ጀርመንና ፈረንሳይ ወዳጅነት ውል ፈረሙ
ማክሰኞ፣ ጥር 14 2011የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ አዲስ የጀርመን እና ፈረንሳይ ወዳጅነት ውል ተፈራረሙ። ሁለቱ መሪዎች ዛሬ በጀርመን የአኸን ከተማ የተፈራረሙት ውል ጀርመን እና ፈረንሳይ በጎርጎሪዮሳዊው 1963 ዓም የተፈራረሙትን በግንኙነታቸው ላይ ቁልፍ ሚና የተጫወተውን የኤሊዜ ስምምነትን የሚያጠናክር እንደሆን ተገልጿል። ሜርክል እና ማክሮ አገሮቻቸውን በሚያዋስነው 450 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው ድንበራቸው የሚካሄደውን የጋራ ትብብር ማሳደግ ፍላጎት አላቸው። በተለይም፣ የአየር ንብረት ለውጥን እና ሽብርተኝ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለመታገል የሚደረገውን ጥረት በተሻለ መንገድ ማስተባበር እንደሚሹ ሜርክል በፍረማው ስነ ስርዓት ላይ ተናግረል።
« የብዙ ወገኖች ትብብር፣ ብሎም፣ የአየር ንብረት ለውጥን መታገልንም ሆነ፣ የዓለም ንግድ ትብብርን ወይም የተመድን ጨምሮ ለዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና መስጠትን የመሳሰለው ጥረት ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግፊት አርፎበታል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከ74 ዓመት፣ ማለትም ከአንድ ሰው እድሜ በኋላ ካሁን በፊት ተቀባይነት አግኝተው የነበሩ ኩነቶች ዛሬ ጥያቄ ውስጥ ገብተዋል። ይህ በመሆኑም፣ አንደኛ፣ በአውሮጳ ህብረት ውስጥ ጀርመን እና ፈረንሳይ የያዙትን ኃላፊነት እንደአዲስ መመልከት አለብን። ስለዚህ፣ ሁለተኛ የትብብራችንን አቅጣጫ እንዳዲስ መለየት ይገባናል። ሶስተኛ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጋራ ርምጃ መውሰድ በሚያስችለን የጋራ ሚና ላይ መግባባት ላይ መድረስ ይኖርብናል።»
አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ