1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድርድር

ሰኞ፣ ጥቅምት 14 2015

በሁለት ዓመቱ ጦርነት የዩናይትድ ስቴትስ፣የብሪታንያ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን አቋም፣ግፊትና ጫና በጥርጣሬ የሚመለከተዉ ኢትዮያዊና ትዉልደ ኢትዮጵያዊ የአርቡን ጥሪም ብዙ አልፈቀደዉም።

https://p.dw.com/p/4IcdK
Äthiopien Soldaten in Mekelle
ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የኃይል ሚዛን ለዉጥና ድርድር

ሰሜን ኢትዮጵያን የሚያወድመዉ ጦርነት ሁለት ዓመት ሊደፍን 10 ቀን ቀረዉ።በሳምንቱ ማብቂያ በተደረገዉ ዉጊያ የኢትዮጵያ መንግስትና ተባባሪዎቹ ኃይላት ጥንታዊ-ታሪካዊቱን አድዋን ጨምሮ የትግራይ ክልልን ትላልቅ ስልታዊ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።ለኢትዮጵያ መንግስት ታላቅ ድል።ለሕወሓት ከፍተኛ ሽንፈት።የሳምንቱ ማብቂያ የሰላም ተስፋ ቃል፣ የዲፕሎማቶች ጫና፣የኃይማኖት መሪዎች ተማፅዕኖ፣ የአደባባይ ሰልፈኞች ተቃዉሞ፣ የድርድር ተስፋና ዝግጅት የተጠናከረበትም ነበር።ሳምንቱ በሌላ ሳምንት ሲተካ ዛሬ የፈደራሉ መንግስትና የሕወሓት መልዕክተኞች ለመነጋገር ደቡብ አፍሪቃ መግባታቸዉ ተዘግቧል።ዉጊያ ከተጀመረ ወዲሕ የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች በይፋ ፊትለፊት ሲገናኙ ያሁኑ የመጀመሪያቸዉ ነዉ።ድል፣ሽንፈት፣ቃል፣ ጫና ዉግዘት ፀሎቱ ሰላም ያሰፍኑ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ

ሶስቱ አደራዳሪዎች
ሶስቱ አደራዳሪዎች

                        

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ (ጥቅምት 10፣2015) ቡራዩ ነበሩ።«ቡራዩ በጣም ታሪክ ጠገብ  አካባቢ መሆንዋን ተገንዝበን እዚሕ የምትመጡ ወደ ትክክለኛ መናገሻችሁ እየመጣችሁ መሆኑን ማወቅ አለባችሁ»

በርግጥም ርዕሰ-ከተማ አዲስ አበባን በስተሰሜን ምዕራብ የምታዋስነዉ ትንሹቱ የኦሮሚያ ከተማ ለበጎ ይሁን ለመጥፎ ታሪካዊ ናት።የዛሬ አራት ዓመት ግድም ያቺን ትንሽ ከተማ በደም ያጨቀየዉ የዘር ተዉሳክ ግን ለነባሩ ታሪኳ ትልቅ ጉድፍ፣ለመጪ ተስፋዋ አስጊ ደንቃራ ላለመሆኑ ማረጋገጪያ ምጥፋቱ ነዉ ጭንቁ።

መስከረም 2011 በከተማይቱ ነዋሪዎች በተለይም በጋሞ ተወላጆች ላይ የዘመቱ የኦሮሞ ወጣቶች በትንሽ ግምት 23 ገደሉ።500 አቆሰሉ።15 ሺሕ አፈናቀሉ።

መዘዙ አርባ ምንጭ ድረስ አስተጋብቶ በጋሞ የሐገር ሽማግሌዎች ብልሐት፣ጥበብና ተማፅዕኖ ረገበ እንጂ  ተጨማሪ አስከሬን፣ቁስለኛ ተፈናቃይ በቆጠርን ነበር።ወንጀለኞች ተቀጥተዉ፣ የሟች ቤተሰቦችና ሰለቦች ተክሰዉ ይሆን? አናዉቅም።

የምናዉቀዉ ቡራዩ ከአራት ዓመት በኋላ ባለፈዉ ሐሙስ  ምናልባት የመላዉ ኢትዮጵያን የቅርብ ዘመን ታሪክ የሚቀይር ታሪካዊ ቃል የተሰማባት መሆኑን ነዉ።የአንድነት ጥሪ፣የሰላም ተስፋ።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ።

«ተባብረን እንስራ።አንድ እንሁን በዘር አንከፋፈል-----በሰሜን ኢትዮጵያ ያለዉም ነገር ይቋጫል።ሠላም ይሆናል።ኢትዮጵያ ሰላም ትሆናለች።እንዲሁ እንደተዋጋን አንቀጥልም።በሰላም በልማት የትግራይ ወንድሞቻችንን ለማልማት በጋራ የምንቆምበት ጊዜ ቅርብ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።»በሌላ ሰፊ ንግግር ማብቂያ የተሰማዉ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መልዕክት ትክክለኛ ይዘት፣ የበጎ ጥሪዉ ገቢራዊነት አነጋግሮ ሳያበቃ ከኒዮርክ ሌላ ጥሪ ተሰማ።አርብ።በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ።

ተቃዉሞ ሰልፈኞች
ተቃዉሞ ሰልፈኞችምስል AFP

                           

«በሁለት ዓመቱ ግጭት ግማሽ ሚሊዮን ያክል ሰዉ ሞቷል።ሌላ ተጨማሪ የጅምላ ግፍ ይፈፀማል የሚለዉ ግምት ዩናይትድ ስቴትስን በጣም አሳስቧታል።ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል።አሁን ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንደነገርኩት ሁሉም ወገኖች ጠመንጃቸዉን አስቀምጠዉ ወደ ሰላም የሚመለሱበት ጊዜ ዘግይቷል።ዉጊያ የሚቆምበትና ለችግረኞች ያለምንም ገደብ የሰብአዊ ርዳታ የሚቀርብበት ጊዜ ነዉ።የናንተ የኤርትራ መከላከያ ኃይላት የጋራ ወታደራዊ ጥቃታቸዉን የሚያቆሙበትና ኤርትራ ወታደሮችዋን ከሰሜናዊ ኢትዮጵያ እንድትስወጣ ኢትዮጵያ የምትጠይቅበት ወቅት ነዉ።»

በሁለት ዓመቱ ጦርነት የዩናይትድ ስቴትስ፣የብሪታንያ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን አቋም፣ግፊትና ጫና በጥርጣሬ የሚመለከተዉ ኢትዮያዊና ትዉልደ ኢትዮጵያዊ የአርቡን ጥሪም ብዙ አልፈቀደዉም።ባለፈዉ ሳምንት ከዋሽግተን እስከ ብራስልስ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ድሬዳዋ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞችም የምዕራባዉያን መንግስታትና ማሕበራት በኢትዮጵያ የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ ይገባሉ በማለት አዉግዘዋል።

                                          

ለኢትዮጵያ ከመንግስት በጀት፣ ለረሐብ እስከተጋለጠዉ ሕዝብ በየዓመቱ በብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የሚረዱት፣ የሚያበድሩና የሚያለቁት ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት እና ሁለቱ የሚመሯቸዉ ተቋማት ናቸዉ።አሁን አዉዳሚዉ ጦርነት እንዲቆም ልዩ ዲፕሎማቶቻቸዉን ሾመዉ የሚባትሉትም እንሱዉ ናቸዉ።

ምዕራባዉያን መንግስታት ለኢትዮጵያዉያን የሚሰጡትን ርዳታ፣ ብድርና ሰላም ለማስፈን የሚያደርጉትን ጥረት የሚጠቅሱ ወገኖች የሳምንቱ ማብቂያዉ ዓይነት ተቃዉሞና ዉግዘት ሌላ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ብለዉ መስጋታቸዉ አልቀረም።የአፋር የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ኃላፊና ብራስልስ ዉስጥ የተደረገዉን ተቃዉሞ ሰልፍ አስተባባሪ ጋአስ አሕመድ ግን ስጋቱን አይጋሩም።ጥያቄያችን አትወግኑ የሚል ነዉ ይላሉ አቶ ገዓስ

ሽረ አንድ መንደር
ሽረ አንድ መንደርምስል Joerg Boethling/IMAGO

«በኢትዮጵያና በአዉሮጳ ሕብረትም ሆነ በአሜሪካ መካከል ያለዉ ወዳጅነት ሁላችንንም የሚያስማማ ነዉ።እኛ እየተቃወምን ያለነዉ ባንድ በኩል ያገደለ ፕሮፓጋንዳችሁን አቁሙ ነዉ----»

                                 

ኢትዮጵያ ዉስጥ የተደረጉ የተቃዉሞ ሰልፎች ያሳሰባቸዉ የምዕራባዉያን መንግስታት ኤምባሲዎች ኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎቻቸዉ እንዲጠነቀቁ፣ሰልፍና ስብሰባ ከሚደረግባቸዉ አካባቢዎች እንዲርቁም ሲመክሩና ሲያስጠነቁ ነበር።እስካሁን የደረሰ ጉዳት ግን የለም።

የዲፕሎማሲዉ ጫና፣የተቃዉሞ ሰልፉና ስጋቱ በናረበት መሐል አድዋናና አካባቢዋ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ከፍተኛ ድል፣ የሕወሓት ተዋጊዎች ታላቅ ሽንፈት ተመዘገበ።የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የፍራንስሲ ተማፅዕኖ-ጥያቄም ከወደ ቫቲካን ተሰማ።ዕሁድኢትዮጵያ የድርድር ፖለቲካ የናፈቃት ሐገር

                                 

«ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደረገዉን ግጭት በፍርሐትና በጥሞና እከታተላለሁ።ሕመም በሚሰማዉ መንፈስ በድጋሚ የምለዉ ሁከት ልዩነትን አይፈታም።አሳዛኝ ጥፋቱን ቢያበረክተዉ እንጂ።ፖለቲካዊ ኃላፊነት ያለባቸዉ ኃይላት የየዋሁን ሕዝብ ስቃይ እንዲቀንሱና ፍትሐዊ መፍትሔ ግን ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ሰላም እንዲያወርዱ እማፀናለሁ።»

ኢትዮጵያ  በቅርብ ዘመን ታሪኳ እሁለት ተገምሰዉ የነበሩ የአፍሪቃ መንግስታትን አደራድራ አንድ ማሕበር እንዲመሰርቱ ረድታለች።ሱዳኖችን፣ ናጄሪያ (ቢያፍራዎችን) ሽምግላለች።የቻዶች ዉዝግብ፣ የፖሊሳሪዮና የሞሮኮ፣ በፖሊሳርዮ በኩል የአልጄሪያና የሞሮኮ ጠብ እንዲረግብ እንደመደራደሪያ ማዕከል አገልግላለች።የሱማሌያና ተፋላሚ ኃይላት፣ የደቡብ ሱዳን ጠበኞችም አደራድራለች።

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ግን የራሳቸዉን ጠብ፣ግጭት፣ ልዩነታቸዉን በድርድር ያስወገዱበት ጊዜ የለም።ካለም አይታወቅም።

 

የአዲስ አበባና የመቀሌ ገዢዎች ጦርነት ከመግጠማቸዉ በፊት የሐገር ሽማግሌዎች፣የኃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች  ያደረጉት የሰላም ጥረትም በዕድሜ የገፉ አዛዉንቶችን ከማልፋት አላለፈም።የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን ያለፈ ታሪክና ልምድ የሚጠቅሱ ወገኖች በአፍሪቃ ሕብረት ሸምጋይነት ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ የተጀመረዉ ንግግርም አግባቢ ዉጤት ማምጣቱን የሚጠራጠሩ አልጠፉም።የአፋር ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ኃላፊ ገአስ አሕመድ አንዱ ናቸዉ።

የተመታ ታንክ
የተመታ ታንክምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

                                       

ይሁንና ጦርነቱ ያሳደረዉ የከፋ ጥፋት፣ በጦር ሜዳ የታየዉ የኃይል ሚዛን ለዉጥ፣ የምዕራባዉያን ጫና፣ የአፍሪቃዉያን ጥረት፤ የነርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፀሎት ምሕላ ሰበብ-ምክንያት ሆኖ ተፋላሚ ኃይላት ከሁነ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ነዉ የብዙዎች ተስፋ።ሁለቱን ወገኖች የወከሉት ተደራዳሪዎች የሚነጋገሩባቸዉ ርዕሶች፣ ቅደም ተከተል፣ የንግግሩ ሒደት፣ የሚደርስበት ስምምነት ካለ ገቢራዊ የማድረጊያዉ ስልት ለጊዜዉ በግልፅ አልተነገረም።ዉይይት፣ የከሸፈ ድርድር፣ አሸናፊ ያልተለየበት ጦርነት

 

ይሁንና የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር ክንደየ ገብረ ሕይወት በትዊተር ገፃቸዉ እንደፃፉት ተደራዳሪ ቡድናቸዉ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ስምምነት እንዲደረግባቸዉ ይፈልጋል።ግጭቱ ባስቸኳይ እንዲቆም-አንድ።ያልተገደበ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ-ሁለት እና የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ-ሶስት።በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስዋ አምባሳደርም ባለፈዉ አርብ ይሕንኑ ነበር ያሉት።

አቶ ገአስ ግን ንግግሩ ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ ሕወሓት ትጥቅ መፍታት፣ የጦር ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ አለባቸዉ ይላሉ።በጦርነቱ የተገዱ አካባቢዎች ሊካሱ ይገባልም።የኢትዮጵያ መንግስት የኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት እንዳስታወቀዉ መንግስት፣ ንግግሩ ግጭቱን በሰላም ለመፍታትና በሐገር መከላከያ ኃይል መስዋዕትነት የተገኘዉን ምድር ላይ ያለዉን ሁኔታ ገቢር ለማድረግ  ጥሩ አጋጣሚ ነዉ ብሎ ያምናል።መስሪያ ቤቱ በቲዊተር ያሰራጨዉ መግለጫ «ምድር ላይ ያለ ሁኔታ» ያለዉን አላብራራም።

የኢትዮጵያ መንግስትም፣ ሕወሓትም የተደራዳሪዎችን ማንነት እስካሁን በግልፅ አላስታወቁም።ይሁንና የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ዉስጥ አዋቂ እያሉ የጠቀሷቸዉ ምንጮች እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስትን የወከሉ 10 ተደራዳሪዎች ደቡብ አፍሪቃ ገብተዋል።ቡድኑ የጠቅላይ ሚንስትር የፀጥታ አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣የፍትሕ ሚንስትር ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዮስ እና የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸዉ ጀምበር ይገኙበታል።

ሕወሓትን ከወከሉ ተደራዳሪዎች ደግሞ ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይና አቶ ጌታቸዉ ረዳ አሉበት ተብሏል።የመጀመሪያዉ ቀን ንግግር የደረሰበት ደረጃ ግን ለዚሕ ዝግጅት አልደረሰልንም።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ