1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትኩረት በአፍሪካ መሰናዶ

ቅዳሜ፣ መስከረም 22 2014

ኢቦላን ለመከላከል ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የዘመቱ የዓለም ጤና ድርጅት ሰራተኞች አስገድዶ መድፈር እና ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል የሚል ክስ ከተሰማ በኋላ ምዕራባውያን ተቋሙ ላይ ጫና እያሳደሩ ነው። በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በርካታ ሴቶች የሥራ ዕድል ለማግኘት ወሲብ እንዲፈጽሙ መጠየቃቸውን እንዲሁም ተገደው መደፈራቸውን ለመርማሪዎች ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/41Akt
Kongo: Erneuter Ausbruch von Ebola
ምስል Reuters/G. Tomasevic

ትኩረት በአፍሪካ መሰናዶ

የኢቦላ ወረርሽኝን ለመከላከል ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የዘመቱ የዓለም ጤና ድርጅት ሰራተኞች አስገድዶ መድፈር እና ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል የሚል ክስ ከተሰማ በኋላ ምዕራባውያን አገራት በተቋሙ ላይ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።

ድርጅቱን በገንዘብ ከሚደግፉ ዋና ዋና አገራት መካከል አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ አውስትራሊያ፣ ኒው ዚላንድ፣ ኖርዌይ፣ ካናዳ እና የአውሮፓ ኅብረት የዓለም ጤና ድርጅት መሰል ድርጊቶችን ለመከላከል ቁርጠኛ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። ጥሪውን ያቀረቡት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በርካታ ሴቶች የሥራ ዕድል ለማግኘት ወሲብ እንዲፈጽሙ መጠየቃቸውን እንዲሁም ተገደው መደፈራቸውን ለመርማሪዎች በመናገራቸው ነው።

"ከዓለም ጤና ድርጅት እንዲህ አይነት ድርጊቶችን ለመከላከል መሠረታዊ ለውጦች ማድረግን ጨምሮ ቁርጠኝነት እንዲኖር እንጠብቃለን" ሲሉ ምዕራባውያኑ አገሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ ጽፈዋል።

የድርጅቱ አባል የሆኑት መንግሥታት "የዓለም ጤና ድርጅት አመራር ቁርጠኝነት ወደ ተጠያቂነት፣ የደረጀ አቅም እና እርምጃ እንዲሁም አፋጣኝ ለውጥ ማምራቱን እናረጋግጣለን" ብለዋል።

ባለፈው ማክሰኞ በገለልተኛ የምርመራ ኮሚቴ ይፋ የሆነው 35 ገጾች ያሉት ሪፖርት ከጎርጎሮሳዊው 2018 እስከ 2020 ባሉት አመታት የኢቦላ ወረርሽኝን ለመከላከል የተሰማሩ የአገሪቱ እና ዓለም አቀፍ የጤና ባለሙያዎች ላይ የቀረቡ ክሶች ላይ ያነጣጠረ ነው።

ጉዳዩን "ለዓለም ጤና ድርጅት የጨለማ ቀን" ያሉት የድርጅቱ ኃላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ለድርጊቱን ሰለባዎች ማዘናቸውን ተናግረው  "ጥፋት ፈጻሚዎች ይቅርታ እንዲደረግላቸው ሳይሆን ተጠያቂነታቸን ማረጋገጥ ቅድሚያ" የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬው የትኩረት በአፍሪካ መሰናዶ በዓለም ጤና ድርጅት ሰራተኞች ላይ የቀረበውን ይኸንን ክስ እና የቱኒያን የፖለቲካ ቀውስ ይዳስሳል።

 

ሙሉ ዘገባውን የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ

 

ገበያው ንጉሴ

እሸቴ በቀለ