1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ግማሽ ቢሊዮን ይሮ ሰጠች

ዓርብ፣ ሰኔ 19 2012

ጀርመን ለዓለሙ የጤና ድርጅት /WHO/ በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን 2020 ዓመት ግማሽ ቢሊዮን ይሮ መስጠትዋን አሳወቅች።  የጀርመን የጤና ሚኒስትር የንስ ሽፓን WHO ዤኔቭ ላይ በነበረዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ጀርመን ለዓለም የጤና ድርጅት 500 ሚሊዮን ይሮ ሰጣለች ፤ ከዚህ ገንዘብ መካከል 200 ሚሊዮን ስራ ላይ ዉሎአል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3ePTT
Schweiz Jens Spahn und Tedros Adhanom Ghebreyesus
ምስል Getty Images/AFP/F. Coffrini

ጀርመን ለዓለሙ የጤና ድርጅት /WHO/ በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን 2020 ዓመት ግማሽ ቢሊዮን ይሮ መስጠትዋን አሳወቅች።  የጀርመን የጤና ሚኒስትር የንስ ሽፓን የዓለም የጤና ድርጅት ዤኔቭ ላይ በነበረዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ጀርመን ለዓለም የጤና ድርጅት 500 ሚሊዮን ይሮ ሰጣለች ፤ ከዚህ ገንዘብ መካከል 200 ሚሊዮን ስራ ላይ ዉሎአል ብለዋል። ሚኒስትሩ  ሃገራቸዉ ለዓለሙ ጤና ድርጅት ጠንካራ ደጋፊና ወዳጅ ሆና እንደምትዘልቅም ተናግረዋል።  ጀርመን ለWHO ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ስትሰጥ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ፤ 
« ጀርመን የ WHO ጠንካራ ደጋፊና ወዳጅ ሆና ትቀጥላለች። አንዳንድ ጊዜም ከፍተኛ ትችት አቅራቢ ወዳጅ ግን ለ WHO ጠንካራ ወዳጅ ሃገር ናት። በዓለም ላይ አሁንም እየታየ ያለዉ ወረርሽኝ የሚያመለክተዉ የዓለም አንድነትን እና ቀዉሱን  በዓለም አቀፍ ደረጃ መቋቋም እንደሚያስፈልግ ነዉ። ስለዚህም ዛሬ ከመቼዉም ጊዜ ይበልጥ ጠንካራ ብቃት ያለዉ እንዲሁም ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለዉን WHOን እንፈልጋለን። »

የጀርመኑ የጤና ሚኒስቴር ሃገራቸዉ ከሰጠችዉ 500 ሚሊዮን ይሮ መካከል 200 ሚሊዮኑ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከአንድንድ ሃገራት ለድርጅቱ ባልተደረጉ ክፍያዎች ምክንያት ለተከሰቱ የተለያዩ ክፍተቶች መዋሉን ተናግረዋል። ሚኒስትሩ ይህን ማለታቸዉ የኮሮና ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ከWHO ጋር የነበራትን ግንኙነት ማለዘብዋን አስመልክቶ ነዉ።  የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዮድሮስ አድሃኖም በበኩላቸዉ ጀርመን ላደረገችዉ ድጋፍ ምስጋናን አቅርበዋል። 

« እንደተነገረዉ ባለዉ ዛሬ ድርጅታችን ፖለቲካዊም ሆነ የፊናንስ ድጋፍን እያገኘ ነዉ ። ለዚህም ታላቅ አክብሮቴን መግለፅ እወዳለሁ።  በዓለም እንደታየዉ ሁሉ ኮቪድ 19  በመቶ ዓመት አንድ ጊዜ የሚከሰት ዓይነት ወረርሺኝ ሲሆን ይሁንና ዓለማችን መዘጋጀት በነበረበት ሁኔታ አለመዘጋጀቱን ያየንበት ነዉ። ከዚህ ትምህርት መዉሰድና ሁላችንም ደህና ካልሆንን ማንናችንም ከወረርሽኙ የተጠበቅን አለመሆናችንን መረዳት ይኖርብናል። »

በዓለም የተለያዩ የዜና አገልግሎቶች ከፍተኛ ትችት የተሰነዘረባት ዩናይትድ ስቴትስ ለዓለሙ የጤና ድርጅት መስጠት የሚገባትን የፋይናንስ እና ፖለቲካዊ ድጋፎች ለድርጅቱ እየሰጠች መሆንዋን ዶ/ር ቴዮድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል። 

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ