1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀኝና ግራ ፖለቲከኞች ፍትጊያ በደቡብ አሜሪካ

ሰኞ፣ ኅዳር 1 2012

ሶሻሊስታዊዉ ርዕዮተ ዓለም ከአዉሮጳና አፍሪቃ-እስከ እስያ በተመታበት በዚያ ዘመን ደቡብ አሜሪካ ላይ ዳግም ማቀጥቀጡ የካፒታሊስቱን ርዕዮተ ዓለም ለሚያቀነቅነዉ ዓለም በተለይም ለዩናይትድ ስቴትስና ለአካባቢዉ ተከታዮችዋ አዲስ ፈተና ነበር።

https://p.dw.com/p/3Sqnq
Bolivien Evo Morales, Alvaro Garcia Linera, Diego Pary
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Karita

ደቡብ አሜሪካ፣ ያንዱ ፌስታ የሌላዉ ድንጋጤ

ቬኑዙዌላን ያሽመደመደዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ ጋብ ሲል፣ ቺሌ በሕዝባዊ ተቃዉሞና አመፅ ትታበጥ ገባች።ዕዉቁ የብራዚል የግራ ፖለቲከኛ ሉዊስ ኢናቺዮ ሉላ ደ ሲልቫ ከወሕኒ ቤት በመለቃቀቸዉ የደቡብ አሜሪካ የግራፖለቲካ አቀንቃኞች ፈንድቀዉ ሳያበቁ፣ የቦሊቪያዉ የግራ ፖለቲከኛ ኢቮ ሞራሌስ ሥልጣን ለቀቁ።የደቡብ አሜሪካዎች ሰሞናዊ ፖለቲካዊ ወግ፣ ያፍታ ወጋችን ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።

2018 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) መጀመሪያ ላይ የቬኑዙዌላን አደባባዮች ያጥለቀለቀዉ ሕዝብ ያነገበዉ ጥያቄ የምርጫ ነፃነትና የምጣኔ ሐብት መርሕ ለዉጥ ቢሆንም መሰረታዊዉ ምክንያት የሶሻሊስቱን ወይም የግራዉን አስተሳሰብ የሚያቀነቅነዉን ሥርዓት ለማስወገድ ያለመ እንደነበረ የተሰወረ አልነበረም።

አንደበተ ርትዑ የቀድሞ ቆፍጣና የጦር መኮንን ሁጎ ራፋኤል ሻቬዝ ፍሪያስ በ1999 የቬኑዙዌላን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን ሲይዙ ያረጀ-ያፈጀ መስሎ የነበረዉ የእነ ፊደል ካስትሮ ርዕዮት ዓለም የመቀጠሉ አብነት ነበር።ሶሻሊስታዊዉ ርዕዮተ ዓለም ከአዉሮጳና አፍሪቃ-እስከ እስያ በተመታበት በዚያ ዘመን ደቡብ አሜሪካ ላይ ዳግም ማቀጥቀጡ የካፒታሊስቱን ርዕዮተ ዓለም ለሚያቀነቅነዉ ዓለም በተለይም ለዩናይትድ ስቴትስና ለአካባቢዉ ተከታዮችዋ አዲስ ፈተና ነበር።

ሻቬዝ የጀመሩት ለድሆች የሚወግን ፖለቲካዊ-ምጣኔ ሐብታዊ መርሕ ብዙዎችን የማስቆጣት፣የማስደንገጥ፣ ሥራዓቱን ለመጣል የማሳደሙን ያክል ለአነስተኛዉ መደብ እንታገላለን የሚሉ ኃይላትን በየሐገሩ ስልጣን እንዲያማትሩ አንዳዶቹም ጋ ለስልጣን እንዲበቁ አብነት ሆኗል።

Lula reist im Vorfeld der Präsidentschaftswahlen 2018 durch Brasilien
ምስል Ricardo Stukert /Instituto Lula

2002 ማብቂያ ብራዚል ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ የቀድሞዉ የሰራተኞች ማሕበር ሊቀመንበርና የብራዚል ሰራተኛ ፓርቲ (PT በፖርቱጋልኛ ምሕፃሩ) መስራች ሉዊስ ኢናቺዮ ሉላ ደ ሲልቫ የደቡብ አሜሪካዊቱን ሰፊ፣ሐብታም ሐገር የመሪነት  ሥልጣን ያዙ።ከወራት በኋላ አርጀንቲና ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ደግሞ እንደ ሉላ ሁሉ ሶሻሊስታዊዉን መርሕ የሚከተሉት ኒስቶር ኪርሽነር አሸነፉ።

ከፍተኛ የነዳጅ ሐብት ከተከማቸባት ቬኑዙዌላ እስከ ደቡብ አሜሪካዊቱ ሰፊ፣ሐብታም የቅይጦች ምድር ብራዚል ያሉ አብያተ መንግሥታትትን የነካስትሮ አስተምሕሮ አቀንቃኞች መቆጣጠራቸዉ የካፒታሊስቱ ርዕዮተ-ዓለም አራማጆችን እንቅልፍ የሚነሳ ነበር።በዚሕ መሐል ነዉ ትንሺቱ፣ወደብ አልባይቱ ሐገር ሌላዉን የካስተሮ ደቀ መዝሙር፣ የመጀመሪያዉን የሐገሬዉን ነባር ተወላጅ ፖለቲከኛ ለስልጣን ያበቃችዉ።ኢቮ ሞራለስ።2006።

የሩቁም የቅርቡም ካፒታሊስት  በጋራም በተናጥልም -የሶሻሊስቶቹን መስፋፋት ለመግታት በምጣኔ ሐብት ሻጥሩ፣ በፖለቲካ-ዲፕሎማሲ-ሕጉ ሴራ ሲረባረብ ዓመታት አስቆጥሯል።
በግራዎቹ የፖለቲካ ጥበብ ማነስ ይሁን በቀኞቹ ግፊት የአርጀንቲናዊ የግራ ፖለቲካ አቀንቃኝ ከዓራት ዓመት በላይ በፕሬዝደትነት አልቀጠሉም።የብራዚልን ምጣኔ ሐብት ባጭር ጊዜ ያንቻረሩት ሉላ ደሲልቫ በ2010 ሥልጣን ለቅቀዋል።ሉላን የተኩት የፓርቲያቸዉ ፖለቲከኛ ዲልማ ሮስፍ በ2016 ከስልጣን ተወግደዋል።ሉላ ደ ሲልቫ ዳግም ስልጣን ይይዛሉ ተብሎ ሲጠበቅ በ2018 በሙስና ተወንጅለዉ ታስረዋል።

በጠንካራዉ የግራ ፖለቲካ አቀንቃኝ በሁጎ ሻቬዝን ላይ የሚደረገዉ የዉስጥና የዉጪ ጫና ከሁሉም የባሰ ነበር።ሕዝብ አሳምፀዉባቸዋል።ላጭር ጊዜም ቢሆን በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን አስወግደዋቸዉ ነበር።ፅኑዉ ፖለቲከኛ በ2013 ሞት እስከቀደማቸዉ ድረስ አልተበገሩም። እስካሁን ያልሞተዉን የሻቬዝን አስተሳሰብ ለመግደል የተኳቸዉን ፖለቲከኞች በተለይ ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮን  ለማስወገድ የሚደረገረገዉ ሁለንተናዊ ግፊት እንደቀጠለ ነዉ። በ2018 በግልፅ የተጀመረዉ የአደባባይ ተቃዉሞ አሁንም ሙሉ በሙሉ አልበረደም።

[No title]
ምስል Paulo Pinto/Instituto Lula

የሐገር ዉስጥ ተቃዉሞዉ የቀኝ ፖለቲካን የሚያራምዱ ፖለቲከኞች የሚመሯቸዉን የአካባቢዉ መንግሥታት ድጋፍ አልተለየዉም። የዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ፣ ለተቃዋሚዎች የመንግስትነት እዉቅና የመስጠት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እርምጃና ድጋፍም እንደቀጠለ ነዉ።ፕሬዝደንት ማዱሮ ግን ዛሬም የካራካስን ቤተ-መንግስት እንደተቆጣጠሩ ነዉ።ኢቮ ሞራሌስ ግን የ14 ዓመት ሥልጣናቸዉን ትናንት በቃኝ አሉ።«ስልጣን ለመልቀቅ ለምን ወሰንኩ? ካርሎስ ሜሳ (ፕሬዝደንታዊዉ ዕጩ እና የተቃዋሚዎቹ መሪ) ሉዊስ ፌርናንዶ ካማቾ ወንድሞቼን የሕብረቱ መሪዎችን ማሳደዳቸዉን እንዲያቆሙ ነዉ።ሜሳ ካማቾ የቺኩስካ አገረገዢን፣ የምክር ቤት እንደራሴዎችን  ቤቶች ማቃጠላቸዉን እንዳይቀጥሉ ነዉ።ሜሳና ካማቾ ሳን ሉዊስ የሚኖሩ የሕብረቱን (ፓርቲ) አባላት ቤተሰቦች ማንገላታታቸዉን፣ ቴዎድሮ ማማኒን ማሰቃየታቸዉን እንዲያቆሙ ነዉ።»

ፕሬዝደንት ኢቮ ሞራሌስ  ብቻ ሳይሆኑ ምክትላቸዉ፣ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤም ሥልጣን ለቀዋል።ከ20 የሚበልጡ ባለስልጣናት ተቃዋሚዎች ያደርሱብናል ያሉትን ጥቃት ሽሽት ሜኪሶ ጥገኝነት እንድትሰጣቸዉ ጠይቀዋል።

ሞራሌስና ተከታዮቻቸዉ ሥልጣን የለቀቁት ፕሬዝደንቱ በቅርቡ የተደረገዉን ምርጫ አጭበርብረዋል በሚል በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ በተከታታይ ባደባባይ ሰልፍ ከተቃወማቸዉ በኋላ ነዉ።ሞራሌስን ሲቃወም የነበረዉ ሕዝብ የፕሬዝደንቱን ሥንብት እንደሰማ ትናንት በየከተሞቹ ሲደሰት ሲቦርቅ ነዉ ያደረዉ።

ሞራሌስ ስልጣን የለቀቁት የሐገሪቱ ጦር ኃይልና የፖሊስ አዛዦች ሥልጣን እንዲለቁ በግልፅ ከጠየቋቸዉ በኋላ ነዉ።ፕሬዝደንቱ ሥልጣን መልቃቀቸዉን ካወጁ በኋላ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ባሰራጩት መልዕክትም ሥልጣን ባይለቁ ኖሩ የሐገራቸዉ ፖሊስ እሳቸዉን ለማሰር የእስር  ዋራንት አዉጥቶ እንደነበር አስታዉቀዋል።የሞራሌስ ስልጣን መልቀቅ ወትሮም የተከፋፈሉትን የደቡብ አሜሪካ መንግሥታት እያነታረከ ነዉ።የቬኑዙዊላ፣የኩባ፣ የአርጀቲና መሪዎችና፣ የብራዚል ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሞራሌስን ሥልጣን መልቀቅ ሕገ-ወጥ በማለት አዉግዘዉታል።ከሁሉም የቀደሙት የቬኑዙዌላ ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሩ የሞራሌስን ሥልጣን መልቀቅ መፈንቅለ መንግስት በማለት አዉግዘዉታል።

Boliviens Präsident Evo Morales

«በቮሊቪያ ፕሬዝደንትና መሪ በኢቮ ሞራሌስ አያም ላይ ዛሬ መፈንቅለ መንግስት ተደርጓል።ባንድ ጊዜ ገሚስ እርምጃ ልትወስድ አትችልም።መፈንቅለ መንግስት ነዉ።በቀኝ ክንፎች የተደረገ መፈንቅለ መንግስት ነዉ።የፋሺስቶች መፈንቅለ መንግስት ነዉ።በአመፅና ሁከት የተቀነባበረ መፈንቅለ መንግሥት ነዉ።በጥላቻ፣በዘረኝነት፤ በከፋ ዘረኝነት ላይ የተመሰረተ መፈንቅለ መንግስት ነዉ።»

የኩባዉ ፕሬዝደንት ሚጉኤል ዲያስ-ካኔል በበኩላቸዉ በቲዊተር ገፃቸዉ ባሰፈሩት ፅሁፍ ለሞራሌስ ድጋፍና ትብብር እንዲደረግ ጠይቀዋል።«የኢቮን ነፃነትና ደሕንነት ለማስጠበቅ ዓለም በጋራ መጣር አለበት» ዲያስ ካኔል እንደፃፉት።

በቅርቡ አርጀቲና ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ባላጋራቸዉን በከፍተኛ የድምፅ ልዩነት ያሸነፉት አልቤርቶ ፌርናንዴስ በበኩላቸዉ እንዳሉት ቦሊቪያ ዉስጥ የደረሰዉ ተቋማዊ መፈረካከስ ተቀባይነት የለዉም።ሜክሲኮ ለሞራሌስ ባለስልጣናት ጥገኝነት ሰጥላች።ሞራሌስ ከፈለጉም ከለላ እንደምትሰጣቸዉ የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አስታዉቀዋል።

የሞራሌስን ሥልጣን መልቀቅ ወይም ደጋፊዎቻቸዉ እንደሚሉት ከስልጣን መወገድ አስቀድመዉ በይፋ ከደገፉት የአካባቢዉ  መንግሥታት የብራዚል መንግሥት ቀዳሚዉ ነዉ።ቀኝ አክራሪዉ የብራዚል ፕሬዝደንት ያር ቦልሶናሮ ቦሊቪያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንድታደርግ የመንግሥታቸዉ ድጋፍ አይለያትም ብለዋል።

የብራዚሉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አርኔስቶ አራዉዮ በበኩላቸዉ በቦልቪያዉ ምርጫ ተፈፀመ ያሉት ማጭበርበር ሞራሌስ ስልጣን እንዲለቁ አስገድዷቸዋል።የኮሎምቢያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣዉ መግለጫ ደግሞ የቦሊቪያ ሕዝብ የወደፊት መሪዉን በነፃነት ይመርጥ ዘንድ የሐገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተባብረዉ እንዲሰሩ ጠይቋል።

የአስራ-አንድ ሚሊዮኖቹ ትንሽ ሐገር የ14 ዓመት የግራ ፖለቲካ አቀንቃኝ ፕሬዝደንቷን በግድ ይሁን በዉድ ስልጣን  ያስለቀቀችዉ የትልቂቱ ደቡብ አሜሪካዊት ሐገር ትልቅ የግራ የፖለቲከኛ ሉላ ደሲልቫ ከእስር ቤት በተለቀቁ ሳልስት ነዉ።በሙስና ወንጀል 12 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዉ የነበሩት ሉላ ደ ሲልቫ 580 ቀናት ከታሰሩ በኋላ በሐገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዉሳኔ የተለቀቁት ባለፈዉ አርብ ነበር።

Bolivien Protest
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

ሉላ ደ ሲልቫ ባለፈዉ ቅዳሜ ለደጋፊዎቻቸዉ «እደገና መጣሁ» ብለዋል።ቀኝ አክራሪዉን የሐገራቸዉን  ፕሬዝደንት የቦልሶናሮ እና የቦልሶናሮን የፖለቲካ አብነት የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝደንት የዶናልድ ትራምፕን መርሕ አጥብቀዉ ተችተዋል። «ይሕ ሰዉዬ (ቦልሶናሮ) አራት ዓመት የመግዛት ሥልጣን አላቸዉ።ይሁንና የተመረጡት የብራዚልን ሕዝብ ለማስተዳደር እንጂ የሪዮ ዲ ዠኔሮ ሚሊሺዎችን እንዲያዙ አይደለም።-----(የአሜሪካ  ፕሬዝደንት ዶናልድ) ትራምፕ የአሜሪካኖችን ችግር ማስወገድ አለባቸዉ እንጂ የደቡብ አሜሪካ ጉዳይ ሊያሳስባቸዉ አይገባም።የአለም ፖሊስ እንዲሆኑ አልተመረጡም።ማስተዳደር ያለበት አሜሪካኖችን ነዉ። እዚያ ያለዉን ድሕነት ለመቀነስ ቢጥሩ ነዉ። አሜሪካኖች ግን በ1990 የበርሊን ግንብ በመናዱ ደስታቸዉን ይገልጣሉ።በሌላ በኩል ግን በድሆች ላይ ግንብ ያንፃሉ። ድሆች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ግንብ ያንፃሉ።ይሕን አንቀበለዉም።»

የደ ሲልቫ መለቀቅ ለብራዚል ብቻ ሳይሆን ለመላዉ ደቡብ አሜሪካ የግራ ፖለቲከኞች ተስፋ ምናልባትም የዳግም ትንሳኤ ምልክት ሆኖ ብዙዎችን አስደስቶ ነበር።የሞራሌስ ከስልጣን መልቀቅ ደግሞ አስደንጋጭ ክስተት። ሐዘንና ደስታ። ደቡብ አሜሪካ።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ