1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደ.አፍሪቃ ሱዳንና ግብፅ የሕዳሴ ድርድርን እንዳያቋርጡ ጠየቀች

ሐሙስ፣ ሐምሌ 30 2012

ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ የሚያደርጉትን ድርድር የምትመራዉ ደቡብ አፍሪቃ ድርድሩ እንዲቀጥል ጠየቀች። ግብፅ ትናንት ረቡዕ ድርድሩ እንዲቆም ስትጠይቅ ሱዳን ደግሞ ከድርድሩ ሙሉ በሙሉ እንደምትወጣ አስጠንቅቃ ነበር።

https://p.dw.com/p/3gYa8
Nationalflagge Südafrika
ምስል Imago Images/F. Sorge

ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ የሚያደርጉትን ድርድር የምትመራዉ ደቡብ አፍሪቃ ድርድሩ እንዲቀጥል ጠየቀች። ግብፅ ትናንት ረቡዕ ድርድሩ እንዲቆም ስትጠይቅ ሱዳን ደግሞ ከድርድሩ ሙሉ በሙሉ እንደምትወጣ አስጠንቅቃ ነበር። የወቅቱ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር እና የድርድሩ መሪ ደቡብ አፍሪቃ በበኩልዋ ዛሬ ባወጣችዉ መግለጫ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታዉቃለች። ኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳን በሕዳሴዉ ግድብ ላይ የሚያደርጉትን ድርድርም እንዳያቋርጡ ደቡብ አፍሪቃ ጠይቃለች።  ትናንት ረቡዕ ግብጽ እና ሱዳን  በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ከሚደረገው ድርድር ማፈንገጣቸዉ የተሰማዉ  ኢትዮጵያ ትናንት በተደረገው ድርድር የግድቡን ውኃ አሞላል የተመለከተ ረቂቅ ደንብ ካቀረበች በኋላ ነበር።

የሱዳኑ የመስኖ ምኒስትር ያሲር አባስ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ረቂቅ ሙሉ ድርድሩን የሚያሰጋ ነው ሲሉ ተናግረዉ ነበር። አባስ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሰነድ የግድቡን የወደፊት አስተዳደር በአባይ ውኃ ላይ ለሚደረስ አጠቃላይ ስምምነት የሚተው ነው። ግብጽም እንደ ሱዳን ሁሉ ኢትዮጵያ ለድርድር ያቀረበችው ሰነድ የግድቡን የወደ ፊት የሥራ ክንውን እና ሕጋዊ የቅራኔ አፈታትን ያላካተተ ነው ብላለች። ኢትዮጵያ ያቀረበችው የግድቡን ውኃ አሞላል የተመለከተ የሥምምነት ረቂቅ "የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጽህፈት ቤት ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መሠረት" መሆኑን የውኃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በያዝነዉ ሳምንት ማክሰኞ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወቃል። የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ምኒስትሩ ስለሺ በቀለ "የመጀመሪያውን የውኃ አሞላል ሥምምነት በፍጥነት ለመፈረም እና በቀጣይ ጊዜያት አጠቃላይ ሥምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር ለመቀጠል" ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ