1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ «አካታች ብሔራዊ ውይይት» ለማካሔድ ቃል ገቡ

ሰኞ፣ መስከረም 24 2014

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ «በመጪው ዘመን ብዝኃነታችንን በጌጥነት ተቀብለን መታረቅ የሚችል ሐሳባችንን አስታርቀን መከበር የሚገባው ልዩነቶቻችችን አክብረን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠንክረን ወደ ከፍታ የምንተምበት ጊዜ ይሆናል። ይኸም እንዲሳካ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ለማጥበብ አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እናካሒዳለን» ብለዋል

https://p.dw.com/p/41FLc
Äthiopien | Vereidigung Abiy Ahmed
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ «አካታች ብሔራዊ ውይይት» ለማካሔድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሐይማኖት አባቶች እና በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በዓለ ሲመታቸው ሲፈጸም ቃል ገቡ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ብሔራዊ ውይይቱ «ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ይፈታሉ ብለው የሚያምኑትን» የሚያካትት እና በኢትዮጵያውያን የሚመራ እንደሚሆን ጥቆማ ሰጥተዋል።

በትግራይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው እና «በክህደት እና በእብሪት  የተጠነሰሰ»  ያሉት ግጭት «እንደ ሀገር እጅግ ከባድ ዋጋ» ማስከፈሉን ዐቢይ በበዓለ ሲመታቸው ተናግረዋል። 

ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ኢትዮጵያን ለመምራት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሲካሔድ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተጋበዙ መሪዎች ንግግር አድርገዋል። 

የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት፣ የጅቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌህ፣ የሴኔጋሉ ማኪ ሳል እና የኬንያው ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታ በመርሐ-ግብሩ ተገኝተው ንግግር ካደረጉ መካከል ይገኙበታል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበዓለ ሲመታቸው «በመጪው ዘመን ብዝኃነታችንን በጌጥነት ተቀብለን መታረቅ የሚችል ሐሳባችንን አስታርቀን መከበር የሚገባው ልዩነቶቻችችን አክብረን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠንክረን ወደ ከፍታ የምንተምበት ጊዜ ይሆናል። ይኸም እንዲሳካ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ለማጥበብ አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እናካሒዳለን» ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ «የምክክር ሒደቱ ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ይፈታሉ ብለው የሚያምኑትን የሚያካትት፤ በፖለቲካ ልሒቃን መካከል ብቻ የሚደረግ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ያገናዘበ አጠቃላይ ሒደቱ አካታች እና አሳታፊ እንዲሁም በኢትዮጵያውያን እየተመራ ሀገር በቀል መፍትሔዎች ለማፍለቅ ታልሞ የሚከናወን ይሆናል» ሲሉ ስለ ብሔራዊ ውይይቱ አካሔድ ጥቆማ ሰጥተዋል።