1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ግብጽ የኅዳሴ ግድብ እንደምታፈርስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 14 2013

"ግብጽ በዚያ መንገድ ልትቀጥል ስለማትችል ኹኔታው አደገኛ ነው" ያሉት ዶናልድ ትራምፕ እየደጋገሙ "በመጨረሻ ያንን ግድብ ያፈርሱታል። ግድቡን ያፈርሱታል። አንዳች ነገር ማድረግ አለብኝ ” ሲሉ ተደምጠዋል። ትራምፕ የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ግብጾች ሊያስቆሙት ይገባ እንደነበርም ለሱዳን እና ለእስራኤል ጠቅላይ ምኒስትሮች ነግረዋቸዋል።

https://p.dw.com/p/3kNY7
USA Washington | Treffen Fitsum Arega, Botschafter Äthiopien & Präsident Donald Trump
ምስል Fitsum Arega - Ethiopian ambassador to the United States

ኢትዮጵያ ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ ያወጣችበትን ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግብጽ እንደምታፈርስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።  ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ግድቡን እንድትገነባ ግብጽ መፍቀድ አልነበረባትም ብለዋል። ይኸን ያሉት ትናንት አርብ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ሱዳን እና እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት መጀመራቸውን በማስመልከት ከጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ነው።

ከሱዳን ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ እና ከእስራኤሉ ጠቅላይ ምኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት ድንገት የኅዳሴ ግድብን ጉዳይ ያነሱት ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት አስተያየት "ግድቡ እንዳለመታደል ሆኖ ውኃ ወደ ናይል እንዳይፈስ ያቆማል" ሲሉ ተደምጠዋል።    

"ሥምምነት አቅርቤላቸው ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ሥምምነቱን ሳትቀበል ቀርታለች። እንደዚያ ማድረግ አልነበረባቸውም። ያ ትልቅ ስህተት ነው" የሚል አስተያየት የሰጡት ዶናልድ ትራምፕ በዚሁ ምክንያት አገራቸው ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን "በርካታ ዕርዳታ" ማቆሟን አረጋግጠዋል።  

"እንደዚያ በማድረጋቸው በርካታ ዕርዳታ መክፈል አቁመናል። ሥምምነቱን ካልተቀበሉ በቀር ያንን ገንዘብ አያዩትም። ውኃ ወደ ናይል እንዳይፈስ የሚያቆም ግድብ ገንብተዋል። ግብጽ ትንሽ በመበሳጨቷ ልትወቅሷት አትችሉም" ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በጉዳዩ ላይ ከሱዳኑ ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ አስተያየት ጠይቀው ነበር።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ በወገናቸው አሜሪካ በዋሽንግተን ሶስቱን አገሮች ለማሸማገል አደረገች ያሉትን ጥረት አድንቀው ለኢትዮጵያ፣ ለሱዳን እና ለግብጽ ከሚጠቅም ሥምምነት ለመድረስ "ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

የአሜሪካ አቋም እና የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር

የፕሬዝዳንቱ አስተያየት የተደመጠው ሱዳን ከእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት መጀመሯን በማስመልከት ከጠቅላይ ምኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና ከጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በስልክ እየተነጋገሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።  ፕሬዝዳንቱ ይኸን ሲናገሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ማይክ ፖምፔዎ እና የአሜሪካ ግምዣ ቤት ኃላፊ ስቴፈን ምኑችንን ጨምሮ በቅርብ ረዳቶቻቸው ተከበው ነበር።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በግድቡ ላይ የሚፈርሙት "ሥምምነት ጨርሼ ነበር። ነገር ግን ሳይቀበሉ ቀሩ" ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ደጋግመው "እንደዚያ ማድረግ አይችሉም" ሲሉ ተደምጠዋል።  

አሜሪካ ሶስቱን አገሮች ለማሸማገል የጀመረችውን ጥረት ኢትዮጵያ ያቋረጠችው ከየካቲት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ነው። የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ያዘጋጀውን የሥምምነት ረቂቅ «የሶስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም» በማለት ውድቅ አድርጋለች።

ኢትዮጵያ በአሜሪካ የተዘጋጀውን የሥምምነት ረቂቅ ውድቅ አደረገች

ኢትዮጵያ ከአሜሪካው ድርድር ካፈገፈገች በኋላ ድርድሩ በደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አሸማጋይነት እንዲካሔድ ተደርጎ ነበር። በአፍሪካ ኅብረት ሥር የሚደረገው ድርድር እስካሁን አልተጠናቀቀም።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ግን ኢትዮጵያ እና ግብጽ በግድቡ ላይ ያላቸው ልዩነት ተካሮ ካይሮ ግድቡን "እንደምታፈርስ" ተናግረዋል። "ግብጽ በዚያ መንገድ ልትቀጥል ስለማትችል ኹኔታው አደገኛ ነው" ያሉት ዶናልድ ትራምፕ እየደጋገሙ "በመጨረሻ ያንን ግድብ ያፈርሱታል። ግድቡን ያፈርሱታል። አንዳች ነገር ማድረግ አለብኝ ” ሲሉ ተደምጠዋል።   

ትራምፕ የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ግብጾች ሊያስቆሙት ይገባ እንደነበርም ለሱዳን እና ለእስራኤል ጠቅላይ ምኒስትሮች ነግረዋቸዋል።  የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉት ታላቁን የኅዳሴ ግድብ ግብጾች "ከመጀመሩ ረዥም ጊዜ በፊት ሊያስቆሙት ይገባ ነበር።"

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ