ገዳዩን ተሕዋሲ ገዳይ ይገኝ ይሆን?
ሰኞ፣ ግንቦት 17 2012ማስታወቂያ
የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመግታት መንግስታት ጥለዉት የነበረዉን እገዳና ክልከላ እያላሉ ነዉ።ይሁንና ገዳዩ ተሕዋሲ አሁንም ብዙ መቶ ሺሕዎችን መግደል፣ሚሊዮኖችን መልከፉ ወይም መያዙ እንደቀጠለ ነዉ።መድሐኒት ወይም ክትባት ለማግኘት የሚደረገዉ ምርምር፣ጥናትና ሙከራ «አበረታች» ዉጤት ማሳየቱ ይነገራል።ከመነገር ወይም ከተስፋ ባለፍ ግን ፈዋሽ መድሐኒት ወይም ክትባት የሚገኝበት ጊዜ በዉል አይታወቅም።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት የዓለምን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ማሽመድመድ በጀመረበት ባለፈዉ መጋቢት ፕሮፌሰር ዘኪ ሸሪፍን አነጋግሬያቸዉ ነበር።ለኢትዮጵያዉያን ምክር ካሉት አንዱ፣ «ወዳጅ ዘመዱን የሚወድ፣ ፍቅር ዉዴታዉን በመራራቅ ያረጋግጥ» ብለዉን ነበር።ፕሮፌሰር ዘኪ በዩናይትድ ስቴትስ የሐርቫርድና የጆርጅ ታዉን ዩኒቨርስቲዎች የሕክምና መምሕር ናቸዉ።የካንሰር ተመራማሪና ማይክሮ ባዮሎጂስት ናቸዉም።አብዛኞቹ መንግስታት ጥለዉት የነበረዉን እገዳ ካላሉ፣ ኦና የቀሩ ከተሞች ዳግም ነብስ ከዘሩ በኋላ ዛሬ ፕሮፌሰር ዘኪን እንደገና ጠየቅናቸዉ።ገዳዩ ተሕዋሲ አሁንም የያኔዉን ያሕል ያሰጋል ብለን? መለሱም።የዛሬዉ ዝግጅታችን ከፕሮፌሰር ዘኪ ጋር ያደረግነዉ ቃለ መጠየቅ ይስተናገድበታል።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ