1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋና ካካዋ ለምን ለስዊዘርላንድ አልሸጥም አለች?

ቅዳሜ፣ መጋቢት 25 2013

የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ባለፈው ሳምንት አገራቸው ከእንግዲህ ለቸኮሌት ማምረቻ በግብዓትነት የሚውለውን ካካዎ ወደ ስዊትዘርላንድ እንደማትልክ አስታውቀዋል። አዶ "ጥሬ ዕቃ እያመረቱ ወደ ውጪ በመላክ ላይ የተመሠረተ የኤኮኖሚ መዋቅር እየተከተልን በመዝለቅ ለጋናውያን በአጭር፣ መካከለኛም ሆነ ረዥም ጊዜ ጠብ የሚል ነገር የለም" ሲሉ ተደምጠዋል

https://p.dw.com/p/3rYSl
Ghana Präsident Nana Akufo-Addo mit Maske
ምስል Francis Kokoroko/REUTERS

ጋና ካካዋ ለምን ለስዊዘርላንድ አልሸጥም አለች?

የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ባለፈው ሳምንት አገራቸው ከእንግዲህ ለቸኮሌት ማምረቻ በግብዓትነት የሚውለውን ካካዎ ወደ ስዊትዘርላንድ እንደማትልክ አስታውቀዋል። "እኛ ጥሬ ዕቃውን እንፈልጋለን፤ እናንተ ደግሞ ጥሬ ዕቃው አላችሁ" ያሉት የስዊዘርላንድ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሲሞኔታ ሶማሩጋ ከጋና አቸቻው ጋር ሆነው ንግግር ባደረጉበት ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል በወርቅ እና በካካዋ የሚደረግ የንግድ ልውውጥ ሥራ እና ሐብት ይፈጥራል ብለው ነበር። 

ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ግን ካካዋን ጨምሮ ጋና ጥሬ ዕቃ ወደ ውጪ እየላከች መዝለቅ አትችልም ሲሉ ፈርጠም ብለው ተናግረዋል። አዶ እንዳሉት አገራቸው በበለጸጉት አገራት በውድ የሚቸበቸበውን ቸኮሌት ራሷ ለማምረት ዕቅድ አላት። "ጥሬ ዕቃ እያመረቱ ወደ ውጪ በመላክ ላይ የተመሠረተ የኤኮኖሚ መዋቅር እየተከተልን በመዝለቅ ለጋናውያን በአጭር፣ መካከለኛም ሆነ ረዥም ጊዜ ጠብ የሚል ነገር የለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

የፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ውሳኔ ከካካዋ እና ወርቅ ንግድ በላይ በበለጸጉት እና ጥሬ ዕቃ በመላክ ላይ ጥገኛ በሆኑት አገራት መካከል ያለውን የተዛባ የንግድ ግንኙነት የሚያሳይ ሆኗል። የዛሬው የትኩረት በአፍሪካ መሰናዶ በዚሁ የጋና ውሳኔ ላይ ያተኩራል።
እንዳልካቸው ፈቃደ
ታምራት ዲንሳ