1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳግም የተከሰተው የአንበጣ መንጋ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 29 2013

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት ከ25 ዓመታት በፊት የተከሰተው አይነት የአንበጣ መንጋ ወረራ ባለፉት በርካታ ወራት አጋጥሟቸው ብዙ ጉዳትም አድርሷል። ከጥቂት ወራት በፊት በነበረው ደረቅ አየር ምክንያት መቀነሱ ሲነገርለት የነበረው ጸረ ሰብሉ አንበጣ በአካባቢው የክረምት ወቅት ዝናብን ተከትሎ ዳግም መታየት ጀምሯል።

https://p.dw.com/p/3w4Cr
Kenia Meru | Heuschreckenplage & Landwirtschaft
ምስል Yasuyyoshi Chiba/AFP/Getty Images

«እንዳለፉት ጊዜያት ላይባባስ ይችላል»

ለጥቂት ወራት የመቀነስ አዝማሚያ ካሳየ በኋላ በሰሜን ምዕራብ ሶማሊያ በጣም ያላደገ የአንበጣ መንጋ እየታየ መሆኑን የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ላይ ጠቁሟል። መረጃው እንደሚለውም በኢትዮጵያ እና ጅቡቲም መጠኑ ከፍ ያለ መንጋ በአጎራባች አካባቢዎች መኖሩንም ገልጿል። ድርጅቱ በተጠቀሰው አካባቢ ያሉት ምናልባት እዚያው የተፈለፈሉ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ነው ያመለከተው። በአሁኑ ጊዜም የባብሩር መስመር ባለበት አይሻ አቅራቢያ እንዲሁም በጅቡቲ እና ሶማሊያ ድንበር አካባቢ አነስተኛ የአንበጣ መንጋ መኖሩን በመጠቆምም፤ በንቃት ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጿል። በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በላይነህ ንጉሤ የአንበጣ ወረራው ያለበት ደረጃ ለጊዜ አያሰጋም ነው የሚሉት።

ከወደ አማራ ክልል ምሥራቅ ዞን አካባቢዎች እንደተሰማው የአንበጣ መንጋ በ38 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ተከስቶ፤ የአካባቢው አርሶ አደር በባህላዊ መንገድ ለማባረር እየታገለ ነው። የግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ኃላፊው ከአምናው ጋር ሲወዳደር አሁን የታየው መጠነኛ ቢሆንም ክትትል እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ። አሁን በአማራ ክልል ምሥራቃ ዞን አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ መነሻው ከሀገር ውስጥ መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊው በቂ ዝግጅት መደረጉንም ነው የገለጹት።

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በመላው ዓለም በ23 ሃገራት የሚኖሩ አንድ ቢሊየን ሰዎች በአንበጣ መንጋ ኑሯቸው ጫና ደርሶበታል።  የተጠናከረው የአንበጣ ወረራ ከጀመረበት ከአንድ ዓመት በፊት አንስቶ በተደረገው የመከላከል ጥረትም 5,3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ተገቢው ክትትል ተደርጎለታል። በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ፣ በሰሜን ሶማሊያ፣ በጅቡቲ እና በየመን ክትትሉ በንቃት መቀጠል እንዳለበትም ያሳስባል።

Infografik Heuschrecken EN

የዓለም ምግብ እና የእርሻ ድርጅት በተለይ ግጭት ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት ያላገኘው የአንበጣ መንጋ ተፈልፍሎ ወደ በርካታ ሃገራት መዛመቱን በየጊዜ ይገልጻል። አንዱ ጋ የተጠናከረ ክትትል እያለ ሌላው ጋር ባለመኖሩም አንበጣን የማጥፋቱን ጥረት ትርጉም እንደሚያሳጣው ነው አቶ በላይነህ አጽንኦት የሰጡት።

አንበጣ በባህሪው ራሱን የሚደብቅበት መንገድ አለው፤ ለምሳሌ ብዛታቸው ሲቀንስ የሚበሩት በሌሊት ሲሆን ማንም ሳያገኛቸው ተደብቀው እንቁላል ይጥላሉ። ይኽና መሰል የአንበጣው ባህሪ በቀላሉ እንዳይጠፋ እንደረዳውም ገልጸዋል። አሁን ወቅቱ የዝናብ ነው፤ ዝናብ ካለ ደግሞ አንበጣን የሚስበው ልምላሜ ይኖራል። ለመራባትም አመቺ እንደሚሆንለት ነው የሚነገረው። በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በላይነህ ፤ ይኽን ሁሉ አስቀድሞ በመገንዘብ ተገቢው ጥንቃቄ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ካጋጠመው የአንበጣ መንጋ ችግር በመነሳትም በርካቶችን በማሰልጠን በክትትል ሥራው ማሰማራቱንም አስረድተዋል። በነገራችን ላይ የዓለም ምግብ እና የእርሻ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በአንድ የእርሻ ማሳ ላይ የሚያርፍ የአንበጣ መንጋ በአንድ ቀን 35 ሺህ ሰዎችን ሊመግብ የሚልች ሰብል ይበላል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ