1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ዮሐንስ ኪዳኔ

ዓርብ፣ ግንቦት 21 2012

ዮሐንስ ኪዳኔ እስካሁን 33 የሚደርሱ የፈጠራ ስራዎች እንዳሉት ይናገራል። በቅርቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ጠቃሚ ናቸው ያላቸውን ስምንት መገልገያዎች ሰርቷል።

https://p.dw.com/p/3cxeg
Äthiopien - Yohannes Kidane
ምስል privat

ዮሐንስ ኪዳኔ

ከዮሐንስ ኪዳኔ የፈጠራ ስራዎች መካከል በቅርቡ የሰራቸው ስምንቱ ፈጠራዎች የኮሮና ተህዋሲን ለመከላከል ይረዳሉ ሲል የሰራቸው ናቸው። ከነዚህ አንዱ በእግር ተጭኖ የሚሰራ የውኃ ማቅረቢያ ነው « እያንዳንዱ ህብረተሰብ 300 ብር ገደማ አውጥቶ የሚያሰራው ነው። ቫይረሱ እንኳን ቢጠፋ የውኃ አጠቃቀማችንን በመጠኑ እንድናደርግ ይረዳናል» ይላል ዮሐንስ። ሌላው ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የሰራው መሣሪያ የመተንፈስ ችግር ለገጠማቸው ሰዎች የሚያገለግል ነዉ። ይህ ፈጠራ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻኛው አይደለም። ዮሐንስ የእሱ ፈጠራ በኤልክትሪክ ወይም በባትሪ ኃይል እንዲሰራ የሰነው « የበሽተኞች ቁጥር ከጨመረ ወደፊት በቂ ነርሶች ላናገኝ እንችላለን። እና ይህን ጫና ከቀነስንላቸው የሚያክሙት በሽተኞች ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል። » በሚል ነው።

Äthiopien - Yohannes Kidane
የፖሊሶች መንገድ ዳር መቀመጫምስል privat

አዲስ አበባ ውስጥ በተለይም ታክሲ እና ሌሎች ተራ ማስያዥያ ስፍራዎች ላይ ርቀትን ማስጠበቅ እንዲቻል መሬት ላይ ቀለም እየተቀባ ተሳፋሪውን ለማራራቅ ቢሞከርም «ሰው ተጠጋግቶ መሰለፉን አላቆመም» ይላል ዮሐንስ። ለዚህም መፍትሄ ነው የሚለው ሁለት ሀሳቦች አሉት። « ተራ አስከባሪዎች የሚዘረጉት ነገር ነው። ተሳፋሪውም እዛ ላይ ነው የሚቀመጠው። ይህም ፒያሳ አራዳ አካባቢ በአገልግሎት ላይ እየዋለ ነው። » ሌላው የርቀት መጠበቂያ ደግሞ ሰው የሚያስረው ቀበቶ ነው። 

ሌላው የስክሪፒቶ ማፅጃውስ እንዴት ነው የሚሰራው?
« አንድ እስክርቢቶ ነው ለምሳሌ ባንክ ውስጥ ደንበኞች ለፎርም መሙያ እየተጠቀሙ ያሉት። የሚያዘው ደግሞ በጣት መካከል ነው። ብዙ ሰው ደግሞ እጁን 20 ሰከንድ ሙሉ በደንብ አድርጎ አይታጠብም።» ስለሆነም ለቫይረሱ ሊጋለጥ ይችላል ይላል ወጣቱ። ስለሆነም ደንበኞች ፅፈው እንደጨረሱ ስክርቢቶን ሲያስቀምጡ በአልኮል እየፀዳ ለሌላ ሰው ዝግጁ ሆኖ ይቀመጣል።

ዮሐንስ የጫማ ሶል ማፅጃ እንዲሆን የሰራው ደግሞ በዋንኛነት አየር መንገድ ውስጥ አገልግሎት ላይ እንዲውል ብሎ ነው። የዚህንም መሞከሪያ ቅርፅ ወይም prototyp ሰርቶ ለአየር መንገዱ አስረክቧል። ዮሐንስ የፈጠራ ስራዎቹ በተለይ ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ይረዳል ብሎ የሰራቸው ወይም የፈጠራቸው መገልገያዎች ምን ያህል በፍጥነት በስራ ላይ ይውላሉ ብሎ ያምናል? « እኛ ፕሮቶታይፑን ሰርቶ ማቅረብ እንጂ ወደ ምርት አንገባም። የእኛ ድርሻ ማሳየት ብቻ ነው።» ይላል። የኮሮና ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዘገይም እንደሚገባ ዮሐንስ እርግጠኛ ነበር። ለዚህም ነው ፈጠራዎቹን አስቀድሞ ማሰላሰል የጀመረው። ኢትዮጵያ ውስጥ ካደጉት ሀገራት የበለጠ ብዙ ነገሮች እንደሚያስፈልጉም ወዲያው ነው የተረዳው። ወጣቱ እነዚህን ከኮሮና ተሕዋሲ መከላከያ ጋር የተያያዙ ፈጠራዎቹን የአዕምሮ ንብረት ፅህፈት ቤት ያስመዘገባቸው የኮሮና ተህዋሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰተ በኋላ ነው። ከዚህ በፊት ባስመዘገባቸው ስራዎቹ ደግሞ ተወዳድሮ እና አሸንፎም ያውቃል። ከእነዚሁ ስኬታማ ስራዎቹ አንዱ የኮንዶሚኒየም ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድን ይመለከታል። 

Äthiopien - Yohannes Kidane
የኮንዶሚኒየም ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃምስል privat

ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ፣ የእንቁላል ማስፈልፈያ፣ የፖሊሶች መንገድ ዳር መቀመጫ እና ሌሎች የፈጠራ ስራዎችም የወጣቱ የስራ ውጤቶች ናቸው። በድርጅቱ ውስጥ ዮሐንስ ስራ ሲያገኝ ብቻ ነው ሰው ቀጥሮ የሚያሰራው። ካለበለዚያ ብቻውን ነው። አልፎ አልፎ የፈጠራ ስራቸውን የሚያከናውኑበት ቦታ የሌላቸውን ወጣቶች በነፃ ወደ እሱ ጋር ሄደው እንዲያከናውኑ እንደሚፈቅድላቸው ገልፆልናል። 
ለመሆኑ የፈጠራ ስራዎችን የአዕምሮ ንብረት ፅህፈት ቤት የማስመዝገብ ሂደቱ ምን ይመስላል? የ 32 አመቱ ዮሐንስ ተሞክሮውን ለሌሎች የፈጠራ ስራ ለሚያስደስታቸው ወጣቶች እንዲህ ሲል ያጋራል « የአዕምሮ ንብረት ፅህፈት ቤት 300 ብር ተከፍሎ ይመዘገባል። መፅሄት ላይ ይወጣል። የኔነው የሚል ካለ እነሱም ያጣራሉ። ከዛ ሰርተፊኬት ለመቀበል ደግሞ ቢያንስ ስምንት ወር ይፈጃል።» 

ሸገርን ማስዋብ የሚለው የከተማ ፕሮጀክት ላይ ዮሀንስ ተካፋይ እንደሆነም ገልጾልናል። ለዚህም ፕሮጀክት እንዲውል የሰራው ለኢትዮጵያ አየር ተስማሚ የሆነ ጥላ ያለው የመናፈሻ መንገድ ዳር ወንበር ነው። አብዛኞቹ የፈጠራ ስራዎቹ በጥቅም ላይ ቢውሉም« ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገር በቀልን ዕውቀት ለማስፋት እና ለመጠቀም ገና ብዙ ይቀረናል« ይላል፤ ቢሆንም ግን እሱ እንደሚለው ለውጥ አለ። 
ልደት አበበ
ነጋሽ መሐመድ