1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግድያ ለማውገዝ ሰልፍ የወጡ የዩነቨርሲቲ ተማሪዎች በፖሊስ ተደበደቡ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 18 2014

በኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ ለማውገዝ አደባባይ የወጡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፖሊስ ተደበደቡ። 200 ገደማ ተማሪዎች በተሳተፉበት ሰልፍ "ሞት በቃ" እንዲሁም "አማራ እየሞተ የምትበለጽግ ኢትዮጵያ የለችም" የሚሉ መፈክሮች ታይተዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገረው ተሳታፊ በድብደባው ብዙ ተማሪዎች ሲጎዱ አምስት ገደማ መታሰራቸውን ተናግሯል

https://p.dw.com/p/4DEv0
Äthiopien | Hauptcampus der Universität Addis Abeba
ምስል Solomon Muchi/DW

ከ 150 እስከ 200 የሚሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኤሮሚያ ክልል ማንነትን መሠረት አድርጎ በአማራዎች ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉትን የጅምላ ግድያ በመቃወም ዛሬ ረፋድ ድምፃቸውን ከግቢው ውጪ አሰሙ።
በሰልፉ ላይ ተሳትፈው የነበሩ ሁለት ተማሪዎች ለDW እንደነገሩት የፌዴራል ፖሊሶች ተማሪዎቹ ለተቃውሞ እንደሚወጡ ቀድሞ መረጃ ስለደረሳቸው ብዙ ተማሪዎች ከዋናው ግቢ እንዳይወጡ " አፈና" አድርገዋል።

ተማሪዎቹ "ምንም አይነት ሰልፍ የሚያስከለክል ነገር ሰይዙ "ተቃውሞ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። አስተጋብተናል ካሏቸው መፈክሮች መካከል " ሞት በቃን፣ አማራ እየሞተ የምትበለጽግ ኢትዮጵያ የለችም፣ ዘር ተለይቶ መገደል ይብቃ፣ እኛ እንደማንኛውም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል መታየትና እኩል ተከብሮ መኖር እንፈልጋለን" የሚሉት እንደሚገኙበት ገልፀዋል። 
በዚሁ ድምጽ የማሰማት ሰላማዊ ላይ "ማንንም ብሔር እና ግለሰብ የሚያጠቃ ምንም የተጠቀሙት ነገር የለም" ሲሊ ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰሙት ተማሪዎች አምስት ኪሎ የሚባለው አካባቢ ሲደርሱ ፖሊሶች ድብደባ እንደፈፀሙ እና ብዙ የተጎዳ ተማሪ መኖሩንም ገልፀዋል።
አንደኛው ተማሪ "በድብደባው ብዙ የተጎዳ ሰው አለ። አሁን የካቲት 12 ሆስፒታል የሚገኙ ሦስት ወይም አራት ተማሪዎች አሉ፣ በጣም ደፍ ፈሷቸዋል፣ ተገምሰዋል፣ ታሽገዋል፣ ሌላ እግሩን ወይም እጁን ያልተመታ የለም" ብሏል። ሰላማዊ ሰልፉም በፖሊሶች መበተኑን ተናግሯል።

DW እኩለ ቀን ገደማ በሥፍራው ባደረገው ምልከታ ሁለት ነጠላ በር ያላቸው "ሲንግል ጋቢን" የሚባሉ የመከላለያ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ላይ አምስት አምስት ወታደሮች ሆነው ዋናው የአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ በር በር ላይ ጥበቃ ሲያደርጉ ተመልክቷል። በሥፍራው የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትም በብዛት ታይተዋል።

በቤታው የነበሩ ወታደሮች ሙሉ ትጥቅ የታጠቁና ስናይፐር የሚባለውን የጦር መሳሪያ ወድረው የያዙ ነበሩ።
ይህንን ክስተት ተከትሌ በማህበራዊ መገናኛዎች ተቀርጾ በተለቀቀ አንድ ምስል ወይም ቪዲዮ ላይ የፌዴራል ፖሊሶች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሲደበድቡ ታይተዋል፣ ተማሪዎቹም ሲጯጯኹ ይሰማል።

ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ