1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ያልቻሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቤቱታ

ሰኞ፣ መጋቢት 4 2015

ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው እናት እና ባልደራስ የተባሉ ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ እንዳይችሉ መከልከላቸውን አስታውቀዋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁለቱም ፓርቲዎች ጉባኤዎች ላይ ታዛቢዎችን በመላክ ስብሰባውን ለመከታተል ሞክሮ እንደነበር ፓርቲዎቹ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4ObwD
Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
ምስል Seyoum Getu/DW

«እናት ፓርቲ እና ባልደራስ»

ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው እናት እና ባልደራስ የተባሉ ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ እንዳይችሉ መከልከላቸውን አስታውቀዋል። ሁለቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ክልከላ ያደረጉባቸው አካላት የመንግሥት የፀጥታ ኃይላት መሆናቸውን ያስታወቁ ሲሆን ይህንንም የሚያደርጉት ጉባኤዎች ሊደረጉባቸው እቅድ የተያዘባቸው ሆቴልና አዳራሽ ባለቤቶችን በቃል በማስፈራራትና እንዳይፈቅዱ በማስጠንቀቅ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ «ተግባር የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያከስም ዐይን ያወጣ  ሕገ - ወጥ ተግባር በመሆኑ የመንግሥትን ድርጊት በጽኑ እናወግዛለን» ያለው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ ( ኢዜማ ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ «የችግሩን ልክ በሚመጥን መልኩ ኃላፊነቱን እንዲወጣ» በማለት ጠይቋል። ፓርቲዎች ተሰብስበው ሥራ አሥፈፃሚዎቻቸውን መምረጥ ካልቻሉ አጠያያቂ ነው የሚለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ቢያደርግም አለመቻሉን ጠቅሶ «በሥርዓቱ በኩል ያለው ማነቆ ከሚታሰበው በላይ ሆኗል» በማለት ድርጊቱን አውግዟል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና ብሔራዊ ምርጫ ቤርድ «ጉባኤው ይካሄድ የሚል» የፈቃድ ደብዳቤ ጽፈውልን ነበር የሚሉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር በቃሉ አጥናፉ ፤ ጉባኤውን ልናካሂድበት ያቀድነው ሆቴል በተደጋጋሚ ከደህንነት ሰዎች በቃል ማስጠንቀቂያ ይሰጠው ስለነበር ጉባኤ ማድረግ አልቻልንም ብለዋል።
«ሕጋዊ የሆኑ ወረቀቶችን ከሚመለከተው አካል ደብዳቤ ይዘናል። ግን ሆቴሎች ጋር ይሄዱና የደህንነት ኃይላት ስብሰባውን እንዳታካሂዱ እያሉ አራት ጊዜ ማስጠንቀቂያ ይሰጧቸዋል። ስለዚህ ሆቴሉ ፈራ፣ በፍፁም ማካሄድ አይችልም አሉ።»
ከዚህ አስቀድሞ እናት ፓርቲ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤን ለማድረግ ቢሞክርም የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዳይጠቀም በመንግሥት ክልከላ እንደተጣለበት አስታውቆ ነበር። ፓርቲው ሕጋዊ ሂደቶችን አሟልቶና የአዳራሽ ክፍያ ፈጽሞ ጉባኤውን ለማድረግ አስቀድመን ወደያዘው አዳራሽ ጉባኤተኛው እንዳይገባ «ከመንግሥት የመጣ ትዕዛዝ» ነው በሚል ተከልክለናል ሲሉ የፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ገልፀው ነበር።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁለቱም ፓርቲዎች ጉባኤዎች ላይ ታዛቢዎችን በመላክ ስብሰባውን ለመከታተል ሞክሮ እንደነበር ፓርቲዎቹ ገልፀዋል። ምርጫ ቦርድ ይህ ችግር እንዲፈታ
«የራሱን የመሰብሰቢያ አዳራሽ አዘጋጅቶ ፓርቲዎች በዚያ ጉባኤ እንዲያካሂዱ ማድረግ ወይም ሌላ መፍትሔ መፈለግ አለበት» ያሉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር በቃሉን ለመሰብሰቢያ አገልግሎት የጠየቃችሁት ሆቴል ከለከለን ያላችሁት ውሸት ነው በሚል መግለጫ አውጥቷል በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ እውነቱን የማይናገሩት «ፍርሃት ውስጥ በመሆናቸው ነው» ብለዋል። በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ ( ኢዜማ ) «ይኽ ተግባር የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያከስም ዐይን ያወጣ ሕገ - ወጥ ተግባር»  መሆኑን በመግለጽ ክልከላ ፈጽሟል ያለውን የመንግሥት አካልን ድርጊት አውግዟል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶክተር ራሔል ባፌ በበኩላቸው «እኛም ተሰሚነትን ያጣንበት ነው» በማለት እርምት እንዲደረግ አሳስበዋል። በጉዳዩ ዙሪያ መንግሥታዊው የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዳዳሪ የሆነው አካል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ እንዲሰጥ ለማድረግ ያደረግሁት ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። የፓርቲዎቹ ጉባኤ እንዳይደረግ ክልከላ አድርጓል የተባለው አካል «መንግሥት» ከመባሉ በቀር የትኛው እንደሆነ በግልጽ ለመረዳት ስላልተቻለ እኛም ለይተን ጥያቄ ለማቅረብ ተቸግረናል።

Äthiopien Addis Ababa | Pressekonferenz | Balderas
ምስል Solomon Muche/DW

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ