1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ የኢሕአዴግ ውኅደት ተቃዋሚዎች ላይ የሰላ ትችት ሰነዘሩ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 8 2012

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢሕአዴግን ለማዋሐድ የተጀመረውን ጥረት በተቃወሙ ወገኖች ላይ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ላለፉት 28 አመታት ኢትዮጵያን ያስተዳደረውን ግንባር ለማዋሐድ የተዘጋጀው ሰነድ ከተጠናቀቀ ከአንድ አመት ከስድስት ወር በላይ ቢሆነውም «ላለመበትን ስንለማመን ከርመናል» ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3RZcD
Äthiopien Addis Abeba | Premierminister Äthiopien Abiy Ahmed veröffentlich Buch zu seiner Ideologie
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ «የመደመር ፍልስፍና» የሚያብራራ መፅሀፋቸው የምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የኢሕአዴግን ውኅደት የተቃወሙ ወገኖችን በጠንካራ ቃላቶች እና አገላለጾች ተችተዋል። የኢህአዴግ ውህደት ውይይት አሁንም አለመጠናቀቁን ገልጸዋል። 

«የፓርቲ ውኅደት ጉዳይ አላለቀም። እኛ የመደመር ፍልስፍናን የምናምን ሰዎች በዴሞክራሲያዊ ውይይት ስለምናምን አንድ አመት ከስድስት ወር ሙሉ ተጠንቶ ያለቀ ሰነድ ጉዳይ ቢሆንም ላለመበትን ስንለማመን እና ስንወያይ ከርመናል። አሁንም ውይይቱ አልተቋጨም» ብለዋል ጠቅላይ ምኒስትሩ። የኢሕአዴግ ውኅደት «ኢትዮጵያን ከፌደራላዊ ሥርዓት ወደ አሃዳዊ ሥርዓት መመለስ ነው» የሚል ተቃውሞ መቅረቡን የጠቀሱት ጠቅላይ ምኒስትሩ በትግራይ፣ በአማራ እና በደቡብ ክልሎች የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ እየተዳደሩ ለበርካታ አመታት መቆየታቸውን ጠቅሰው ትችቱን አጣጥለዋል።

«ውይይቱ ሳይቋጭ አንዳንዶች ‘ይኸ የፓርቲ ውኅደት መጨፍለቅ ነው፤ ኢትዮጵያን ከፌደራላዊ ሥርዓት ወደ አሃዳዊ ሥርዓት መመለስ ነው ’ የሚል በእኛ ውስጥ ታስቦ የማያውቀውን መርዶ አረዱን። የፓርቲው አንድ መሆን ኢትዮጵያን የሚጨፈለቅ ከሆነ ኢትዮጵያ አልነበረችም፤ ተጨፍልቃለች ማለት ነው። ምክንያቱም ትግራይ ውስጥ ሕወሓት የሚባል ድርጅት እንጂ ኩናማ የራሱ ድርጅት የለውም። ኢሮብ የራሱ ድርጅት የለውም። ኢሮብ የራሱ ልዩ ወረዳ አለው፤ ኩናማ የራሱ ልዩ ወረዳ አለው። በሕወሓት ይተዳደራል፤ ነገር ግን የፌደራል ሥርዓት አልተጨፈለቀም» ሲሉ የሀሳቡን አቀንቃኞች ሞግተዋል።  

የጠቅላይ ምኒስትሩ የዛሬው ንግግር ከሕወሓት አመራሮች ጋር ያላቸው ግንኙነት የበለጠ መሻከሩን ያሳበቀ ሆኗል። የኢሕአዴግ መሥራች የሆነው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ «በውኅደት ስም፣ በፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ፣ አዲስ አሃዳዊ ድርጅት ሊመሰረት አይገባም» ብሎ ነበር። «የኢሕአዴግ ውኅደት ሊቆይ የሚገባው ጉዳይ ነው» ያለው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ኢሕአዴግን ለማዋሐድ የተጀመረው ጥረት «ከግንባሩ እምነትና መተዳደሪያ ደንብ ውጭ ነው» ሲል አቋሙን አንጸባርቋል።

Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ግን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት «አንድ የኤኮኖሚ እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር» ርዕይ እንዳለው በመጥቀስ የውኅደቱን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል። እርሳቸው በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት ኢሕአዴግ «እንኳን ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ራሱም አንድ መሆን ተስኖት ቆይቷል» ሲሉም ነቅፈዋል። የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በባለፈው ሳምንት መግለጫው ግንባሩ ከተዋሐደ «የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኢሕአዴግ የያዘውን ፕሮግራም መሰረት አድርገው የሰጡት አገርን የመምራት ስልጣን ያከትማል» ቢልም ጠቅላይ ምኒስትሩ ግን ውኅደትን በተመለከተ በኢሕአዴግ አራት አባል ድርጅቶች ተቀባይነት የሚያገኘው ሐሳብ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል። 

«በተሰጠው ዕድል መጠቀም ሳይችል ዕድል ሲነጠቅ በትውልድ ዕድል መቀለድ አይቻልም። ኢሕአዴግ እንዴት ይዋሃዳል? ምን ስም እና ግብር ይኖረዋል? የሚለውን እኔ አልወስንም። እኔ ዴሞክራት መሪ ስለሆንኩ ለውይይት ሐሳቤን አቀርባለሁ። የተሻለ ሐሳብ እና የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ብዙኃን ሐሳብ የሆነውን ግን በቅርቡ ለሕዝባችን እንገልፃለን።»

ጠቅላይ ምኒስትሩ በመጽሐፍ መልክ ያዘጋጁት የመደመር ፍልስፍና የሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን ጨምሮ «እያንዳንዱ ዜጋ ሀገሬን ልመራ እችላለሁ» ብሎ የሚዘጋጅባት፤ «ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር» የሚያስብ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል። ሕወሓት ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ግን በውህደት ስም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶችንም ህልውና የሚያጠፋ እንደሆነ አስጠንቅቆ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው እርሳቸው የሚያቀነቅኑትን መንገድ የሚቃወሙ አማራጭ ሐሳብ እንዲያቀርቡ በዛሬው ንግግራቸው ጠይቀዋል።

«መደመር ፍልስፍና ከሆነ እና ፓርቲው ከተዋሀደ ወደ እልቂት እንገባለን የሚለው ጉዳይ-እልቂትን ምን አመጣው? አንድ ፓርቲ መሆን እና መደመር የማያዋጣ ከሆነ ጀግና ሰው ውስኪውን አስቀምጦ መባዛት የሚል አማራጭ ሐሳብ ይዞ ይመጣል። ያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ መደመር እና መባዛትን ጎን ለጎን ያይና፤ መደመር አያስፈልገኝም ይላል። ሐሳብ እያለ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ምን ያገዳድለናል? እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚቀጥለው አማራጭ መገዳደል ነው የሚለው የ19ኛው ክፍለ ዘመን የማርክስ እና የሌኒን እሳቤ ነው። መደመር እንደዚህ አያምንም። መደመር ‘እኛ ውስኪ ጠጪ ኢሕአዴጎች እባካችሁን ውሐ የናፈቀው ሕዝብ እንዳለ አትርሱ’ ይላል» ብለዋል። 

EPRDF Logo

ኢሕአዴግ የሚመራበትን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት ይተካል ተብሎ የሚጠበቀው እና «የመደመር ፍልስፍና» የሚያብራራው የጠቅላይ ምኒስትሩ መጽሐፍ አዲስ አበባ በሚገኘው የሚሊኒየም አዳራሽ እርሳቸው እና ባለቤታቸው ዝናሽ ታያቸው በተገኙበት በይፋ ተመርቋል። ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች 64 ከተሞች የተመረቀው የጠቅላይ ምኒስትሩ መፅሐፍ በኦሮምኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች በአንድ ሚሊዮን ኮፒ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በዛሬው የመጽሐፍ ምረቃ መርሐ-ግብር ንግግራቸው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ስለ ኤርትራ እና በቅርቡ ስላገኙት የኖቤል የሰላም ሽልማት አንስተዋል። «የኤርትራ መንግሥት እና የኤርትራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሥጋት አይደሉም፤ ተስፋ ናቸው» ያሉት ዐቢይ «ወንድሞቻችን ጋር የጀመርንውን ዕርቅ ወደ ብልፅግና እናሸጋግራለን እንጂ ወደ ኋላ አንመልም» ሲሉ ተናግረዋል። 


እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ