1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ገዳማዊቷ የሙዚቃ አቀናባሪ፤ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 19 2015

ከዚህ ዓለም ድካም በ99 ዓመታቸው ማረፋቸው የተሰማው ገዳማዊቷ የሙዚቃ ቀማሪ፤ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የሁለት ዓለም ታሪክ ያካተቱ መሆናቸው ይነገርላቸዋል። በቅርብ የሚያውቋቸው የሙዚቃ አዋቂ፣ ምሁር፣ ሀገር ወዳድ እንዲሁም ሃይማኖተኛ መሆናቸውንም ይገልጻሉ።

https://p.dw.com/p/4POhv
John Lennons Klavier
ምስል AP

«ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ»

 በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ትልቅ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ግንባር ቀደም ሰዎች መካከል የሚጠቀሱት እማሆን ጽጌ ማርያም በቅርብ ሰዎቻቸው ሞት እንዲሁም በኢትዮጵያ ሁኔታ ሲያዝኑ መኖራቸውን እስራኤል በኖሩባቸው ዓመታት በየጊዜው ይጎበኛቸው እንደነበር የገለጸልን ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን አሁንስ አረፉ ነው ያላቸው።

በግል ታሪካቸው ላይ ያጠነጠነው «ደጅ አዳሪው መንደኛ» የተሰኘው ይኽ የሙዚቃ ቅንብር በብዙዎች ዘንድ ዕውቅና አስገኝቶላቸዋል። ገና በአፍላ ወጣትነት የዕድሜ ዘመናቸው መንፈሳዊውን ሕይወት የመረጡት እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ፤ ዘመናዊውን ትምህርት ባሕር ተሻግረው ቀስመዋል። ታኅሣሥ 13 ቀን 1916 ዓ.ም. የተወለዱት እማሆይ ጽጌ ማሪያም በስድስት ዓመታቸው ከዘመናዊ የሙዚቃ ዓለም ጋር በመገናኘታቸው በዘጠኝ ዓመታቸው በቫዮሊን ትርኢት ለማሳየት መቻላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በ1928 ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ ከመላ ቤተሰባቸው ጋር በመሰደድ የጥቁር አንበሳ ጦር ተቀላቅለው በሽምቅ ውጊያ ሦስት ወንድሞቻቸው ተገድለዋል። ጦርነቱ ሲፋፋምም ቤተሰባቸው በሙሉ ወደ ኔፕልስ፣ ጣሊያን በግዞት ተወስዶ እዚያ ቆይተዋል። ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እሳቸውም ሆኑ ቤተሰባቸው በጸረ ፋሽስት ትግል በአርበኝነት መሰለፋቸውን ታሪክ መዝግቦታል ነው የሚለው።

«ቤተሰቡ በሙሉ ፋሺዝምን ለመዋጋት ዱር የገባ ነው።»

Äthiopien Emahoy Tsege Maryam Gebrue
እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ምስል Mahlet Fasil/DW

ከጣሊያን ሽንፈት በኋላ ወደ ካይሮ በመጓዝ የሙዚቃ ትምህርታቸውን የቀጠሉ ሲሆን ወደ ሀገራቸው ተመልሰውም የክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ባንድ ዳይሬክተር ሆነው መሥራቸው ተመዝግቧል። ዕብራይስጥ፤ አማርኛና ግይዝን ጨምሮ ወደ ሰባት የሚጠጉ ቋንቋዎችን ይናገሩ የነበሩት የሙዚቃ አዋቂ፤ በቤተመንግሥት ከንጉሡ ፊት ከሚያቀርቡት ሙዚቃ ሌላ በአስተርጓሚነትም ማገልገላቸው ተመዝግቧል።

የቤተሰቦቻቸው ሞት እንዲሁም በቅርብ የሚያውቋቸውን ንጉሣዊ ቤተሰብና ታላላቅ ሰዎች ሕልፈት ሀዘን ላይ ጥሏቸው እንደኖሩ ኢየሩሳሌም የሚኖረው እና በቅርብ የሚያውቃቸው ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ይናገራል።

«እማሆይ ጽጌ በሀዘን ላይ የነበሩ ሰው ናቸው። በመሠረቱ በጣም ኢንተሌክቹዋል ናቸው ምሁር ናቸው፤ ሀገር ወዳድ ናቸው ሃይማኖተኛም ናቸው። በነገሥታቱ አሟሟት እና በሌሎችም ኢትዮጵያውያን አሟሟት በጣም ያዝናሉ።»

የመጀመሪያ የሙዚቃ ሥራቸው በ1959 ዓ,ም ጀርመን ሀገር በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እገዛ በሸክላ የታተመ ሲሆን፤ ሙዚቃውም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የፒያኖ የረቂቅ ሙዚቃ ሸክላ ሆኖ ተመዝግቧል። ገዳማዊቱ የሙዚቃ ቀማሪ ብቸኝነትን፤ የሀገር ናፍቆትን ከሚያንጸባርቁት የታወቁ ሥራዎቻቸው ሌላ ወደ አድማጭ ያልደረሱ ከመቶ በላይ የሙዚቃ ኖታዎችን ዋጋ ሰጥቶ የሚረከባቸው እንዳላገኙ ከእሳቸው መረዳቱንም ነው ጋዜጠኛ ዜናነህ የገለጸው።

Symbolbild Retro Notenblätter
የሙዚቃ ኖታምስል Colourbox

ሥራዎቻቸውን ክላሲካል ከሚባለው የሾፐን፤ ሹበርት እና ሹማን ሥራዎች ስልት ላይ ተመርኩዘው ኢትዮጵያዊ በሆነ ቃና እንዳቀረቡ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ዶክተር ዕዝራ አባተ ገልጸውልናል። ታዋቂው ፒያኒስ ግርማ ይፍራ ሸዋ በበኩሉ እማሆይን የማይተኩ ይላቸዋል።

ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤትም በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ለሥራቸውና ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት ተዘጋጅቷል። ከምንኩስና በፊት የውብዳር ገብሩ ይባሉ ስለነበሩት እማሆይ ጽጌ ማርያም ዘጋሪድያንን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በአንድናቆት የታጀቡ ታሪኮችን በተለያዩ ጊዜያት ጽፈዋል። ስለእማሆይ ማን ያልጻፈ አለ የሚለው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የሁለት ዓለም ታሪክ ያላቸው ይላቸዋል።

«ሙዚቃ ይጫወታሉ እንደገና ደግሞ መነኩሲት ናቸው፤ ያልተለመደ ነገር ነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፤ ግን በፒያኖ የሚጫወቱት ምንድነው የሚለው ነው ትልቁ ነገር ነር።»

በወጣትነታቸው ምድራዊውን ዓለም በመናቅ የምንኩስና ሕይወትን በግሸን ማርያም እንደጀመሩ የሚነገርላቸው እማሆይ ጽጌ ማርያም ላለፉት ከ40 ዓመታት በላይ ኑሯቸውን በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም አድርገው ሥዕሎችን ከመሳል ጎን ለጎን የሙዚቃ ኖታዎችን በመጻፍ ቆይተዋል። በ99 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የፊታችን ዓርብ ዕለት የቀብር ሥርዓታቸው ይፈጸማል።

 ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር