1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድርድር፣ የሱዳን ድንበር ውጥረት እና ሃጫሉ ሁንዴሳን የዘከረው ሽልማት

ዓርብ፣ ሰኔ 24 2014

«የሠላም ድርድሩ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ቢያልቅ ምኞታችን ነው። እውነት ለዚች አገርና ለሕዝቧ የሚያስቡ ከሆነ በሁለቱም ወገኖች መሐል ለሚነሱ አጀንዳዎች ሳይሆን እስከአሁን ለጠፋው የሰው ሕይወት እና ንብረት መውደም ብሎም ቅድሚያ ለሐገርና ለሕዝብ በመቆርቆር ከግትርነት ወጥተው ሁለቱም ወገኖች ለሠላም ብቻ ትግል ቢያደርጉ መልካም ነው።»

https://p.dw.com/p/4DXYO
Infografik Karte Äthiopien EN

ድርድሩ፤ የድንበሩ ውጥረቱ እና የሀጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ ሽልማት

የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለሰላም ንግግር ለመቀመጥ ፍላጎት ማሳየታቸው ፣ የኢትዮ ሱዳን አዲሱ የድንበር አካባቢ ውጥረት እንዲሁም የአርቲስት ሃቻሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ አዋርድ  የሳምንቱ የማህበራዊ መገናኛ አውታሮች አበይት ጉዳዮች ሆነው ሰንብተዋል። ጤና ይጥልን አድማጮች ይህ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችን ነው። 
መሸጋገሪያ 
የኢትዮጵያ መንግሥት ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ህወሓት ጋር ለማካሄድ ላቀደው ድርድር የሚወክለውን ቡድን አባላት አስታወቋል።  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰብሳቢነት ከተሰየሙበት ከዚህ ቡድን አባላት ውስጥ ዶክተር ጌድዮን ጢሞትዮስ የፍትህ ሚኒስትር፣አቶ ተመስገን ጥሩነህ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ይገኙበታል። በምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሚመራዉ ኮሚቴው የመረጃ፣የፍትሕ፣ የወታደራዊና ዲፕሎማሲ ባለስልጣናትና ባለሙያዎችን ያካተተ ነዉ። ሕወሓት ለሰላም ንግግሩ ፍላጎት እንዳለው ቢያሳውቅም  የሚወክሉትን ተደራዳሪዎች ማንነት እስካሁን አላሳወቀም። ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በቅርቡ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ድርድሩ ኬኒያ እንዲደረግ እና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ እንዲያደራድሩ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል። የፌዴራሉ መንግስት ግን ድርድሩ በአፍሪቃ ህብረት ጥላ ስር ብቻ እንዲደረግ ነው ፍላጎቱ ። ውስጥ ውስጡን ሲወራ የነበረው የፌዴራል መንግስቱ እና የትግራይ ኃይሎች ለድርድር የመዘጋጀታቸው ወሬ ወደ ተጨባጭ ዝግጅት መሸጋገሩ እንደተሰማ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሳምንቱ አበይት መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። ባሻ የዤሎይ ሁለቱ ኃይላት ወደ ድርድር ለመምጣት ያሳዩትን ፍላጎት ትልቅ ትርጉም በሰጡበት አስተያየታቸው «ዋናው ነገር ለሰላም ወደ ድርድር አሁን መምጣት መቻላችን ነው!» ብለዋል። «የትኛውም ጦርነት ወይ በአንደኛው የፍጹም የበላይነት ወይ በድርድር ነው የሚቋጨው!»  በማለት ጦርነቱ በድርድር ሊቋጭ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። 
ተደራዳሪዎችን በተመለከተ የግለሰቦች ሚና የጎላ ነው ብዬ አላምንም ምክንያቱም ከኋላቸው ያለውን የፖለቲካ ተቋም ዓላማ ይዘው ስለሚንቀሳቀሱ ሲሆን የድርድር ጊዜውን የማፋጠን/የማዘግየት ጉዳይ ላይ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል!
እጅግ ወሳኙ ነገር ለዚህች በታሪክ ከጦርነት መከራና ስቃይ መለየት ላልቻለች ሃገር ከእንግዲህ ጠመንጃ በቃን የሚል ስር ነቀል እሳቤ የሚይዝ መንግስትና ህብረተሰብ ማግኘት መቻል ነው! ሃገር ለማዳን ያሰብ ድርድር እንዲሆን መጸለይ አለብን!»
የድርድሩን መካሄድ በእርግጥ ሰላም ወዳዱ ህዝብ በጉጉት የሚጠብቀውና ዕልቂት እና ሰቆቃው እንዲያበቃ ፍላጎቱ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ ይሰማል። ተደራዳሪዎቹ ከድርድር በፊት ያነሷቸው አንዳንድ የተናጥል  ሃሳቦች ስጋት እንዳቻረባቸው የገለጹም አልጠፉም  ሳንጆ ካሳ የተባሉ ባሰፈሩት ሃሳባቸው  «የሠላም ድርድሩ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ቢያልቅ ምኞታችን ነው። 
ነገር ግን የሠላም ድርድሩ በአሁኑ ሰአት በሁለቱም ወገኖች እንደ አጀንዳ የሚቀርቡት ነገሮች ድርድሩ ላይ እንቅፋት እንዳይሆኑ ስጋት አለኝ፤  ይላሉ። ቀጠል አድርገውም 
እውነት ለዚች አገርና ለሕዝቧ የሚያስቡ ከሆነ በሁለቱም ወገኖች መሐል ለሚነሱ አጀንዳዎች ሳይሆን እስከአሁን ለጠፋው የሠው ሕይወት እና ንብረት መውደም ብሎም ቅድሚያ ለሐገርና ለሕዝብ በመቆርቆር ከግትርነት ወጥተው ሁለቱም ወገኖች ለሠላም ብቻ ትግል ቢያደርጉ መልካም ነው፤ እንደኔ እንደኔ ከሆነ ግን ድርድሩ ከወድሁ እያስፈራኝ የመጣ ጉዳይ ሆኗል» ብለዋል።
እስክንድር ሃይሉ ባሕሩ የተባሉ አስተያየት ሰጬ ደግሞ ሁለቱ ወገኖች የመደራደር ፍላጎት አሳይተው ሳያበቁ እያሳዩ ነው ነው ባሉት ያለተገባ አስተያየት ላይ ባሰፈሩት ሃሳባቸው 
« ወደ ድርድር የሚሄድ እየተሳደበ: እየተራገመና "ባትደራደር በጠንካራ ወታደራዊ ዘመቻ እደቁስሀለሁ!" እያለ አይደለም። ድርድር ለማድረግ ከፈቀደበት እስከ ድርድሩ ሰላማዊ ሂደት ከስድብ መቆጠብ ለድርድሩ መልካም ነው።» ብለዋል። 
በመጨረሻም ብርሃኑ ዲንሳ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ባሰፈሩት አስተያየት ርዕሰ ጉዳዩን ስንቋጭ  ሃሳቡ እንዲህ ሰፍሯል። « ቀድሞውንም ጦርነቱ አስፈላጊ ሆኖ ሳይሆን በአንዳንድ ፅንፈኞችና በጥላቻ በሰከሩ ያልበሰሉ አመራሮች ፍላጎት እንዲሁም በበቀል በተሞሉ የኤርትራ ባለስልጣናት ግፊት የተደረገ የእርስ በእርስ ጦርነት ነበር በዚህም ሀገሪቱ በታሪክ ያልታሰበ እና ያልተገመተ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ውድመትን አስተናግዳለች ። ዘግይቶም ቢሆን እየተወሰደ ያለው የሠላም አማራጭ የሆነው ድርድር ብቸኛ የመፍትሔ አካል ሰለሆነ ሁለቱንም እኩል በሚያግባባ መልኩ ማንም በማይጎዳ መልኩ ከልብ ይቅር ለፈጣሪ ተባብሎ እርቀ ሰላም ቢወርድ ለሀገሪቱ ትልቅ ድል ነው።» ብለዋል። በእርግጥ ነው ለሰላም የተሸነፈ ሁሉንስ ያሸነፈ አይደለምን? ወደ ተከታዩ ርዕሰ ጉዳይ እንለፍ፤
ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚዋሰኑባቸው የድንበር አካባቢዎች ሰባት የሱዳን ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት መካከል አዲስ ውጥረት አስከትሏል። ይህንኑ ተከትሎ ሱዳን የአጸፋ ያለችውን ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ መውሰዷ ታይቷል። ኢትዮጵያ በበኩሏ የወታደሮቹ ግድያ በመደበና ጦር አለመፈጸሙን ፤ ነገር ግን የሱዳን ወታደሮች ድንበር ተላልው መገኘታቸውን በጸብ አጫሪነት ከሳለች። አዲሱ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ላይ ውጥረት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት ያገኘው ሌላው የሳምንቱ አበይት ጉዳይ ሲሆን በርካታ ሰዎች አስተያየቶቻቸውን አካፍለውበታል። 
አሊ ከተማ ኩመራ ባሰፈሩት አስተያየት «ለምንድነው ስለ ሱዳን የሀገራችንን ግዛት በሀይል መቆጣጠር አሁን የምንጨነቀው? ኤርትራ እኮ የሀገራችንን ግዛት በሀይል ከተቆጣጠረች ቆየች ሁለት አመት አደረገች::ሉአላዊነታችንን መድፈር ለኤርትራ ከተፈቀደ ለምን ለሱዳን ለኬንያ ... ይከለከላል?» ሲሉ መኮንን ወልዴ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ አስተያየት ሰጭ ደግሞ «ድንበር ጥሶ ለወረራ የመጣውን የጠላት ወታደር አበባ ይዘን አንቀበልም የምን ማጣራት የምን የሃዘን መግለጫ መላክ በሀይል የወረረውን በሀይል ማስወጣት እንጂ መለማመጥ አያስፈልግም ።» ብለዋል።
 ገነቲ ፈይሳ «ሱዳን ከሶስት ዓመት በላይ ኑሬአለው ።እንደ ሱዳን ኢትዮጵያን የሚፈራ አላየሁም ። ኮሎኔል መንግሥቱ መጣ ከተባለ መግቢያ መዉጫ ያጡ ነበር።  ዛሬ ተጨማሪ ቦታ አልያዙም የሚል ዜና መስማት ያማል።በማለት የቀደመውን ጊዜ በቁጭት ያስታወሱበትን ሃሳብ አስፍረዋል።
በድንበር ውዝግቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሚወጡ መረጃዎችን ማመን የተሳናቸው የአብስ ጫኔ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ « መንግስትን ከማመን ሱዳን ያለችውን ማመን ሳይቀል አይቀርም። » ይላሉ። «ዱቄት ሆኗል ሲል ከርሞ ያሁሉ ውድመት የመጣው መንግስት በመታመኑ ነው። ጎበዝ መንግስትን እንመን ወይስ ሱዳንን?» በማለት ሃሳባቸውን አስፍረዋል።
መሀመድ ተማም በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ስሜታቸው መደበላለቁን በገለጹበት ሃሳባቸው «ሀገሬ ስትደፈር ይሰማኝ ነበር አሁን ግን ስሜቴ ምን እያለኝ እደሆነ አልገባኝም ውስጣዊ የሀገሬ ፍቅር የት እደሄደ ገራ ገባኝ ሰዋች ከምንም ጋር ሳታገናኙ ምክራቹን ለግሱኝ፤ የምስማው መዓት በዝቶ አላውቅም ብቻ, » ብለዋል። መኮንን ወልዱ ደግሞ «ታፍራና ተከብራ ለዘመናት የኖረችው የቴዎድሮስ አገር የምኒልክ አገር የነ መንጌ አገር በዚህ ትውልድ ዘመን ያውም በሱዳን መደፈሯ ያሳዝናል ያንገበግባል»
ሳሙኤል አበበ ደግሞ «ይህ ሁሉ ጋጋታና ያዙኝ ልቀቁኝ ምንድንነው ወ/ሮ ሱዳን በጣም ተዘነጋሽ እንዴ መሪዎቻችን ቢቀያየሩም የኢትዮጵያ ህዝብና ጀግንነት አልተቀየረም ዛሬም የግብፅንና የተላላኪዎችን ወሬ ሰምተሽ ማሽላላት አብዝተሻል ፤አሁንም ቢሆን ጀግና መሪ እንዳለን እወቂ » በማለት ሃሳባቸውን አስፍረዋል። 
መሸጋገሪያ 
የተወዳጁ የኦሮሞ የሙዚቃ ንጉስ ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ ሁለት ዓመት ሞላው ። የአርቲስቱ ህልፈት ለቤተሰቦቹ ብቻም ሳይሆን በመላው ኦሮሞ እና የእርሱ አድናቂ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዛሬም ድረስ ያስቆጫል። ከሰሞኑ ደግሞ በእርሱ ስም የተቋቋመው ፋውንዴሽን ሁለተኛውን ዓመት የሙት ዓመት መታሰቢያ የዓመቱ ምርጥ የአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ስራዎችን ሸልሟል። የሽልማት ስነስረዓቱ በአጭር ጊዜ የተከናወነ ቢሆንም የባለቤቱን የሀዘን እና የልብ ስብራት ፣ እንዲሁም በአርቲስቱ ግድa እና እስካሁንም ፍትህ አላገኘም የሚሉ በርካታ አስተያየቶችን እያጋሩ ይገኛሉ። ከእነዚህም  ውስጥ አሌክስ ፎ በሚል የፌስ ቡክ ከሰፈረ አስተያየት ላይ «የሐጫሉ ባለቤት ለስንት ዓመት የሐዘን ልብስ ልትለብስ ነው? እድሜ ልካችንን ማዘናችን እንደማይቀር ግልፅ ነው። ጥቁር መልበስ ግን እስከ መቼ? በማለት ይጠይቃሉ። ባለቤቱ በተለይ ያንን የመሰለ ተቋም ካቋቋመችና ለመጪዎቹ መዓት ዓመታት ሐጬን የምያስታውስ ተጨባጭ ስራ ከጀመረች በኋላ፣ በደስታ ቀና ብላ ስራዎቹን መስራት ላይ ማተኮር አለባት ብዬ ነው ማስበው » ይላሉ ። ቀጠል አድርገውም ። 
ሐዘን ይሰብራል፣ ሞራል ይገላል፣ ጉልበት ያዝላል። አንድ ግዜ ሰብሰብ በሉና ልብስ አስቀይሯት፣ ሕግና ባሕሉን አላውቅም ግን፣ በቃት!!» ይላል። 

Äthiopien Denkmal des Künstlers Hachalu Hundessa in Ambo eingeweiht
ምስል Seyoum Getu/DW
 Sudan-Äthiopien Grenze
ምስል Nariman El-Mofty/AP/picture alliance
Äthiopien Metema | Grenze zum Sudan
ምስል Alemenew Mekonnen/DW
Sudan General Abdel Fattah al-Burhan
ምስል Mahmoud Hjaj /AA/picture alliance
Äthiopien Konflikt in Tigray | Debretsion Gebremichael
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS
Äthiopien | Demeke Mekonnen Hassen
ምስል Graham Carlow/Creative Commons

ተፉ ተፉ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ «በመጀመሪያ ሀጫሉን ያስገደለው ማነው ነው ? ለምን አላማ ጭዳ ሆነ ? ምን ትርፍ ለማግኝት አስገደሉት ? »በማለት በጥያኤ ላይ ጥያቄ እያከታተሉ አስፍረዋል።  በመቀጠልም። «በሱ ሰበብ ለምን የአማራ እና የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዬች በጭካኔ እንዲተጨፈጨፉ ተደረገ ? የፍርድ ሂደቱን ቤተሰቦቹ እንዲሁም አድናቂወቹ ህዘቡ ለምን አልተዋጠላቸውም ? ብዙ ያልተመለሰ ጥያቄ አለ ? ሀጫሉ ሞቶም በስሙ ድራማ እና የፖለቲካ ቁማሩ አስአሁኗ ደቂቃ ቀጥሎአል ለምን ?» ብለዋል። 
ዮሐንስ ጌታነህ ደግሞ «በሀጫሉ ሞት እልፍ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል ፣ ንብታቸው ወድሟል በአጠቃላይ በኦሮሚያ ምድር ዘግናኝ ድርጊት ተፈፅሟል። የእሱን ሞት ስናስብ በሱ ምክንያት የሞቱትን ንፁሃን ዜጎች እያሰብን።» በማለት ሃሳባቸውን አስፍረዋል። 


ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ