1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጊኒ፤ ከ13 ዓመት በፊት በግፍ ግድያ የፈፀሙ ለፍርድ ቀረቡ

ቅዳሜ፣ መስከረም 21 2015

ጊኒያውያን ከ13 ዓመታት በፊት ቢያንስ 157 ሰዎች ለተገደሉበት እልቂት ፍትህ እንዲገኝ የጠበቁበት ጊዜ በቅርቡ እንደሚያበቃ ተስፋ አግኝተዋል። የቀድሞው የሁንታ መሪ ሙሳ ካማራ እና የቀድሞ ሌተናቶቹ ከዳኛ ፊት ለፊት እንደሚቀርቡ በዚሁ ሳምንት ይፋ ተደርጓል።

https://p.dw.com/p/4Hbx7
Guinea Beisetzung Opfer Conakry Massaker 2009
ምስል Getty Images/AFP/Seyllou

ተከሳሾቹ የቀደሞ የሃገሪቱ አመራሮች ናቸዉ

ጊኒያውያን ከ13 ዓመታት በፊት  ቢያንስ 157 ሰዎች ለተገደሉበት እልቂት ፍትህ እንዲገኝ የጠበቁበት ጊዜ በቅርቡ እንደሚያበቃ ተስፋ አግኝተዋል። የቀድሞው የሁንታ መሪ ሙሳ ካማራ እና የቀድሞ ሌተናቶቹ ከዳኛ ፊት ለፊት እንደሚቀርቡ በዚሁ ሳምንት ይፋ ተደርጓል።   

Capt Moussa Dadis Camara Afrika Guinea
ምስል picture-alliance/dpa

በጎርጎረሳዉያኑ 2009 መዲና ኮናክሪ ዉስጥ ከደረሰው እልቂት በሕይወት የተረፈችው ሣራን ሲስ የጸጥታ ኃይሎች በሕዝቡ ላይ ጥይት መተኮስ በጀመሩበት ስታዲየም ውስጥ ስለዚያ ቀን አሁንም ድንጋጤዉ አለቀቃትም። አንድ ወጣት ከዓመፅ እና ግድያዉ ለመሸሽ ግንብ ግድግዳን ላይ ዘልላ እንድትወጣ ሊረዳት መሞከሩን ትናገራለች። ግን ረዳትዋ በድንገት አይኗ ስር ተገደለ

«ግንብ ግድግዳ ላይ ለመውጣት እየሞከርኩ ነበር እና አንድ ወጣት፣ እህት ቆይ ልርዳሽ አለኝ። ከግድግዳው ጫፍ ላይ ነበርኩ ። በጣም የሚገርመው ነገር ወደ ታች እንድወርድ እንዲረዳኝ መለስ ብዬ ስጠይቀዉ፤ ቀስ በቀስ መሬት ላይ ሲወድቅ አየሁት ። ተኩሶበት እየወደቀ ነበር። ግድያዉን ሳስብ አሁንም አለቅሳለሁ።»

በዚያ ቀን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኮናክሪ ስታድየም ተሰብስበው የተቃዋሚዎችን ጥንካሬ ለማሳየት እና ከዘጠኝ ወራት በፊት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት አማካኝነት ወደ ስልጣን የመጡት የሁንታ መሪ ሙሳ "ዳዲስ" ካማራ በጎርጎረሳዉያኑ ጥር ወር 2010 ዓ.ም ለምርጫ ከመቅረብ እንዲታቀብ ለማሳሰብ የተካሄደ ተቃዉሞ ነበር። ወታደሮች፣ ፖሊሶችና የሚሊሻ አባላት ተኩስ በመክፈት ቢያንስ 157 ሰዎችን በገደለው የሁለት ሰዓት ግጭት ምላሽ ሰጡ።

በዚህ ረብሻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ቢያንስ 109 ሴቶች እንደተደፈሩም የተባበሩት መንግሥታት የሰየመዉ ዓለም አቀፍ የምርመራ ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት ገልጿል። ይሁን እንጂ እውነተኛው አኃዝ ከዚህ ከፍ ያለ እንደሆን ይገመታልም ተብሏል።

ይህን አሰቃቂ እልቂት ከፈፀሙት ተጠርጣሪዎች መካከል የቀድሞው የሁንታ መሪ ካማራ እና ከፍተኛ ማዕረግ የሰጣቸዉ ሦስት መኮንኖች ለምርመራ እንዲቀርቡ ተወስኗል። በስደት በቡርኪና ፋሶ ይኖሩ የነበረዉ ሙሳ ካማራ ፍርድ ፊት ለመቅረብ ባለፈዉ ቅዳሜ ምሽት ላይ ወደ ጊኒ ተመልሷል። ሌሎቹ ሦስት ተከሳሾች እልቂቱ ከተፈጸመ በኋላ ባሉት 13 ዓመታት በጊኒ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ ከፍርድ ነፃ ሆነው ቆይተዋል ።   

Guinea Beisetzung Opfer Conakry Massaker 2009
ምስል Seyllou/AFP/Getty Images

የ 11 ተጠርጣሪዎች ችሎት በዚህ ሳምንት ረቡዕ እልቂቱ በተፈፀመበት ኮናክሪ ስቴድዮም አካባቢ ተጀምሯል።  ጊኒ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች ስር እንደ ወደቀች ነዉ። በአሁኑ ጊዜ ሃገሪቱን የሚመሩት የወታደራዊ ሁንታ መሪ ማማዲ ዱምቡያ ናቸው። ዱምቡያ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ 2021 ወደ ስልጣን የመጡት ሃገሪቱን ለ 11 ዓመታት ይመራ የነበረዉን የሲቪል መንግሥት ገልብጠዉ ነዉ። 

ዱምቡያ ሐምሌ ወር ላይ የጊኒ ጭፍጨፋ ችሎት በዚህ ዓመት ይካሄዳል ሲሉ ይፋ ማድረጋቸዉ ህዝብን አስገርሞ አስደንግጦም ነበር። ይሁንና እንደ ብዙዎች ጥርጣሪ የፍርድ ሂደቱ በቀነ ቀጠሮዎች ይጓተታል ተብሎ ይገመታል። በጊኒ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኤስኒ ሳል እንደሚሉት ችሎቱ ተጠናቆ ፍትህ መምጣት አለበት።

«ድል አይደለም፤ የስራዉ አንድ እርምጃ ነው ። የፍርድ ሂደቱ መጠናቀቅ አለበት። በሁሉም ተከሳሾች ፊት የፍርድ ሂደቱ መከናወን አለበት። የምንወክላቸዉ ተጎጂዎች እንዲመጡም ሁኔታዎች መፍጠር አለበት»

በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱን ስልጣን ተቆጣጥሮ የሚገኘዉ ወታደራዊ ሁንታ ጊኒን ወደ ዴሞክራሲ ለመመለስ ፕሮግራም ሳይመቻች ከቀረ በሚል ከጊዜ ወደ ጊዜ ግፊት እየደረበት ይገኛል። ባለፈው ሳምንት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የሁንታዉን የገንዘብ ሀብት አቀዝቅዞ አባላቱ በአካባቢው ሃገራት እንዳይጓዙ አግዷል። የቡድኑ የልማት ባንክም የጊኒን ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ ሰርዟል።

Guinea Juntachef Mamady Doumbouya
ምስል Xinhua/imago images

በጊኒ የሲቪል ማህበረሰብ አራማጅ ሞሃመድ ካማራ ለDW እንደገለፁት ችሎቱ በርካታ መፈንቅለ-መንግሰት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ተከትሎ የጊኒን የቆሸሽ ምስል ሊያሻሽል እንደሚችል ገልጸዋል። የምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ሃገር ጊኒ እንደባውክሳይት እና ወርቅ በመሳሰሉ የተፈጥሮ ሃብቶች የበለጸገች ብትሆንም አሁንም በዓለም ላይ እጅግ ድሃ ከሆኑት ሀገሮች አንዷ ሆና ትቀጥላለች። ይህ እውነታ ደግሞ ከፖለቲካ አለመረጋጋት የመጣ እዉነታ መሆኑን መሃመድ ካማራ ይናገራሉ። ስለሆነም ይላሉ ካማራ በጊኒ አስከፊ ጭፍጨፋ ከተካሄደ  ከ 13 ዓመታት  በኋላ ችሎት መጀመሩ ፍትህን በሃገሪቱ ለማስፈን አንድ ርምጃ ይሆናል።

"እፎይታ ይሰማኛል። ከ2010 ጀምሮ ይህን ችሎት ስንጠባበቅ ቆይተናል፤ በመጨረሻም የጊኒ ባለ ሥልጣናትና የፍትሕ ሥርዓት ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ ወስነዋል። ይህ በእርግጥም ጥሩ ነገር ነው።"

አዜብ ታደሰ / ክሪስቲን ክሪፓል

ታምራት ዲንሳ