1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደብዛው ጠፍቶ የሰነበተዉ ጋዜጠኛ፤ የሃይማኖቶች የመሰለዉ ዉዝግብ፤ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ጭማሪ

ዓርብ፣ ግንቦት 5 2014

«እንኳን ጉዳት ሳያደርሱብህ ለልጆችህና ለቤተሰብህ በቃህ፤ ይህ አስተዳደር ከወያኔ አገዛዝ የባሰ ጨቋኝና ዘራፊ ይሆናል ብሎ ማንም ይከብዳል። ወንጀል የሰራ ለዚያውም ንፁኃን ፆመኞች ቀብር ላይ በሐዘን ላይ እያሉ የገደለን ህዝብ ተረባርቦ ፍትህ ካላሰጠ ፈጣሪን እፈራለሁ ቢል ውሸቱን ነው። የምን ዋጋ ማስተካከያ ነዉ። የዋጋ ጭማሪ ነዉ የሚባለዉ»

https://p.dw.com/p/4BF4w
Social Media Apps | WhatsApp Facebook Twitter Instagram
ምስል Nasir Kachroo/ZUMA Press/imago images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በእዚህ ዝግጅታችን እንዲሁም ደብዛው ጠፍቶ የሰነበተዉ ጋዜጠኛ በዘጠኝ ቀኑ ከታፈነበት መለቀቁ፤ የሃይማኖቶች የመሰለዉ ዉዝግብ እንዲሁም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ጭማሪ በተሰኙ ርዕሶች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምቀን ይዘናል። 

በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች እሁድ ሚያዚያ 23 ቀን፣2014 ዓ.ም ከቤቱ የተወሰደዉ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ለዘጠኝ ቀናት የነበረበት አድራሻ ሳይታወቅ በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ዓይኑን ተሸፍኖ እራሱን ቤቱ ደጃፍ ላይ እንዳገኘ ገለጾአል። በጤንነቱ ላይ ምንም ነገር እንዳልደረሰም ተናግሮአል።

Fake News Photo Illustration
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

ጎሳዬ ወልደስላሴ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በአስተያየታቸዉ «አሳዛኝ አገር »ይላሉ። «የሚለዋወጥ መንግስት ሁሉ ያለፈውን እያወገዘ የባሰ አፋኝ የሚሆንባት ያልታደለች ሀገር። እንኳን ጉዳት ሳያደርሱብህ ለልጆችህና ለቤተሰብህ በቃህ፤ አራት ዓመት ሳይሞላው ይህ አስተዳደር ከወያኔ አገዛዝ የባሰ ጨቋኝና ዘራፊ ይሆናል ብሎ ማንም ይከብዳል። ግን የረሱት እንደወጡ መውረድም እንዳለ እና እንደሚጠየቁም መርሳታቸው ነው  የሚገርመው» ሲሉ አስተያየታቸዉን ይደመድማሉ።

«አጥፊ ጋዜጠኛ መታሰር አለበት» ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት ታምሩ ኖፕ የተባሉ የመገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ «ለሃገር ሰላም የሚሰራ ጋዜጠኛ ማን ታስሮ ያውቃል? ጋዜጠኛ ላይ የወንጀልም የፍትሀብሄርም የወጣ አዋጅ  አይቀርላቸውም፡ ህጋዊ ልጉዋም ማበጀት ግድ ነውና» ሲሉ ፤ በዚሁ ሰሞን ታስቦ የዋለዉን የመናገር ነፃነት የደፈቀ የመሰለ አይነት አስተያየት አስቀምጠዋል።

ዳኒ መኮንን የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ በበኩላቸዉ፤ «አሜን እንኳን ለቤትህ በቃህ የኔ ጎበዝ። መያዝህ ሳይሆን ተይዘህ ብዙ እንደ አንተ በግፍ የታሰሩትን ያስለቀክ እና ያስፈታህ ንፁህ እውነተኛ የኢትዮጵያ ምርጥ ጋዜጠኛ ነህ። ሌሎች ጋዜጠኞች መማር ካለባቸው ከአንተ ከጀግናው መማር ይገባቸዋል። ጎበዜ የኔ ጎበዝ እድሜና ጤና የዛሪዋ ልደታ ትስጥህ» ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።  

ኦማር እሸቱ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ «ህግና መንግስት የሌላት ሀገር እሆነች ነው።  አንድ ሀገር ዜጎች የሚዳኙበት ፍትሃዊ ህግና ህጉን ተግባራዊ የሚያደርግ ጠንካራ መንግስት ያስፈልጋል። እንደ አለመታደል ሁኖ እኛ ሁለቱም የለንም። እንደ ከብት ተነድተን እንታጎራለን፤ መብትና ግደታ የለም» ሲሉ አስተያየታችዉን ደምድመዋል።

ሰዒዳ ይማም «በጣም ያሳፍራል እንደ አገር ውርደት ነው። ያውም መሃል አዲስ አበባ። የፌድራል መንግሥት መቀመጫ በተባለ ቦታ?» በጥያቄ አስተያየታቸዉን ያበቃሉ።

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

ባለፈዉ ሚያዚያ 18  ጎንደር ከተማ ዉስጥ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸዉን፣ ሐብት ንብረት ማዉደሙንና ቤተ-እምነቶችን ማቃጠላቸዉን የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ጉባኤ አዉግዞአል። የጉባኤዉ አባላትና የተለያዩ ሃይማኖቶች ተጠሪዎች እዚያዉ ጎንደር ዉስጥ ባደረጉት ዉይይት ለተገደሉት ሰዎች ቤተሰቦች ካሳ እንዲሰጥና የወደሙ ተቋማትን በጋራ መልሶ ለመገንባት ተስማምተዋል።

ካሳዬ ወንድሙ፤ የተባሉ አስተያየት ሰጭ «በክርስቲያኑ እና በሙስሊሙ መካከል ጦርነት እንዲነሳ ተቀናጅታችሁ ስትሰሩ የነበራችሁ ለደረሰባችሁ የፖለቲካ ክስረት መጽናናትን እንመኛለን» ሲሉ አስተያየታቸዉን ያበቃሉ።

እዮብ ዓለሙ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛዎች ተጠቃሚ፤ «ወንጀል የሰራ ለዚያውም ንፁኃን ፆመኞች ቀብር ላይ በሐዘን ላይ እያሉ የገደለ ለፍርድ ካልቀረበ፤ ካልተቀጣ የኢትዮጵያ ህዝብ ተረባርቦ ፍትህ ካላሰጠ ፈጣሪን እፈራለሁ ቢል ውሸቱን ነው። ወንድሙን ንቋል። ነግ በኔላይ ቢደርስ ብሎ ማሰብ አቅቶታል ። በተለይ ግፍ መፍራት አቁሟል ማለት ነው። ፍትህ በግፍ ለተገደሉት ሙስሊም ወንድሞች። እንዲሁም ፍትህ ለክርስቲያን በማያገባቸው ለተገደሉ ሁሉ። ህግ ይከበር፤ ለኢትዮጵያ ሰላም ሲባል» አስተያየታቸዉን ያበቃሉ።

ጥላሁን ምትኩ በበኩላቸዉ « በስልጤ ዞን በቅርቡ ቃጠሎ ደርሶባችው የነበሩ የእምነት ተቋማትን መልሶ የመገንባት ሥራ መጀመሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አጥፊዎች በየትም ቦታ ያሉ እንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ የተሳተፋ ያስተባበሩ፤ በህግ ሊጠየቁ እና የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ ይገባል። አለበለዚያ ዛሬ የተገነቡት ነገ እንደማይወድሙ ማረጋገጫ የለም»

Russland | Social Media
ምስል Sefa Karacan/AA/picture alliance

ዛዲክ ኡስማን በበኩላቸዉ፤ «ይህ ሁሉ  ለዓመታት የተሰበከ የጥላቻ ንግግር ውጤት ነዉ። በቤተ እምነት መንፈሳዊ ነገር መሰበኩ ቀርቶ ጦር የሚያማዝዙ ሰበካዎች እየተጧጧፉ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዛሬ እያየን ያለነው የእነዚህ ሰበካዎችን ውጤት ገፈቱን ነው። እየተደገሰ ያለው የከፋ ነው» ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

እውነታኛ ሽማግሌ «በሀገሪቱ ላይ ያለ አይመሥለኝም» ሲሉ አስተያየታቸዉን የፃፉት ከድር ሙዘይን «እዉነተኛ ሽማግሌ ቢኖርማ በስሜት የሚነዳ ወጣት ሀይ የሚለው ባልጠፋ ነበር» ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ምንላለሁ እንዳሻው፤ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ «አገሪቱ በልዩነት የተመሰረተች ስለ ሆነች እኮ ነው ? እና በመቻቻልና በልዩነት የተሞሉ አብሮነትን የሚያጎለብቱ ተቋማት ከሌላት እናንተስ በምን መልኩ በጋራ ትመራ ትላላችሁ ?» ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚያዚያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም አንስቶ የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ አድርጓል። ለዋጋ ማስተካከያው ምክንያት የሆነው የዓለም አቀፍ የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እንደሆነ መንግሥት አስታውቋል።

«የምን ዋጋ ማስተካከያ ነዉ ። ጥርት ባለ አማርኛ የዋጋ ጭማሪ ነዉ የሚባለዉ» ሲሉ አስተያየታቸዉን የፃፉት ፍቅር ማሻ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸዉ።

አኒ ካሳ በበኩላቸዉ «ናይጀሪያ ከአፍሪቃ ባለ ነዳጅ ሀገር ነች፤ግን ደግሞ በነዳጅ ዋጋ መናር ምክኒያት የሀገር ውስጥ የአየር በረራወቿን ሰርዛለች እና ይህ ዉድነት የመጣዉ ከቤንዚን እጥረት አይደለም።» ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።  

ሚኪ ጥበቡ፤ የተባሉ የፉስቡክ ተከታታይ በአስተያየታቸዉ «ቤንዚል እና ነጭ ናፍጣ ዋጋቸው መቀራረቡ እና መጥበቡ ተገቢ አይመስልም።  ምክንያቱም አብዛኛው የነጭ ናፍጣ ተጠቃሚ መኪኖች አገልጋዬች ናቸው። እነዚህ ግልጋሎት እሚሰጡ መኪኖች ድጎማ  ቢደረግላቸው ጥሩ ነው። መንግስት እልህ የተጋባው ቤንዚል ከሚጠቀሙ መኪኖች እና ከተማውን ከሚሞሉ ተሽከርካሪ እና ባላሃብቶች ጋር ነው። እና የናፍጣ ተጠቃሚ መኪኖችም ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው» ሲሉ ሃሳባቸዉን ጽፈዋል።

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Ozan Kose/AFP/Getty Images

ዳንኤል ጌታቸዉ የተባሉ በበኩላቸዉ «ከሁሉም መንግስት ሁኔታውን በአግባቡ ማስተዋል አቅቶታል። ድጎማውን መቀጠል ይሻለው ነበር። አጠቃላይ የኢኮኖሚ ቀውስ ከመፍጠር ሰው ለምን ኖሮን ተቋቋመ ይመስላል። ሁሉም ነገር ልክ አለው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሀብታሞች ምንም አይነኩም። እንደውም መካከለኛ ገቢ ያለውን ከባለሀብቱ የባሠ ማራራቅ ነው። ሎጀስቲክስ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ ነው። መንግሥት ይሄንን በወሬ ብቻ ያውቀዋል። እናም ለሌቦች መንገድ ይከፍታል። ድግስ በየጊዜው ይደግሳል። የእነሱ ኢትዮጵያ እና የኛ ኢትዮጵያ ይለያያል እንዴ? ነዳጅ ብቻ አይደለም። የመንግስት አገልግሎት ክፍያም ጨምሯል። ሌላም ሌላም። እመረጣችሁ ህዝብ ባታማርሩ ይሻላል» ሲሉ ፅፈዋል።

ወልጫፎ ነጋሽ ገብሪ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ «ለዋጋ መናር ሁሉ ምክንያት አንድ ነገር ነዉ ባይ ናቸዉ። ለዚህ ሁሉ የዋጋ ጭማሪ መነሻው ፋሽስታዊዉ የሩሲያ የጦር ኃይል፤ ዩክሬይንን በመውረሩ ነው። በዓለም ላይ የነዳጅ ዘይት እና የምግብ ምርት ዋጋ ጨምሯል፤ እጅግ ጨምሯል» ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

አድማጮች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ያሳባሰብንበት ዝግጅታችን እዚህ ላይ አበቃ። አዘጋጅዋ አዜብ ታደሰ ነኝ።

 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ