው ነግረውናል አቶ ካሱ።

 

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 

አዜብ ታደሰ