1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግንቦት 23፤ ትንባሆ ያለማጨስ ቀን

ማክሰኞ፣ ግንቦት 24 2013

በየዓመቱ በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ግንቦት 31 በኢትዮጵያ ደግሞ 23 ቀን በተመድ ዓለም አቀፍ ትንባሆ ያለማጨስ ቀን ይታሰባል። ዕለቱ በዓለም የጤና ድርጅት እንዲታሰብ የተወሰነው በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ከ1987 ዓ,ም ጀምሮ ነው። ስንቶች ዕለቱን ትናንት አስበውት ይሆን? ትንባሆስ ተላላፊ ላልሆኑ አደገኛ ህመሞች እንደሚዳርግስ?

https://p.dw.com/p/3uJJV
Bildergalerie Rauchverbot
ምስል picture-alliance/AP Photo/Ng Han Guan

«በዓመት አንዴ በመላው ዓለም ይታሰባል»

በመላው ዓለም በየዓመቱ ከስምንት ሚሊየን በላይ ሰዎች በትንባሆ መዘዝ እንደሚሞቱ ይነገራል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከእነዚህ መካከል 1,2 ሚሊየን የሚሆኑት ቀጥታ አጫሾች ሳይሆኑ ለጭሱ የተጋለጡ ናቸው። የዓለም የጤና ድርጅት ትንባሆ ያለማጨስ ቀን እንዲታሰብ ዋና መነሻው የሆነውም በትንባሆ መዘዝ ለሚመጡ ህመሞች ትኩረት በመስጠት ለመከላከል የሚቻል ሞትን እንዲሁም የህመም ምክንያቶችን ለመቀነስ በማሰብ ነው። በአሁኑ ጊዜ የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ዓለምን ግራ በማጋባቱ ትኩረት ወደእሱ ላይ ሆኖ እንጂ ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች የሚሞተው ሰው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑ እየተነገረ ከርሟል። በዚህ መሰናዶ በተለያዩ ጊዜያት ማብራሪያ የሰጡ የህክምን ባለሙያዎች ጥናቶችን እና የየዕለት አስተውሏቸውን ተመርኩዘው እንደገለጹት በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ጨምሯል። የደም ግፊት፤ የስኳር፣ የተለያዩ አካላትን የሚጎዳው ካንሰር፤ እና የኩላሊት ህመሞች በአብዛኛው መንስኤያቸው ትንባሆ የሚሆንበት ዕድል ከፍተኛ መሆኑን ነው አቶ ወንዱ በቀለ የማትያስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የገለጹልን። የዓለም የጤና ድርጅት ይኽ ዕለት በየዓመቱ እንዲታሰብ ሲወስን ዋነኛ ግቡ ሰዎች ትንባሆ የሚያስከትለውን መዘዝ ተረድተው ራሳቸውን ከዚህ እንዲህ እንዲያርቁ ለማስገንዘብ ነው።

Türkei Tabakkonsum Protest
ምስል Getty Images/AFP/A. Altan

ችግሩን ለመቀነስም በዓለም የጤና ድርጅት መሪነት የተለያዩ ሃገራት የትንባሆ አጠቃቀም ላይ ጠንከር ያለ መመሪያና ደንብ በማውጣት የየዜጎቻቸውን ሕይወት እንዲታደጉ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕዝብ በሚሰበሰብበት ስፍራ ማጨስ መከልከልን ጨምሮ የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። ኢትዮጵያም እንዲህ ያለውን ርምጃ መውሰድ የሚያስችል ደንብ ከአራት ዓመታት በፊት በምክር ቤቷ አጽድቃለች። የማዕቀፉ ዋና ትኩረት ደግሞ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ እንዳይጨስ ከማድረግ ጀምሮ ዋጋውን ከፍ በማድረግ፣ የትንባሆ አቅርቦት እንዲስተጓጎል ማድረግ ነው። ሆኖም ይኽ የተሳካው ሌላው ቀርቶ ከአፍሪቃ ውስጥ አብዛኞቹ ሃገራት ደንቡን ከተቀበሉ በኋላ ነው ምክር ቤት የወሰነው። ለምን ይሆን? ደንቡ እንዲጸድቅ ይታገሉ ከነበሩት መካከል ማትዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ ነበርና አቶ ወንዱ ዋና ዋና የሚባሉትን ምክንያቶች ገልጸውልናል።

Verhandlungen über Antitabak-Konvention in Genf
ምስል AP

እንዲህም ሆኖ ትንባሆ ቁጥጥር ላይ እስካሁን በተሠሩ ሥራዎች በተከታታይ ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ሽልማቶችን  አግኝታለች። የሀገሪቱ ምክር ቤት በአፍሪቃ አህጉር እጅግ ጠንካራ የሚባል ደንብ በማውጣቱ ሲሸለም፤ ዘንድሮ ደግሞ የኢትዮጵያ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊ ተሸልመዋል። ባለፈው ዓመትም አቶ ወንዱ በቀለ በዚህ ረገድ በማስተባበር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማት አግኝተዋል።   

ትንባሆ ማጨስን ለማቆም አንድ መቶ ምክንያቶች እንዳሉ ያመለከተው የዓለም የጤና ድርጅት ዘንድሮ መሪ ቃል ያደረገው ለማቆም ቁረጥ የሚል ነው። ጤናን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች በቀላሉ ሊሸሹት የሚቻል ብቸኛው መንስኤ ደግሞ ማጨስ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል። ማጨስ ማቆም የሚፈልጉ የትንባሆ ሱሰኞችን በተገቢ ምክሮች ለመደገፍም ዝግጁነቱንም ይፋ አድርጓል።

 ሸዋዬ ለገሠ