1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀግና ወይስ አሸባሪ? የፖል ረሰሰበጂና አወዛጋቢ ተክለ-ስብዕናዎች

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 30 2012

ሆቴል ርዋንዳ በተባለው ፊልም የጀገኑት ፖል ረሰሰበጂና ዓለም የሚያውቃቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ርዋንዳውያንን ከጅምላ ፍጅት በመታደጋቸው ነበር። ባለፈው ሰኞ እጃቸው በካቴና ተጠፍሮ ኪጋሊ የደረሱት ረሰሰበጂና ግን በርዋንዳ መንግሥት በግድያ፣ በእገታ እና ቤት በማቃጠል ይወነጀላሉ። የርዋንዳ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በሽብር መመከሰሳቸውን አስታውቋል

https://p.dw.com/p/3i2zb
Ruanda Paul Rusesabagina
ፖል ረሰሰበጂና የርዋንዳ ንቅናቄ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ (MRCD) የተባለው የተቃዋሚዎች ጥምረት መሪ ናቸውምስል Imago Images/Belga/M. Maeterlinck

ረሰሰበጂና እንዴት ለርዋንዳ መንግሥት ተላልፈው እንደተሰጡ የሚታወቅ ነገር የለም

የ66 አመቱ ፖል ረሰሰበጂና እጃቸው በካቴና ተጠፍሮ አፋቸው ላይ የኮሮና ወረርሽኝ ከበረታ ወዲህ የተለመደ እየሆነ የመጣውን ጭንብል ጣል አድርገው፤ ሱፋቸውን ግጥም አድርገው እንደለበሱ ከዱባይ ኪጋሊ ገቡ። በትውልድ ርዋንዳዊ በዜግነት ቤልጅየማዊ የሆኑት የአሜሪካ ነዋሪ የፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ መንግሥት ባቀረበው ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ ነበር በቁጥጥር ሥር ውለው ከዱባይ ኪጋሊ የገቡት። እስራቸው በጎርጎሮሳዊው 1994 ዓ.ም. በርዋንዳ የጅምላ ጭፍጭፋ በተፈጸመበት ውቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደብቀው ማዳናቸውን በሚተርከው ሆቴል ርዋንዳ በተባለው ፊልም ላወቃቸው ዓለም ብቻ ሳይሆን ለልጃቸው ሮጀር ረሰሰበጂና ጭምር እንግዳ ነበር። 

ሮጀር ረሰሰበጂና "ምን እንደተፈጠር የምናውቀው ነገር የለም። ነገር ግን የርዋንዳ መንግሥት ሲከታተላቸው እንደነበር ግን ግልጽ ነው። በዚህም አፍነው የሚወስዱበት ዕድል እንዳገኙ እገምታለሁ። ዱባይ እንደነበር ነው የማውቀው። ነገር ግን ማረጋገጫ ገና አላገኘንም። ለረዥም አመታት የርዋንዳን መንግሥት ይተች ነበር። ይኸ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አላስደሰተም። ስሙን ሊያጠፉት እና ሊያስሩት ይፈልጉ ነበር" ሲል ተናግሯል። 

ፖል ረሰሰበጂና እንዴት ለርዋንዳ መንግሥት ተላልፈው እንደተሰጡ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሆቴል ርዋንዳ ፊልም በጀገኑት ሰው እስር ጉዳይ እጇ እንደሌለበት አስታውቃለች። ረሰሰበጂና ከዱባይ አውሮፕላን ተሳፍረው በበረሩ በቀናት ልዩነት እጃቸው በካቴና ተጠፍሮ ለቀረፃ ከተደረደሩ የቴሌብዥን ካሜራዎች እና ጋዜጠኞች ፊት በኪጋሊ የተከሰቱት ባለፈው ሰኞ ነበር። ትዕይንቱ "ሆቴል ርዋንዳ" የተባለው ፊልም በመላው ዓለም በተመለከቱት እና ባደነቁት ሰዎች ዘንድ ለፖል ረሰሰበጂና ያላበሰው የጀግና ተዕለ-ስብዕና ለመሰረዝ የተደረገ ጥረት አድርገው የተረዱት በርካቶች ናቸው። 

Film Hotel Ruanda
ፖል ረሰሰበጂና ስማቸው በዓለም የናኘው ሆቴል ርዋንዳ የተባለው ፊልም በሆሊውድ ተሰርቶ ከፍተኛ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነበር። በፊልሙ ረሰሰበጂናን ወክሎ ዋናውን ገጸ ባሕሪ የተወነው አሜሪካዊው ዶን ቺድል ነበርምስል picture-alliance/dpa/Tobis Film

ያ ፊልም ከሑቱ እና ቱትሲ ጎሳዎች የሚወለዱት ሰው ከ26 አመታት በፊት ከተፈጸመው የጅምላ ፍጅት 1,200 ሰዎች ያስተዳድሩት በነበረ ሆቴል ውስጥ አስጠልለው መታደጋቸውን ይተርካል። በዚሁ ምክንያት ሰብዓዊነታቸው አድናቆት ተቸሮት ሜዳልያዎች ተሸልመዋል። በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው የርዋንዳ መንግሥት በወገኑ በግድያ፣ በእገታ እና ቤት በማቃጠል ይወነጅላቸዋል። ሁለቱ ተክለ-ስብዕናዎች ለበርካቶች ለማስታረቅ የሚቸግሩ ናቸው። ተንታኞች ጉዳዩን በጥንቃቄ ይመለከቱታል። ከእነዚህ መካከል በለንደን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ፊል ክላርክ ይገኙበታል። 

"ክሶቹ በፍርድ ቤት ጉዳዩ እንዲታይ የሚያበቃ ተዓማኒነት አላቸው ብዬ አስባለሁ። ክሶቹ አዲስ አይደሉም። የርዋንዳ መንግሥት በ2010 ረሰሰበጂና የርዋንዳ ነፃ አውጪ ኃይሎች (FDLR) የተባለውን እና በምሥራቃዊ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰውን የሑቲ አማፂ ቡድን በገንዘብ ይደግፋሉ ሲል ከሷቸው ነበር። ስለዚህ መንግሥት ለረዥም አመታት ሲከታተላቸው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የኪጋሊን መንግሥት በትጥቅ ትግል ከሥልጣን ማውረድ ይገባል የሚል ቪዲዮ በዩትዩብ በማሰራጨታቸው በተለይ በውጪ አገራት በሚኖሩ ርዋንዳውያን ዘንድ ታዋቂ ሆነው ነበር። በትጥቅ ትግል ውስጥ ባላቸው ሚና ባለፉት አስር አመታት ገደማ ስማቸው በክፋት ሲነሳ ቆይቷል። በስተመጨረሻ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሚያስገርም አይደለም። ነገር ግን የሚቀርቡባቸው ማስረጃዎች በፍርድ ቤት ምን ያክል ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ማየት ይኖርብናል" ይላሉ ፊል ክላርክ።  

ርዋንዳን የከፋፈሉት ሰው

በርዋንዳ የረሰሰበጂና እስር ዕኩል ተቀባይነት አላገኘም። የዶይቼ ቬለው የርዋንዳ ዘጋቢ አሌክ ንጋራምቤ "በርካቶች መታሰራቸውን ጥሩ ዜና አድርገው ተቀብለውታል። በዚህም የተወሰነ የአገሪቱ ክፍል ዳግም አይቃወስም የሚል ዕምነት አላቸው" ሲል ተናግሯል። ንጋራምቤ እንደሚለው በተለይ በተቃዋሚዎች ዘንድ ጉዳዩ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ተገዳዳሪዎቻቸውን ለማጥፋት የሚወስዷቸው እርምጃዎች አንድ አካል አድርገው ወስደውታል። 

Äthiopien AU-Gipfel in Addis Adeba
የፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ መንግሥት ርዋንዳን ከጅምላ ፍጅቱ በኋላ በማረጋጋት እና በፈጣን ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ቢወደስም በአምባገነንነት ይወቀሳል። ምስል Getty Images/AFP/M. Tewelde

ሌላው የዶይቼ ቬለ ጋዜጠኛ ጎንዛጉዌ ሙጋንዋ ከሰባት ወራት ገደማ በፊት የርዋንዳ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎች በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መገደላቸውን ያስታውሳል። "ይኸ ለርዋንዳ መንግሥት ስኬት ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ቀስ በቀስ የትጥቅ ትግል መሪዎችን እየቀነሰ ነው" ይላል ሙጋንዋ።  ሙጋንዋ "ተቃዋሚዎች ካጋሜ እና መንግሥታቸውን በጦር መሳሪያ ለመጋፈጥ በመሞከራቸው ትልቅ ስህተት ሰርተዋል። ምክንያቱም ካጋሜ በዚህ ረገድ ጠንካራ ናቸው" ሲል ያክላል። 

ሙጋንዋ የጠቀሰው ከሁለት አመታት በፊት በደቡባዊ ርዋንዳ ሰላማዊ ሰዎች ገድሏል ተብሎ የሚከሰሰው ብሔራዊ ነፃ አውጪ ጦር (FLN) መቋቋም ነው። ይኸ ታጣቂ ቡድን የርዋንዳ ንቅናቄ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ (MRCD) የተባለው የተቃዋሚዎች ጥምረት የጦር ክንፍ ነው። ረሰሰበጂና ደግሞ ከንቅናቄው መሪዎች አንዱ ናቸው።  የርዋንዳ ባለሥልጣናት የ66 አመቱ ረሰሰበጂና ሆቴል ርዋንዳ ፋውንዴሽን በተባለው ተቋማቸው በኩል አማፂውን በገንዘብ ይደግፋሉ ብለው ይከሷቸዋል። 

የወደቀ ጀግና?

በዜግነት ቤልጅየማዊ የሆኑት ረሰሰበጂና በግዳጅ ወደ ርዋንዳ የመመለስ ሥጋት ሳይኖርባቸው በአሜሪካዋ ሳን አንቶኒዮ ይኖሩ ነበር። ቤልጅየምም ሆነች አሜሪካ ስለ እስራቸው በይፋ ያሉት ነገር የለም። ቀድሞም አሳልፈው አልሰጧቸውም። ፊል ክላርክ እንደሚሉት ይኸ ርዋንዳ ከምዕራቡ ያላትን የተወሳሰበ ግንኙነት ይጠቁማል። 

"በርካታ የምዕራብ አገራት በርዋንዳ ጉዳይ የተከፋፈለ አቋም ነው ያላቸው። በርካታ ለጋሾች በርዋንዳ የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ረገድ ሥጋት አላቸው። የተነቃቃ ተቃዋሚ እንዲኖርም ይፈልጋሉ። ቤልጅየም፣ አሜሪካ እና ብሪታኒያን ለመሳሰሉ አገሮች እንደ ረሰሰበጂና ያሉ ሰዎች የሚፈልጉት የተነቃቃ የርዋንዳ ተቃዋሚ ኃይል ሆነው ታይተዋቸዋል። የዛኑ ያክል ለእነዚህ ምዕራባውያን አገሮች እነ ረሰሰበጂና ነፍጥ ለማንሳት እና የርዋንዳን መንግሥት በትጥቅ ትግል ለመጣል የያዙት የከረረ አቋም አሳሳቢ ሆኖባቸዋል። ከዚህ ቀደም ረሰሰበጂናን ማንም ሊያቆማቸው ያልሞከረው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል" ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ።  "የፖለቲካ ንቅናቄያቸው እንዲያብብ፤ በውጭ አገራት በሚኖሩ ርዋንዳውያን ዘንድ አዋጪ የፖለቲካ ተቃዋሚ ኃይል እንዲፈጥሩ ዕድል የመስጠት ሙከራ ይመስላል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በምዕራባውያኑ አቋማቸው እጅግ የከረረ ሆኖ መታየት የጀመረ ይመስላል። በዚህም ምክንያት ባለፉት ቀናት እስራቸውን በማመቻቸት ረገድ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትብብር ታዝበናል" ሲሉ አክለዋል። 

የቀድሞው የሆቴል ባለቤት ከጅምላ ጭፍጨፋ ያገራቸውን ሰዎች ለመታደግ የፈጸሙት ድርጊት በቅርብ ጊዜያት የበረታ ጥያቄ ተነስቶበታል። በሆሊውድ ለተሰራው ፊልም ምስጋና ይድረሰውና በምዕራባውያኑ ዘንድ እንደ ዛሬም እንደ አዳኝ ይቆጠሩ እንጂ "ከ26 አመታት በፊት ከተፈጸመው የጅምላ ፍጅት የተረፉ ጥቂት ሰዎች እና የርዋንዳ መንግሥት ሰውየው ከጥቃት ያዳኗቸውን ክፍያ ጠይቀዋል" እያሉ እንደሚከሱ የዶይቼ ቬለው አሌክስ ንጋራምቤ ይናገራል። 

Ruanda Kigali Paul Rusesabagina nach Festnahme
ፖል ረሰሰበጂና እንዴት ለርዋንዳ መንግሥት ተላልፈው እንደተሰጡ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለምምስል picture-alliance/AP Photo

ተንታኙ ፊል ክላርክ እንደሚሉት ሰውየው የርዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜን መቃወም ከጀመሩ በኋላ በአገራቸው የስም ማጥፋት ዘመቻ ተደርጎባቸዋል። ይህ ብቻ አይደለም። ከ26 አመታት በፊት በተግባር የተፈጸመው ድርጊት እርሳቸው ያገራቸውን ሰዎች ከጅምላ ፍጅት ለመታደግ ፈጸሙት ተብሎ በፊልሙ ከቀረበላቸው ታሪክ የባሰ እጅግ የተወሳሰበ ነው። "ከጅምላ ግድያው የተረፉ እንደሚሉት ረሰሰበጂና በርካታ ቱትሲዎችን ለሑቱ ታጣቂዎች አሳልፈው ሰጥተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሆቴሉ ከተጠለሉ ቱትሲዎች ከለላ ለሰጡበት ክፍያ ጠይቀዋል። ስለዚህ በረሰሰበጂና ከለላ አግኝተው ከጅምላ ግድያው ለተረፉ በፊልሙ እንደቀረቡት ጀግና አይደሉም" የሚሉት ፊል ክላርክ ከጅምላ ግድያው የተረፉ ሰዎችን አነጋግረው ነበር። 

"በሆቴሉ ውስጥ ከነበሩ ሰዎች ጋር ባደረኩት ቃለመጠይቅ የተረዳሁት አንድ ነገር ረሰሰበጂና በፊልሙ እና ባገኙት ዓለም አቀፋዊ ሙገሳ ተጠቅመው የሚል ኮሊን ሆቴልን ታሪክ ለራሳቸው ዝና ጠልፈውታል። ባለፉት ጥቂት አመታት ከጅምላ ግድያው የተረፉ ሰዎች ድምጽ ከፍ ብሎ መሰማቱ እጅግ ዋና ጉዳይ ነው። በዚህም በ1994 ዓ.ም. ረሰሰበጂና ማን እንደነበሩ? በማሳየት ጉዳዩ ምን ያክል ውስብስብ እንደሆነ እንድንረዳ አድርጓል" ይላሉ። 

ይኸ በርዋንዳ ጉዳይ ግራ ለተጋቡት ምዕራባውያን ተጨማሪ ውስብስብ ጉዳይ ሆኗል። ርዋንዳ በአንድ በኩል ከለጋሾች የሚሰጣትን ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል ተስፋ የሚጣልበት ኤኮኖሚያዊ ዕድገት አሳይታለች። አገሪቱ ካለፈችበት አሰቃቂ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ በኋላ ሰላም በማስፈን እና በእርቅ ረገድ አመርቂ እርምጃ ማሳየቷ ሌላው በጎ ጎን እንደሆነ ፊል ክላርክ ይናገራሉ።  በሌላ በኩል እንደ ክላርክ አባባል "ላለፉት አስር እና አስራ አምስት አመታት ርዋንዳ ጠንካራ ተቃዋሚ የሌለባት፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የሚገደሉባት እና የሚሰደዱባት አገር" ሆናለች። ምዕራባውያኑ ዕርዳታ ተቀባዮቻቸው ሊብራል ዴሞክራት እንዲሆኑ የተሰጣቸውን ገንዘብም በአግባቡ እንዲጠቀሙ ይሻሉ። በአንድ በኩል ምዕራባውያኑ በአንድ በኩል ያስቀመጧቸውን መስፈርቶች አሟልታ ሌላውን ለምታጎድል አገር ዝግጁ አይመስሉም። 

"ምዕራባውያን ለጋሾች በርዋንዳ የገጠማቸው የሚሰጡትን ገንዘብ በአግባቡ የሚጠቀም ነገር ግን አምባገነን የሆነ መንግሥት ነው። አብዛኞቹ ለጋሾች እነዚህ ተቃራኒ መልኮች የሚያስታርቁበት ሥርዓት የላቸውም። ስለዚህ ርዋንዳ እንዲህ ውስብስብ ሆነ የምዕራባውያን ዲፕሎማቶችን በለሊት ታባንናቸዋለች" ይላሉ ተንታኙ። 
ክሪስቲና ክሪፓል| እሸቴ በቀለ