1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰለሞን ደመቀ

ዓርብ፣ ጥር 21 2013

ሰለሞን ደመቀ ይባላል። 23 ዓመቱ ነው።  «የፊልም ክህሎት፣ፍቅርና ትልቅ ዓላማ ያለኝ ወጣት ነኝ» ይላል። የካሜራ ባለሙያ ነው። ከዚህም ባሻገር የተለያዩ «የጀብዱ ድርሰቶችን በመፃፍ ሀገሬን በዓለም ለማስተዋወቅ ተዘጋጅቻለሁ» ይላል።

https://p.dw.com/p/3oWoP
Solomon Demeke | Kameramann
ምስል privat

«ጊዜዬን በሙሉ የማጠፋው ድርሰት በመፃፍ ነው»: ሰለሞን ደመቀ

ሰለሞን ደመቀ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር የካሜራ ባለሙያ ነው። በአሁኑ ሰዓት ተቀጥሮ ዩቲውብ ላይ የሚለቀቁ ቃለ መጠይቆችን ይቀርፃል። «ለፊልም የተለየ ፍቅር እና ተሰጥዎ አለኝ» የሚለው ሰለሞን እስካሁን አምስት የፊልም ድርሰቶች ፅፎ ጨርሷል። ከሁሉም ፅሁፎች «የጀብዱ ዘውግ» መፃፍ ያስደስተኛል ይላል። « ምናባዊ ነው፤ ጥንት በነበሩ ድርጊቶች ነው የሚከናወነው። ፊልሙ ላይ ጀግና ይኖራል። ያ ጀግና ደግሞ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነው።» ወጣቱ የፃፋቸው የፊልም ድርሰቶች ግጭቶችን ያካተተ ቢሆንም ፊልሙን በሁሉም የእድሜ ክልል ያለ ኢትዮጵያዊ ሊያየው እንዲችል አድርጌ ነው የፃፍኩት ይላል ፤ ለዚህም ምክንያት አለው። «በተለይ ለአዲሱ ትውልድ በጥንት ጀግኖቻችንን እንዲያውቁ የልጆችን ልብ መያዝ በሚችል አቀራረብ ያንን ታሪክ እንዲያውቁ ማድረግ ነው።» እነዚህ ገፀ ባህሪያትም የሚገጥማቸውን ችግሮች ሲፈቱ አሳያለው ወጣቱ። 


እነዚህንም ድርሰቶች ለመፃፍ የተለያዩ ከግዕዝ የተተረጎሙ መጽሐፍትን ማንበብ እንደነበረበት ሰለሞን ይናገራል። ወጣቱን እምብዛም ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመዱ ድርሰቶችን እንዲፅፍ ይበልጥ ያነቃቁት እሱ እንደሚለው የሚያነባቸው መጽሐፍት እና የውጭ ሀገር ፊልሞች ናቸው። « ውጪ ላይ ያሉት ፊልሞች ከእኛ ከተተረጎሙት ፊልሞች ጋር ይቀራረባሉ። እና እኛ የነበሩንን መፅሐፍት ወደ ፊልም እየቀየርን እየተጠቀምንበት አይደለም» ድርሰቶቹም አጫጭር እና ተከታታይ ታሪኮች ናቸው ይላል ሰለሞን።
የሰለሞን ትልቁ ፈተና  ይህንን ፊልም ዕውን የሚያደርግለት ፕሮዲውሰር ማጣቱ ነው። « አፃፃፉን ቢወዱትም ገንዘብ አውጥተው ፕሮዲውስ ለማድረግ የሚቸግራቸው ነገር የጊዜ ጉዳይ ነው። ቶሎ አያልቅም፣ ገንዘብ አያመጣም፣ ህዝቡ የፍቅር እና ኮሜዲ ነው የሚወደው ይሉኛል» ይላል። ሌላው ደግሞ ገፀ ባህሪዎቹን እንዴት እንደምንሰራ አላውቅም ይሉኛል ይላል።
የካሜራ ባለሙያ የሆነው የ23 ዓመቱ ወጣት ግን ባለ ሙሉ ተስፋ ነው። እነዚህን ምናባዊ ገፀ ባህሪያትም በፊልሙ የሚያካትትበትን መንገድ ታሳቢ አድርጌ ነው የፃፍኩት ይላል። 

ከልጅነቴ አንስቶ ለትምህርት ቤቶች አጫጭር ታሪኮችን ፅፌ አቅርብ ነበር የሚለው ሰለሞን ምንም እንኳን እስካሁን የፊልም ህልሙን እውን ማድረግ ባይችልም፤ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ያበቃው የግል ጥረቱ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራል። «ራሴን ማስተማር ነበረብኝ። ድርሰቱን በየቀኑ ነው የምፅፈው። መውጫው ብቻ ነው የጠፋብኝ» ይላል የጀብዱ ድርሰቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ጀግኖችን በማካተት የተለየ ፊልም ይዞ ለመቅረብ የተነሳው የካሜራና የፊልም ባለሙያ ሰለሞን ደመቀ።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ