1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ዴሞክራሲ እንዲያሸንፍ እንሰራለን!" -የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ 

ቅዳሜ፣ መጋቢት 18 2013

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) መጪው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰራ አስታወቀ፣ ፓርቲው ለክልልና ለፌደራል ተወካዮች ምክር ቤቶች በአጠቃላይ ለ147 መቀመጫዎች ይወዳደራል፡፡ አዴኃን በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው እንግልትና ግድያ እንዲቆም መደራጀት አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡ 

https://p.dw.com/p/3rGr9
Äthiopien | Vorsitzende der UEDF Tesfahun Alemneh
ምስል DW/A. Mekonnen

"ዴሞክራሲ እንዲያሸንፍ እንሰራለን!" -የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ 

የንቅናቄው አመራሮች በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት አዴኃን በምርጫው በክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሳተፋል፡፡ እስከዛሬ የተደረጉ ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊ አአልነበሩም ብሎ የሚያምነው አዴኃን፣ 6ኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ግን ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና በህዝብ ዘንድ ታአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አሰራለሁ ብሏል፡፡ 
የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ በተለይ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ዴሞክራሲ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ እንሰራለን ነው ያሉት፡፡ 
ከምርጫ በፊትና ከምርጫ በኋላ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ የሚሉት አቶ ተስፋሁን ሂደቱ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና በተለይ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ድርብ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ 
አዴኃን የሚከተላቸውን እሴቶችና መርሆች ያብራሩት ደግሞ የንቅናቄው የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ እንጅነር ሙሉጌታ ፀጋዬ ናቸው፡፡ 
አሁን አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት፣ እንግልትና ወከባ በዘላቂነት ለማስቆም የሚቻለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት ብቻ እንደሆነ የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ አስረድተዋል፡፡ 
የአዴኋን የምርጫ ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ ምርጫው ስንሻው የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሌላው መንገድ መደራጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 
በአማራ ስም የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አንድ በመምጣት በአማራ ላይ የተደቀነበትን የህልውና ፈተና መመከት አለበት ሲሉ አቶ ምርጫው ተናግረዋል፡፡ 
አዴኃን ለለአማራ ክልል ምክርቤትና ለፌደራል ተወካዮች ምክር ቤት በአጠቃላይ ለ147 መቀመጫዎች ይወዳደራል፡፡ 
በአማራ ክልል በክልል ደረጃ ከሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የአማራ ዴሞክራሲ ኃይል ንቅናቁና የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ይገኙበታል፡፡ 
በአማራ ክልል በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚወዳደሩ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ ብልፅግና፣ አብንና ኢዜማ ይጠቀሳሉ፡፡ 
ዓለምነው መኮንን