1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶላር በአርባ ብር

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 28 2013

በኢትዮጵያ ባንኮች ካለፈው ሰኞ ጀምሮ አንድ የአሜሪካ ዶላር ምንዛሪ ከአርባ ብር በላይ ከፍ ብሏል። የምንዛሪ ተመኑ 40 ብር የደረሰው በየዕለቱ ሽርፍራፊ ሳንቲሞች እየጨመረ ነው። የመንግሥት እርምጃ በተለምዶ ጥቁር ተብሎ በሚጠራው የጎንዮሽ ግብይት እና በባንኮች በሚከወነው ምንዛሪ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ጭምር ያቀደ ቢሆንም አልተሳካም

https://p.dw.com/p/3nawa
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ከኤኮኖሚው ዓለም ፦ ዶላር በአርባ ብር

የዛሬ አመት ታኅሳስ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ባንኮች በ31 ብር ከ85 ሳንቲም ገደማ የሚገዙትን አንድ የአሜሪካ ዶላር 32 ብር ከ50 ሳንቲም ገደማ መልሰው ይሸጡ ነበር። ልክ በአመቱ ብር በባንኮች ግብይት ከዶላር አኳያ የነበረው የምንዛሪ ተመን እጅግ ተዳክሟል። ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የአንድ ዶላር የምዛሪ ተመን ከ40 ብር በላይ ከፍ ብሏል።

ይኸ ግብይቱን በቅርበት ለሚከታተሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ እንግዳ ነገር አልሆነም። "የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በ2019 መጨረሻ በገባው ውል አንደኛው ቅድመ ሁኔታ በሒደት የውጭ ምንዛሪ [እጥረትን] ጉዳይ በቋሚነት መፍታት የሚለው እንደ አማራጭ ተቀምጧል። አንደኛው መንገድ እንደዚህ በሒደት የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ነው። እርምጃው የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ከሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ጋር ያስቀመጡልን ነው። ብር ከእነሱ ስናገኝ ይኸንን መተግበር አለብን" የሚሉት አቶ አብዱልመናን ሥምምነቱ ከተፈጸመ አንስቶ "የኢትዮጵያ መንግሥት ብርን ቀስ በቀስ ማዳከም እንደጀመረ" ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ገቢራዊ ስታደርግ የዓለም የገንዘብ ድርጅት 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ተስማምቷል። በዚህ ሥምምነት መሠረት የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት መፍታት እና በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መዘርጋት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከዓለም የገንዘብ ድርጅት በገባው ውል ከተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ብር ከዶላር አኳያ ያለውን የምንዛሪ ተመን ከፍ ባለ መጠን ማዳከሟን ዶክተር ቢኒያም በዳሶ ያስታውሳሉ። በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ የበጀት ማሻሻያ ኢንሺየቲቭ የጥናት ዘርፍን በኃላፊነት የሚመሩት ዶክተር ቢያኒያም "የብር ዋጋ ሲቀንስ፤ የዶላር ዋጋ ሲወደድ አገር ውስጥ ይሸጥ የነበረ ሰው ምርቱን ወደ ውጪ ልኮ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ያመጣል" በሚል ስሌት ብርን የማዳከም እርምጃ እንደሚወሰድ ይናገራሉ።

"በሚያሳዝን ሁኔታ ያ ወደ እውነታ ሲለወጥ አልታየም" የሚሉት  ዶክተር ቢኒያም "በኤኮኖሚው ላይ ሊያመጣ የሚችለው ትልቁ ተፅዕኖ ከሸማቹ አንፃር የዋጋ ግሽበት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ነው። ከዚያም አልፎ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ የተበደረው ብድር አለ። ያንን በኢትዮጵያ ገንዘብ ግብር ሰብስቦ ወደ ውጭ ምንዛሪ ለውጦ መክፈል ይኖርበታል። ስለዚህ የመንግሥት ዕዳ በኢትዮጵያ ብር ሲታሰብ ይጨምራል" ሲሉ ዳፋው የውጭ አገራት ብድር ያጎበጠው መንግሥትም እንደማይቀርለት አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ባንኮች ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን አሁን ካለበት ደረጃ ሲደርስ በየዕለቱ ሽርፍራፊ ሳንቲሞች እየጨመረ በሒደት ነው።  ብር ከዶላር አንፃር የነበረውን ተመን ከአስር አመታት ገደማ በፊት በ17 ከመቶ ሲዳከም በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ወደ 40 በመቶ ገደማ የዋጋ ግሽበት ፈጥሮ ነበር። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ መንግሥት አሁን የተከተለው ስልት ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ዘገምተኛ በሆነ ፍጥነት ሲጨምር በገበያው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ "አይስተዋልም" ከሚል መነሾ እንደሆነ ይናገራሉ።

Äthiopien |Äthiopischer Händler auf einem traditionellen Markt in Debre Markos
ብር እየተዳከመ ሲሔድ ኢትዮጵያ ከውጭ ገበያ የምትሸምታቸው ሸቀጦች ዋጋ ይጨምራል፤ መንግሥት ከውጭ የተበደረው ገንዘብም ይንራል። ምስል DW/E. Bekele

"ብር በከፍተኛ መጠን ሲዳከም ገበያ ላይ የሚፈጥረው ከባድ ተፅዕኖ አለ። መንግሥት ያንን አይነት አካሔድ አልፈለገም። በጥቁር እና በይፋዊው ግብይት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ቀስ እያሉ ብርን ማዳከም አይስተዋልም። ገበያም ላይ እንደበፊቶቹ ከባድ ተፅዕኖ አይፈጥርም ከሚል እሳቤ ነው።  አንዴም ተደረገ ቀስ እያለም ተደረገ ገበያ ላይ የሚፈጥረው ተመሳሳይ ውጤት ነው" የሚሉት አቶ አብዱልመናን ብር ተዳክሞ ዶላር ሲወደድ የኢትዮጵያ ሸቀጦችን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎችን ያበረታታል፤ አገሪቱም ከዓለም ገበያ የምትሸምታቸውን ሸቀጦች ይቀንሳል የሚለው ስሌት ለመሥራቱ ግን ጥርጣሬ አላቸው።

"የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ የተመን ችግር ብቻ አይደለም ያለበት። ከአቅርቦት፣ ከሎጂስቲክስ ከሙስና ጋር በተያያዘ ሌሎች ብዙ የተተበተቡበት ችግሮች አሉ። ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ የምታስገባቸው ደግሞ 90 በመቶው ነዳጅ፣ መድሐኒት የሕፃናት ምግብን የመሳሰሉ የምንፈልጋቸው ስትራቴጂክ ሸቀጦች ናቸው። ችግሩ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዋጋ ሲጨመር ዞሮ የውጭ ንግድ ላይ ይመጣል። በውጭ ንግድ የተሰማራው ነጋዴ እንደ ግብዓት የሚጠቀመው ዕቃ ውድ ይሆንበታል" የሚሉት አቶ አብዱልመናን "የአገሪቱ የወጪ ንግድ ማነቆ የሆኑበትን መፍታት ነው የሚሻለው" ሲሉ ይመክራሉ።

ኢትዮጵያ ለረዥም አመታት የተከተለችው የውጭ ምንዛሪ ግብይት እና ዝውውር ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ነበር። ዶክተር ቢኒያም እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የነበረው የውጭ ግብይት ሥርዓት "ያመጣው ነገር ቢኖር በጎንዮሽ ያሉ ኪራይ የሚሰበስቡትን ሰዎች ማበልጸግ እና በተለያዩ ዘርፎች ነጋዴዎች እና አምራቾች መሐል ያለውን የምንዛሪ ክፍፍል ማዛባት ነው።"

Äthiopien Omo Kuraz Zuckerfabrik
የስኳር ፋብሪካዎችን ጨምሮ ልማታዊው መንግሥት የጀመራቸው ግዙፍ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይፈታል የሚል እምነት የመንግሥት ባለሥልጣናት ነበራቸውምስል Ethiopian Sugar Corporation

"ልማታዊ" የነበረው መግሥት ይከተል የነበረው የግብይት ሥርዓት የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እና አምራቾች አቅም እስኪያዳብሩ ጊዜ መግዣ አድርጎ ያቀርበው ነበር። የታቀደው አለመሳካቱ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲን ለሚተቹ እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ላሉ ተቋማት "የበለጠ ማስረጃ" እንደሆነላቸው ዶክተር ቢኒያም አስረድተዋል።

ባለፉት አመታት ግብይቱ በገበያው አቅርቦት እና ፍላጎት እንዲመራ የማድረግ ፍላጎት እንዳለ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጠቁመዋል። ዶክተር ቢኒያም እንደሚሉት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ የመከሩት መፍትሔ ፈታኝ ቢሆንም ወደ ቀደመው የግብይት ሥልት መመለስ ግን እንደማያዋጣ ይናገራሉ።

ዶላር የተራበው የኢትዮጵያ ገበያ

በተለምዶ ጥቁር እየተባለ በሚጠራው በጎንዮሹ ገበያ የአሜሪካው ዶላር የሚመነዘርበት ተመን ከቦታ ቦታ ቢለያይም ከባንክ ግብይቱ የመቀራረብ ምልክት እያሳየ አይደለም። ዶይቼ ቬለ ባደረገው ማጣራት በአዲስ አበባው የጎንዮሽ ገበያ ባለፈው ሳምንት አንድ የአሜሪካ ዶላር ከ51 እስከ 56 ብር ሲመነዘር እንደነበር ለመረዳት ችሏል። በሁለቱ ግብይቶች መካከል ያለው ልዩነት መንግሥት እንዳቀደው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም እንደጠቆሙት ብር ሲዳከም ሲጠብ አልታየም።

በአዲስ አበባ ገበያ ኢትዮጵያ ከውጭ የምተሸምታቸው እቃዎች ዋጋ በየዕለቱ ጭማሪ በማሳየት ላይ እንደሚገኝ በግብይቱ የሚሳተፉ ግለሰቦችን በማነጋገር ዶይቼ ቬለ ለመረዳት ችሏል። በተለይ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች እና የግንባታ ዕቃዎች በቀናት ልዩነት የዋጋ ልዩነት ያሳያሉ ከተባሉት መካከል ይገኙበታል። ኢትዮጵያ ወትሮም የውጭ ምንዛሪ ክምችቷ በቂ እንዳልሆነ የሚያስታውሱት ዶክተር ቢኒያም አገሪቱ አሁንም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ዕገዛ ሊያሻት እንደሚችል ያስረዳሉ።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ