የዶ/ር መረራ ጉዲና የፍርድ ቤት ውሎ
ሐሙስ፣ ጥር 18 2009በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ጠበቆች ዛሬ ታኅሳስ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሆኗል። አንድ ተጠርጣሪ የዋስትና መብት የሚከለከለው ማስረጃዎች ያጠፋል፤ ምስክሮችን ያባብላል፤ ወንጀል ይፈፅማል አሊያም ከሐገር ይኮበልላል የሚል ሥጋት ሲኖር ብቻ ነው ይላሉ ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም። ዶ/ር መረራ ከእነዚህ ስጋቶች ነፃ ናቸው በሚል እምነት ዋስትና መጠየቃቸውን ተናግረዋል። ጠበቃው ከምርመራ በኋላ ክስ በይፋ ሲመሰረት በድጋሚ ዋስትና እንደሚጠይቁም ተናግረዋል። ጠበቆቹ ተጠርጣሪው ወደ ሁለት ወር ገደማ በመታሰራቸው ክርክሩ እንዲጀመር ያቀረቡትንም ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል።
ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ደንበኛቸውን በሳምንት ሁለት ቀናት (ረቡዕ እና ዓርብ) ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል። ዶ/ር መረራ ጉዲና አሁንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት አልተፈቀደላቸውም። የዶ/ር መረራ ጉዲና የምርመራ ሒደት እስከ አራት ወራት ሊዘልቅ ቢችልም ጠበቃቸው በድጋሚ ተቃውሟቸውን እንደሚገልጡ ተናግረዋል። መርማሪ ፖሊስ በተደጋጋሚ ሌላ ቀነ-ቀጠሮ ሊጠይቅ ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ዶ/ር ያዕቆብ መረጃ የማሰባሰቡ ሒደት እስካሁን መጠናቀቅ ነበረበት ብለዋል። ዛሬ ያስቻለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የዶ/ር መረራ ጉዲናን ጉዳይ ለመጪው የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል።
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ