1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግድያና ማፈናቀል፤ ኦሮሚያ ክልል ወለጋ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 27 2015

በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች ላለፉት አራት ዓመታት የአማራ ማንነት ባላቸው ሰዎች ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉት የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ ማፈናቀል፣ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት በመንግሥት መዋቅር ድጋፍ የተፈፀመ ነው ሲሉ ሦስት ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፖርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ገለፁ።

https://p.dw.com/p/4KYdI
Äthiopien | Parteien verurteilen die Gewalteskaltation in der Oromia Region
ምስል Solomon Muchie/DW

«በመንግሥት መዋቅር ድጋፍ የተፈፀመ ነው» አሉ

በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች ላለፉት አራት ዓመታት የአማራ ማንነት ባላቸው ሰዎች ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉት የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ ማፈናቀል፣ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት በመንግሥት መዋቅር ድጋፍ የተፈፀመ ነው ሲሉ ሦስት ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፖርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ገለፁ። የሚፈፀሙ ወንጀሎች በኦነግ ሸኔ ተፈፀሙ እየተባለ ቢቆይም እያደር እየጠራ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጭምር ግንባር ቀደም የጥፋቱ ተሳታፊ እየሆኑ ነው ሲሉ እናት፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ ፓርቲዎች ገልፀዋል። በማናለብኝነት እና በጭካኔ እየተፈፀመ ቀጥሏል ያሉት የዜጎች ጭካኔ የተሞላበት ግድያ እና ማፈናቀል እንዲቆም ችግሩ የተከሰተባቸው አካባቢዎች በወታደራዊ እዝ ሥር እንዲመሩ፣ አጥፊዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ሦስቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ኢዜማ በተናጠል ባወጣው መግለጫ ደግሞ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ እና በመደበኛ የፀጥታ ኃይል ለመጠበቅ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ መንግሥት ግድያው በሚፈፀምባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን እንዲያስታጥቅ ጠይቋል።

እናት፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ የተባሉ ፓርቲዎች በጋራ ፣ ኢዜማ በተናጠል ዛሬ በሰጧቸው መግለጫዎች መንግሥት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወለጋ ዞኖች ውስጥ እየተፈፀመ የሚገኘውን አሰቃቂ የዜጎች ግድያ እንዲያስቆም፣ አጥፊዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል። በሌላ በኩል ይህ ሁሉ ጥፋት እየደረሰ ያለው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ሰዎች ድጋፍ መሆኑን በተናጠልም ሆነ በጋራ መግለጫ ያወጡት ፓርቲዎች አስታውቀዋል። አቶ ጌትነት ወርቁ የእናት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የሦስቱን ፓርቲዎች የጋራ አቃም በንባብ አቅርበዋል። «በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች በተደጋጋሚ ጊዜ ላለፉት አራት ዓመታት የአማራ ማንነት ባላቸው ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ፣ ማፈናቀል ፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት በመንግሥት መዋቅር ድጋፍ የተፈፀመ ለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ» ብለዋል። 

የታጣቂዎች ግድያ ያላባራበት የወለጋ ወረዳዎች

ፓርቲዎቹ «የደም ምድር እየሆነ የመጣው» ሲሉ በገለፁት የምስራቅ ወለጋ ዞን ፍጅቶች መፈፀማቸውን፣ በመቶዎች መሞታቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ከቤት ንብረት መፈናቀላቸውንና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱን አስታውቀዋል።

አካባቢውም በወታደራዊ እዝ ሥር እንዲተዳደር ጠይቀዋል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ኢዜማ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ሰሞነኛውን በዜጎች ላይ የደረሰውን እልቂት "መንግሥት የሚባል ነገር የለም እንዲባል ለማድረግ" የተፈፀመ ነው በማለት ችግሩ የሚባባሰው "ወያኔ" ሲሉ የጠሩት ሕወሓት ሲሸነፍ የሚከሰት ክስተት አድርገው አቅርበውታል።

Äthiopien Politik PK Oromia
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ኢዜማ መግለጫምስል Solomon Muchie/DW

በምስራቅ ወለጋ ጉትን ከተማና አካባቢው የጸጥታ ችግር

የኢዜማ ብሔራዊ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ ባነበቡት መግለጫ «አሁንም ብዙ ዜጎች በኦነግ ሸኔ ታግተው ይገኛሉ» ብለዋል። «የኦሮሚይ  ክልልም ሆነ የፌዴራል ማምግሥታት በእርግጥም ሀገር አየመሩ መሆናቸውን በገቢር ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል» ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ መንግሥት በማንኛውም ሁኔታ የዜጎችን ሁለንተናዊ ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ፣ በአካባቢው ያለው ሁኔታ ተጣርቶ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና አፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ እና ድጋፍ ለተጎጂዎች እንዲቀርብ እንዲሁም ለጉዳዩ ዘላቂ እና ሁለንተናዊ መፍትኄ እንዲበጅ ጠይቋል።

ወለጋ ውስጥ ስለተፈፀመው ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ማውደም እና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት የፌዴራሉም ይሁን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት እስካሁን ምንም ያሉት ነገር፣ የሰጡትም ማብራሪ የለም።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ