1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ አቋም እና የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር

እሑድ፣ ሐምሌ 26 2012

ኢትዮጵያ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ በተከተለችው አቋም የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ለአገሪቱ የምትሰጠውን ዕገዛ የመከልከል ሐሳብ እንዳለው ፎሬይን ፖሊሲ ዘግቧል። እውነት ከሆነ ጉዳዩ ስለ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት ምን ይናገራል? አሜሪካስ በድርድሩ የኢትዮጵያን ዕምነት እስክታጣ ለግብጽ የመወገን አዝማሚያ ለምን አሳየች?

https://p.dw.com/p/3gGtG
USA Washington | Treffen Fitsum Arega, Botschafter Äthiopien & Präsident Donald Trump
ምስል Fitsum Arega - Ethiopian ambassador to the United States

ውይይት፦ የአሜሪካ አቋም እና የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር

በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ፎሬይን ፖሊሲ መጽሔት ባለፈው ሳምንት የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ዕርዳታ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ በተከተለችው አቋም ምክንያት ለመከልከል እያሰበ እንደሆነ ዘግቧል። በዘገባው መሠረት የአሜሪካ ግምዣ ቤት ለኢትዮጵያ ሊሰጡ የታቀዱ ዕርዳታዎችን እንዲገመግም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ጠይቋል። ፎሬይን ፖሊሲ ያነጋገራቸው ሶስት ባለሥልጣናት ዓላማው ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ዕርዳታውን ለማቀብ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል። በዘገባው መሠረት ይኸ የሰብዓዊ ዕርዳታዎችን አይመለከትም።

ፎሬይን ፖሊሲ ያነጋገራቸው የአሜሪካ ባለሥልጣን የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በድርድሩ ለግብጽ የመወገን እምነት እንዳደረበት ተናግረዋል። አሜሪካ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የሚደረገውን የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር በታዛቢነት ተቀላቅላ ረቂቅ ሥምምነት ወደማዘጋጀት ከተሸጋገረች በኋላ በኢትዮጵያ በኩል ገለልተኝነቷ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል። ኢትዮጵያም ድርድሩን እስከማቋረጥ ደርሳለች። በአዲስ አበባ፣ ካይሮ፣ ኻርቱም እና ዋሽንግተን ሲካሔድ የቆየው ድርድር ያለ ውጤት ተበትኖ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት እንዲከናወን ሆኗል። አሜሪካ አሁንም ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በዚሁ ድርድር በታዛቢነት እየተሳተፈች ትገኛለች። 

አሜሪካ በኢትዮጵያ የ5 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ትብብር (International Development Finance Corporation) በተባለው ተቋም በኩል ፈሰስ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት የኢትዮጵያው የገንዘብ ምኒስትር አሕመድ ሽዴ ባለፈው የካቲት 2011 ዓ.ም ተናግረው ነበር። ከሶስት እስከ አምስት አመታት ገቢራዊ ይሆናል ተብሎ የነበረው ይኸ መዋዕለ ንዋይ የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ እና ቻይና በአገሪቱ ላይ ያላትን ሚና ለመገዳደር የታቀደ ነበር። ከዚህ ባሻገር በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ.ም. አሜሪካ ከ824 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለኢትዮጵያ ዕገዛ ያደረገች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 497 ሚሊዮን ዶላር የሰብዓዊ ዕርዳታ ነበር።

ይኸ የውይይት መሰናዶ አሜሪካ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር ውስጥ ያላትን ሚና እና የፕሬዝዳትን ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በእርግጥ ኢትዮጵያን ዕርዳታ ይከለክል እንደሁ ያጠይቃል። በውይይቱ የፓን አፍሪካ የጥናት ባለሙያዋ ማሕሌት አየለ፤ በዓለም ባንክ በከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉት እና የናይል ክለብ መሥራች እና ሊቀመንበር ዶክተር ዮናስ ብሩ እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ የፖለቲካ ተንታኝ ሆነው ያገለገሉት ሰላሐዲን እሸቱ ተሳትፈዋል።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ