1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደመናን ወደ ዝናብ የሚቀይረው ቴክኖሎጅ

ረቡዕ፣ መጋቢት 22 2013

ይህ ቴክኖሎጅ በተበታተኑ የደመና ቅንጣቶች ላይ «ሲልበር  አዮዳይድ»እና «ፖታሼም ክሎራይድ»ን የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮችን ወደ ከባቢ አየር በመበተን ደመናን ወደ በረዶ ከዚያም ወደ ዝናብ የሚለውጥ ነው።

https://p.dw.com/p/3rNSh
US-Bundesstaat Louisiana wappnet sich für möglichen Hurrikan
ምስል Getty Images/AFP/S. Herald

ሳይንስና ቴክኒዎሎጂ


ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያለፈው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ መንገድ ደመናን ወደ  ዝናብ  የመቀየር ሥራ መጀመሯን ገልጸዋል። ይህንን ተከትሎ ደመናን የማዝነብ ቴክኖሎጅ በብዙዎች ዘንድ ብዙ መነጋገሪያ ሆኗል። ለመሆኑ ቴክኖሎጅው ምንድነው? የትኖቹ ሃገራትስ ተገበሩት? ጥቅምና ጉዳቱስ? 
 በሰው ሠራሽ መንገድ ደመናን ወደ ዝናብ መቀየር  ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር Cloud seeding በደመና ውስጥ እርጥበትን በመፍጠር ዝናብ ለማግኘት የሚደረግ  ሰው ሠራሽ  የአየር ሁኔታ ማሻሻያ ነው። ይህ ዘዴ በተበታተኑ የደመና ቅንጣቶች ላይ  «ሲልበር  አዮዳይድ» እና « ፖታሼም ክሎራይድ»ን የመሳሰሉ  ንጥረ ነገሮችን  ወደ ከባቢ አየር በመበተን ደመናን ወደ በረዶ ከዚያም ወደ ዝናብ የመለወጥ  ሂደት ነው። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሜትርዮሎጅ ኤጀንሲ የአየር ትንበያ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታምሩ ከበደ እንደሚገልፁት ይህ ቴክኖሎጅ ሃገራት የዝናብ እጥረትን ለመቋቋም ከሚጠቀሙበት ሳይንሳዊ ዘዴ መካከል አንዱ ሲሆን በዓለም ላይ በርካታ አስርተ ዓመታትን አስቆጥሯል። 
ደመናን ወደ ዝናብ ለመቀየር የሚደረገው የንጥረ ነገር ርጭትም አውሮፕላንን በመጠቀም አልያም መሬት ላይ በሚተኮሱ መሳሪያዎች አማካኝነት በሁለት መንገድ  የሚከናወን ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ  ቴክኖሎጂ ከ10 እስከ 15 በመቶ የዝናብ መጠንን ከፍ ሊያደርግ ይችላል። ያም ሆኖ ይህ ዘዴ በተፈጥሮ የሚገኝ ደመናን የሚፈልግ ሲሆን፤ አየር ላይ ደመና ከሌለ ግን ደመና መፍጠርም ይሁን ዝናብ የማመንጨት  አቅም የለውም።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደመናን ወደ ዝናብ ለመቀየር በጣም ከተለመዱት  «ሲልቨር አዮዳይድ» እና «ፖታሲየም አዮዳይድ» በተጨማሪ ወደ ጋዝነት መለወጥ የሚችለው «ፕሮፔን»  የተባለው ፈሳሽም ለዚሁ ሥራ ይውላል። እንደ  ደረቅ በረዶና  ጨውን የመሳሰሉ ነገሮችን መጠቀምም እየተለመደ መጥቷል። ይሁን እንጅ በደመና ቅንጣቶች ውስጥ የሚረጩት እነዚህ ንጥረ ነገሮች  በውሃ ውስጥ ለሚኖሩ  ሕይወት ያላቸው ነገሮች መርዛማ ሊሆኑና አካባቢንም ሊጎዱ እንደሚችሉ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ ሲባል  የሥነ-ምህዳራዊ ለውጦች፣ የኦዞን መሳሳት፣ ቀጣይነት ያለው የውቅያኖስ አሲድነት ፣መደበኛ የዝናብ ሂደት መዛባትን ፣ የደመና ቅንጣቶች በረዶ በመዝራት ድንገት እንዲቀዘቅዙ ሲደረጉ ያልተጠበቀ የአየር ሙቀት ለውጥ ሊያስከትል ይችላል ማለት ነው። የአየር ትንበያ ባለሙያው አቶ ታምርሩ ከበደ ግን ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል ባይ ናቸው።
ደመናን ወደ ዝናብ በመቀየሩ ሂደት የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ መርዛማ ያልሆኑ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም እንደ አማራጭ የሚታይ ሲሆን፤ የዘርፉ  ተመራማሪዎች «ካልሲየም ክሎራይድ» የተባለው ንጥረ ነገር  የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል።ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ  በኢትዮጵያ ተጀመረ ያሉት ደመናን ወደ ዝናብ በመቀየር ሂደት  ጥቅም ላይ የዋለው  በዋጋው ዝቅተኛ የሆነውና የሶዲየም ክሎራይድና የፖታሺየም ክሎራይድ ድብልቅ የሆነው «ሃይድሮስኮፒክስ » የተሰኘው ንጥረ ነገር መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። እንደ ባለሙያው የንጥረ ነገሩ አጠቃቀምም ቢሆን በአነስተኛ መጠንና ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ ነው።  
በጎርጎሪያኑ 18 91 ሊዊስ ጋትማን የተባሉ የሳይንስ ሊቅ ፈሳሽ ካርቦንዳይ ኦክሳይድን ደመና ላይ በመርጨት ዝናብ ማግኘት ይቻላል የሚል ፅንሰ-ሃሳብ ያፈለቁ ሲሆን፤ ኢርቪንግ ላንግሙየር የተባሉ አሜሪካዊው የኖቬል ተሸላሚ  የሳይንስ ሊቅ ይህንን ንድፈ ሃሳብ በቤተ ሙከራ ውስጥ በጎርጎሪያኑ 1946 አረጋግጠዋል። ቪንሰንት ሽዓፈር እና  በርናንድ ቮንጉት የተባሉ ባልደረቦቻቸው ደግሞ በ«ሲልቨር አዮዳይድ» በደመና ውስጥ  ከነጌቲቭ 10 እስከ ነጌቲቭ 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ  ባለው የሙቀት መጠን  የውሃ ትነትን ወደ በረዶ ቅንጣቶች፤ከነጌቲቭ 20 እስከ ኔጌቲቭ  7 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ባለው የሙቀት መጠን ደግሞ የበረዶ ቅንጣቶችን ወደ ዝናብ መለውጥ እንደሚቻል ይፋ አድርገዋል።እንደ  አቶ ታምሩ ይህ ቴክኖሎጅ ከዝናብ ባሻገር በረዶ ረግቶ እንዲቀመጥ በማድረግ ሰብሎችን ከጉዳት መከላከልና በአውሮፕላን በረራ ወቅት ጉምን የመሳሰሉ  ለዕይታ የሚጋርዱ ነገሮችን ለመከላከልም ያስችላል።
ይህ ቴክኖሎጅ  ህዳር 13 ቀን 1948 በአሜሪካ በኒው ዮርክ  የተጀመረ ሲሆን፤በካናዳ  በ1956 ለመጀመሪያ ጊዜ  ሰብሎችን ከበረዶ ጉዳት ለመከላከል ጥቅም ላይ ዉሎ ነበር ።ቻይና፣ሩሲያ እና ታይላንድ በሰው ሠራሽ ዝናብ አማካኝነት የደን ቃጠሎዎችን በተሳካ ሁኔታ ተቆጣጥረዋል። በአውስትራሊያም  ለድርቅ ወቅት የሚያገለግል ተጨማሪ ውሃ ለማጠራቀም ይጠቀሙበታል። በ2008 ቤጂንግ በተካሄደው ኦሎምፒክ በመክፈቻ ሥነ ሥርዓትም  ዝናብን ለመከላከል ይህንን ቴክኖሎጅ መጠቀሟ ይነገራል። 
አንዳንድ የኤዥያ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ሃገራት ድርቅና የውሃ እጥረትን ለመቋቋም ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። በአፍሪካም  በጎርጎሪያኑ 1985 የሞሮኮ መንግሥት ‹አል-ጋይት› የተባለ የደመና ማዝነብ ፕሮግራም ያቋቋመ ሲሆን፤ በሀገሪቱ  በ1999 ዓም ለመጀመሪያ ጊዜ  ጥቅም ላይ ውሏል። ሌላዋ አፍሪቃዊት ሀገር  ቡርኪናፋሶ  ከ 1999 እስከ 2002 ባሉት ዓመታት፤ ከ2005 ጀምሮ ደግሞ ሴኔጋል  ቴክኖሎጅውን ተጠቅመዋል። ማሊ እና ኒጀር  ደግሞ ይህንን ሳይንሳዊ ዘዴ  በብሔራዊ ደረጃ ጥቅም ላይ ያዋሉ የአፍሪቃ ሃገራት ናቸው። እንደ ዓለም አቀፉ የአየር ትንበያ ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለም ላይ ከ50 በላይ ሀገራት ይህንን ቴክኖሎጅ ተጠቅመዋል። በዘንድሮው ዓመት ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ተጠቃሚ አፍሪቃዊት ሀገር ሆናለች።ቴክኖሎጅው የሚያደርሰው ተፅዕኖና ጉዳት ግን በተመራማሪዎች ዘንድ አሁንም ድረስ  አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል። 

Iran Alborz-Gebirge
ምስል Yasser Al-Zayyat/AFP
Iran Alborz-Gebirge
ምስል Yasser Al-Zayyat/AFP
Cessna 208 Caravan
ምስል Getty Images/AFP/L. Suwanrumpha

ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ