1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ናሚቢያ ዉስጥ የዘር ማጥፋት መፈጸሟን ማመኗ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 24 2013

አመጹን እንዲቆጣጠር የተላከው የጀርመን ጀነራል ሎታር ፎን ትሮታ ለወታደሮቹ ትዕዛዝ የሰጠው ሰዎቹን እንዲያጠፉ ነበር።በታሪክ ምሁራን ግምት ቢያንስ 60 ሺህ ሄሬሮዎችና ቁጥራቸው 10ሺህ የሚጠጋ ናማዎች ከ1904 እስከ 1908 ተገድለዋል።የቅኝ ገዥዋ የጀርመን ወታደሮች ጅምላ ጭፍጨፋ በማካሄድ ሴቶችና ህጻናት ወደ በረሃው እንዲሸሹ አደረጉ።

https://p.dw.com/p/3uJPt
Namibia, Windhuk I Denkmal zur Erinnerung an den Völkermord von Herero und Nama
ምስል Jürgen Bätz/dpa/picture alliance

ጀርመን ናሚቢያ ዉስጥ የዘር ማጥፋት መፈጸሟን ማመኗ

ጀርመን ናምቢያን ቅኝ በገዛችበት ዘመን የዘር ማጥፋት መፈጸሟን ባለፈው ሳምንት በይፋ አምናለች። ናሚቢያን ለመካስም ቃል ገብታለች። እርምጃው በናሚብያ መንግሥት ተቀባይነት አግኝቷል። የዘር ማጥፋት የተፈጸመባቸው ሰዎች ዝርያዎች ግን ተቃውመውታል። «ዛሬ እነዚህን ድርጊቶችም የዘር ማጥፋት ብለን በይፋ እንጠራቸዋለን። ይህን በማድረጋችን ለታሪካዊ ሃላፊነታችንም እውቅና እንሰጣለን። »

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ፣ጀርመን ናምብያን ቅኝ በገዛችበት ዘመን በብዙ ሺህዎች በሚቆጠሩ ናሚብያውያን ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ የዘር ማጥፋት ሲሉ ያመኑበት መግለጫቸው ነበር። ማስ ባለፈው ሐሙስ በሰጡት መግለጫ ጀርመን ከጎርጎሮሳዊው 1884 እስከ 1915 ናሚብያን ቅኝ በገዛችበት ወቅት በናምብያውያን ላይ የተፈጸመውን የግፍ ግድያ፣የዘር ማጥፋት ስትል ከማመኗም በተጨማሪ  ለድርጊቱም ይቅርታ ጠይቃለች።ያኔ በግፍ ለተገደሉት ሰዎች ዝርያዎችም በቢሊዮን ዩሮ የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠትም ቃል ገብታለች።

«ከጀርመን ታሪካዊና የሞራል ሃላፊነት በመነሳት፣ የናሚብያን ህዝብና የድርጊቱ ሰለባዎችን ዝርያዎች ይቅርታ እንጠይቃለን። በሰለባዎች ላይ ለደረሰው መጠኑ ለማይለካ በደል እውቅና በመስጠት በአመዛኙ ለናሚብያና ለሰለባዎች ዝርያዎች፣ለግንባታና ለልማት መርሃ ግብሮች የሚውል አንድ ቢሊዮን አንድ መቶ ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ እንሰጣለን።»

Deutschland | Namibia | Aussöhnungsabkommen | Bundesaußenminister Heiko Maas
ምስል Tobias Schwarz/AP Photo/picture alliance

ይህ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዩሮ  ወይም  ሦስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላርም በ30 ዓመታት ውስጥ እንደሚከፈል፣ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎቹም ግፉ የተፈጸመባቸው  የሄሬሮና የናማ ህዝቦች ዝርያዎች መሆን እንዳለባቸው ስምምነት ላይ መደረሱን  ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው ተናግረዋል።ይህን የጀርመንን  ውሳኔ የናሚብያ መንግሥት አወድሷል። የናሚብያው ፕሬዝዳንት ሃጌ ጋይንጎብ ቃል አቀባይ አልፍሬዶ  ሄንጋሪ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በሰጡት ቃለ ምልልስ «ጀርመን የዘር ማጥፋት መፈጸሙን መቀበሏን በትክክለኛው አቅጣጫ የወሰደችው የመጀመሪያው እርምጃ ብለውታል።የሁለተኛው እርምጃ ማለትም የይቅርታው መሰረት ሲሆን ከዚያ ካሳ ይከተላል ሲሉም አክለዋል።ጀርመን የናሚብያን የቅኝ ግዛት ዘመን ጭፈጨፋ የዘር ማጥፋት ስትል ተቀብላ ይቅርታ ለጠየቀችበትና ሃላፊነቱን ለወሰደችበት ለዚህ ድርጊት እውቅና የሰጠችው የናሚብያና የጀርመን መንግሥታት ካካሄዱት ከአምስት ዓመታት በላይ ከወሰደ ድርድር በኋላ ነው።የጀርመን ቅን ገዥ ወራሪዎች በተለይ ከጎርጎሮሳዊው 1904 እስከ 1908 በአስር ሺህዎች የተቆጠሩ የሄሬሮና የናማ ጎሳዎችን ገድለዋል።ይህንንም የታሪክ ምሁራን የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲሉ ሰይመውታል። ጀርመን ናሚብያን ቅኝ በገዛችበት ዘመን፣ ናሚቢያ« ጀርመን ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ»ተብላ ነበር የምትጠራው።ያኔ በተለይም ከብቶቻቸውንና መሪታቸውን የተነጠቁት ናሚብያውያኑ የሄሮሮ ጎሳ አባላት፣በ1904 ለአመጽ ሲነሱ የናማ ጎሳ አባላትም ተቀላቀሏቸው። የጀርመን ቅኝ ገዥ ወታደሮች አመጹን በግፍ እርምጃ ተቆጣጠሩት። በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 1904 በዋተርበርጉ ውጊያ ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ  ቁጥራቸው 80 ሺህ የሚጠጋ ሄሬሮዎች ከመኖሪያቸው ሲሸሹ የጀርመን ወታደሮች በያኔው አጠራር ካላሃሪ እስከሚባለው በረሃ ድረስ አሳደው ካጠቋቸው በኋላ የተረፉት 15 ሺህ ብቻ ናቸው። አመጹን እንዲቆጣጠር የተላከው የጀርመን ጀነራል ሎታር ፎን ትሮታ ለወታደሮቹ ትዕዛዝ የሰጠው ሰዎቹን እንዲያጠፉ ነበር። በታሪክ ምሁራን ግምት ቢያንስ 60 ሺህ ሄሬሮዎችና ቁጥራቸው 10ሺህ የሚጠጋ ናማዎች ከጎርጎሮሳዊው 1904 እስከ 1908 ተገድለዋል።ቅኝ ገዥዋ የጀርመን ወታደሮች ጅምላ ጭፍጨፋ በማካሄድ ሴቶችና ህጻናት ወደ በረሃው እንዲሸሹ አደረጉ።በዚያም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በውኃ ጥም አለቁ።ከዚህ ሌላ ብዙም ያልተነገረላቸው የሰዎች ማጎሪያ ስፍራዎችንም መስርተው ነበር።ከመካከላቸው አንዱ ሻርክ በተባለው ደሴት ይገኛል። በወቅቱ የሄሬሮና የናማ ጎሳ አባላትን አጽሞች ስለ«ሰው ልጅ አመጣጥ»ለሚደረገው ጥናት በሚል ሰበብና ሌሎች ንብረቶች ተሰርቀው ወደ ሀገርዋ ተወስደዋል።ናሚብያ ከዚያ በኋላ ለ75 ዓመታት በደቡብ አፍሪቃ ስር ቆይታ በጎርጎሮሳዊው 1990 የዛሬ 31 ዓመት ነጻነትዋን ተጎናፀፈች።ያኔ የተፈጸመው ግፍ ግን የናሚቢያንንና የጀርመንን ግንኙነት ለምዕተ ዓመታት አጠልሽቶት ቆይቷል።ጀርመን ለተፈጸመው ግፍ ይቅርታ እንድትጠይቅ ድርድሮች የተጀመሩት በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም ነበር።በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓም ከመቶ ዓመት በፊት ጀርመን ከናሚብያ የወሰደቻቸውን የሄሬሮና የናማዎች አፅሞች ስትመልስ የጀርመን የዓለም አቀፍ የባህል ፖሊሲ ሚኒስትር ሚሼል ሙንተርፌሪንግ «ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ ብለው ነበር። »   

Illustration | Hauptmann Franke Im Kampf Gegen Die Hereros
ምስል picture-alliance/Heritage-Images/The Print Collector

የዘር ማጥፋት ሰለባ ናሚብያውያን ዝርያዎችና ናሚብያውያን የፖለቲካ አራማጆች አሁን ጀርመን እሰጣለሁ ያለችው ገንዘቡ በቂ አይደለም ሲሉ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። ከመካከላቸው የናሚብያ የዘር ማጥፋት ማኅበር ሊቀ መንበር ሌይድሎው ፔሪንጋንዳ አንዱ ናቸው።

«የጀርመን መንግሥት ወደ ቀልቡ ተመልሶ ከ1904 እስከ 1908 የፈጸመው የዘር ማጥፋት ነው ሲል እውቅና በመስጠቱ በጣም ተደስቻለሁ። በአሁኑ ጊዜ የጀርመን መንግሥት ለዘር ማጥፋት ሰለባዎች ማኅበረሰብ እሰጣለሁ ባለው የገንዘብ መጠን ግን ደስተኛ አይደለንም። ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው  ከናሚቢያ ለገበያ የሚቀርቡ ሰብሎች የሚመረቱበት  መሬት በአናሳዎቹ ናምቢያውያን ፣ነጭ ጀርመናውያን ቁጥጥር ስር ነው።በኛ እምነት ለዚህ መሬት ሊከፈለን ወይም መሬቱን የጀርመን መንግሥት ሊገዛው ይገባል ።»

Deutschland Gedenkgottesdienst in Berlin für die Opfer des Völkermordes in Namibia
ምስል Imago/epd

በናሚብያ የሄሬሮ ጎሳ መሪ ደግሞ በስምምነቱ መንግሥት ዋነኛው አካል መሆኑን ተችተዋል።ጀርመንና ናሚብያው ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ አራማጅ ቡድኖች ጀርመን ቀጥተኛ ካሳ ባለመስጠቷ ስምምነቱን አልተቀበሉም። መሠረቱን ጀርመን ያደረገው «በርሊን ፖስት ኮሎንያል» የተባለው ቡድን ስምምነቱን ዋጋ ቢስ ብሎታል።ባለፈው አርብ ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ያደራጀው ይኽው ቡድን እንደሚለው በድርድሮቹ ሂደት ከሄሬሮና የናማ ማኅበረሰብ ጋር በቂ ምክክር አልተደረገም።

እስራኤል ካውናትጂኬ የሄሬሮ ዝርያ ያላቸው የጉዳዩ አራማጅ ናቸው።

«እውቅና እንጠብቃለን። ይቅርታ ከዚያ በኋላ ስለ ካሳ መነጋገር አለብን።ይህን ያህል የምንለው ቁጥር የለንም ።ሆኖም ይህ ከናሚቢያ መንግሥትና የሄሬሮዎች ተወካዮች ተብለው ከተሾሙ ሰዎች  ጋር ሳይሆን ከኛ ጋር በቀጥታ ልንደራደርበት የሚገባ ጉዳይ ነው።ይህ ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም።»

ሌላዋ ተቃዋሚ ፋቱ ሲላህ ደግሞ የተፈጸመው ዘር ማጥፋት መሆኑን እውቅና መስጠቱ መጀመሪያው እንጂ መጨረሻው አይደለም ስትል አሳስባለች።

Namibia Windhoek | Proteste | Kolonialverbrechen
ምስል Sonja Smith/AP Photo/picture alliance

«እኛ እዚህ የምንገኘው ስምምነቱ በቂ ስላልሆነ ነው።ለዘር ማጥፋት እንዲህ ያለ እውቅና መስጠት መጀመሪያ ብቻ ነው።የዘር ማጥፋት መዘዞች ሊከተሉ ይገባል።»

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ በበኩላቸው ጀርመን ድርጊቱን የዘር ማጥፋት ስትል እውቅና የሰጠችበትን ዓላማ አሳውቀዋል።

«ግባችን ለሰለባዎቹ  መታሰቢያነት ወደ ከልብ ወደ መነጨ እርቅ የሚወስድ መንገድ መፈለግ ነው። ይህ በዛሬይቱ ናሚብያ በቅኝ ግዛት ዘመን ለተፈጸሙት እውቅና የመስጠትና በተለይ ከ1904 እስከ 1908 የተፈጸሙትን ግፎች በግልጽ የማስቀመጥ አካል ነው።ዛሬ በይፋ ያኔ የተፈጸሙትን የዘር ማጥፋት ስንል የጠራናቸው።»

ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የሁለቱም ሃገራት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ስምምነቱን ማጽደቅ አለባቸው ከስድስት ዓመታት ድርድር በኋላ የተደረሰበት የዚህ ስምምነት  ሰነድም  ዊንድሆክ ናሚብያ ውስጥ በሁለቱ ሃገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰኔ ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል። የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርም በናሚብያ ፓርላማ ተገኝተው በይፋ ይቅርታ ሊጠይቁ ይችላሉ ተብሏል።ይሁንና የስምምነቱ ተቃዋሚዎች ሽታይንማየርን እዚህ አይምጡ አንፈልግዎትም ብለዋቸዋል።

«ሚስተር ሽታይንማየር በናሚብያ አይፈለጉም አንቀበልዎትም»

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ