1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን የዩኤስ አሜሪካ ጫና

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 21 2010

የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና አማጽያን ሥልጣን መጋራት የሚያስችላቸውን  የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ከሁለት ቀናት በፊት ተፈራረሙ። ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች በካርቱም ሱዳን በተፈራረሙት ውል መሰረት፣ ሳልቫ ኪር ፕሬዝዳንት ሆነው ይቀጥላሉ፣ የአማጽያኑ መሪ ሪየክ ማቻር ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።

https://p.dw.com/p/32DPu
Uganda Südsudan - Friedensgespräch zwischen Präsident Kiir, Oppositionsführer Machar und der ugandische Präsident Museveni
ምስል Getty Images/AFP/S. Sadurni

ስምምነቱ ደቡብ ሱዳናውያን የናፈቁትን ሰላም ያወርድ ይሆን?

ሀገሪቱ  ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚወከሉ ሌሎች አራት  ምክትል ፕሬዝዳንቶችም ይኖሯታል።  የመጨረሻው የሰላም ውል በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 5 ከተፈረመ በኋላ ደግሞ በሦስት ወራት ውስጥ ለ36 ወራት ሥልጣን ላይ የሚቆይ  ከተለያዩት ቡድኖች የሚውጣጡ 35 ሚኒስትሮች  የሚሮሩት የሽግግር መንግሥት እንደሚመሰረት ይጠበቃል። 550  አባላት የሚኖሩት ምክር ቤትም ይቋቋማል። 
ይህ በደቡብ ሱዳን ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የሚካሄደውን የርስበርስ ጦርነት  ያበቃል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል። የመጀመሪያ ደረጃው የሰላም ስምምነት ከመፈረሙ ጥቂት ቀናት ቀደም ሲል በሁለቱ ተቀናቃኝ መሪዎች ግትር አቋም የተሰላቸችው  ዩኤስ አሜሪካ  የሰላም ስምምነት  እንዲደርሱ ጫና አሳርፋለች።  የኋይት ሀውስ ቤተመንግሥት ፕሬዚደንት ኪር እና ሪየክ ማቸር ጦርነቱን እና  በሰበቡ የቀጠለውን ሰብዓዊ ስቃይ እንዲያበቃ የታሰበውን ስምምነት ተግባራዊ ማድረጋቸውን ዩኤስ አሜሪካ እንደምትጠራጠረው  በመግለጽ፣ ስምምነት ካልደረሱ በአንጻራቸው ርምጃ እንደምትወስድ ዝቷል።   የሰላም ሂደት ሲቭሉን  ማህበረሰብ፣ አብያተ ክርስትያን፣ ሴቶች እና ሌሎች የህብረተሰቡን ክፍሎች ሁሉ የማያካትት ከሆነ  የደቡብ ሱዳን ዋነኛ የሰብዓዊ ርዳታ አቅራቢ የሆነችው ዩኤስ አሜሪካ  ለደቡብ ሱዳን የምትሰጠውን ድጋፍ  እንደምታቋርጥ ያሰማችው  ይህ ዛቻ  ኪር እና ማቸርን ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ግፊት በማሳረፉ ላይ ወሳኝ ሚና መጫወቱን ታዛቢዎች ተናግረዋል። ይኸው የዩኤስ ዛቻም ብዙዎቹን የደቡብ ሱዳን ዜጎችን ሳያሳስብ አላለፈም።  ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተገንጥላ ነፃነቷን ባገኝችበት ሂደት ላይ ቁልፍ ሚና የተጫወተችው ዩኤስ አሜሪካ የፖለቲካ መሪዎቹ የእርቀ ሰላሙን ሂደት ለማውረዱን ሂደት ቁርጠንነት ባለማሳየታቸው  ያሰማችውን ዛቻ መልሳ እንድታጤነው እና ተግባራዊ እንዳታደርግም ጠይቀዋል።  የ45 ዓመቱ የመዲናይቱ ጁባ ነዋሪ አቴም ፒተር ዩኤስ አሜሪካ ርዳታዋን የምታቋርጥበት ድርጊት የተራ ደቡብ ሱዳናውያንን ችግር ያባብሰዋል።
« ዩኤስ አሜሪካ ዛቻዋን እውን ከማድረጓ በፊት የሀገሪቱን ሰብዓዊ  ሁኔታን እንድትመለከት እማጸናለሁ። የደቡብ ሱዳን መሪዎችም የዩኤስን ዛቻ እንደቀላል ነገር ሳያዩ ለሰላሙ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡ እጠይቃለሁ።»
የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሀከቢ ሳንደርስ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና የዓማጽያኑ መሪ ሪየክ ማቸር ሰላም ለማውረድ የተጀመረውን ሂደት ለማሳካት በቂ ጥረት አላደረጉም ስትል ወቅሳለች። የደቡብ ሱዳን መንግሥት የዩኤስ ወቀሳ ቅር እንዳሰኘው ያመለከተ ሲሆን፣ የሀገሩ የውጭ ጉዳይ   ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማይዌን ማኮል ወቀሳውን ሀሰት ሲሉ አስተባብለዋል።
«  ቁርጠኝነት ተጓድሏል ያሉበትን አነጋገራቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ባለፉት ጊዜያት ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቸር  ባንድ ላይ ተቀምጠው ሲነጋገሩ፣ ሲደራደሩ እና በአንድነት ለመስራት መቻላቸውን ተመልክተናል። 
የደቡብ ሱዳን ዜጎች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና በተለይ ዩኤስ አሜሪካ ያሰሙ ዛቻ ያካባቢ ሀገራት በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማውረድ የጀመሩትን ጥረት እንዲሳካ እና ተቀናቃኞቹ ወገኖች ስምምነት  እንዲፈራረሙ በማድረጉ ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ያምናሉ።
በፕሬዚደንት ኪር እና ሪየክ ማቸር ካሁን ቀደም የተፈራረሟቸው በርካታ የተኩስ አቁም ደንቦች በተዳጋጋሚ ወዲያው መጣሳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በውጊያው በአስር ሽሺህ የሚቆጠሩ ተገድለዋል። ከሁለት ሚልዮን የሚበልጡም ተፈናቅለዋል ወይም ተሰደዋል። በሀገሪቱ ከቀሩትም መካከልም ብዙዎችን እረሀቡ አፋፍ ላይ አድርሷቸዋል።

Gorom-Flüchtlingslager im Südsudan
ምስል DW/T. Marima
USA, Washington: Pressesprecherin Sarah Sanders im Weißen Haus
ሳራ ሀከቢ ሳንደርስምስል Getty Images/AFP/T. Katopodis

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ