„ይህ የወንድ“ ወይም „ይህ የሴት ሙያ ነው“ የሚለው ነገር አለ ወይስ ቀርቷል?
ዓርብ፣ ሚያዝያ 16 2018
በዚህ በጀርመን በየዓመቱ ለአዳጊ ሴቶች እና ወንዶች አንድ ፕሮግራም ይዘጋጃል። ይህም ቀን ትናንት ሀሙስ ውሏል። አላማው በፆታ ላይ መሠረት ያደረገ ለአንድ ሙያ ያለንን ግንዛቤ መቀየር ነው። „ይህ የወንድ“ ወይም „ይህ የሴት ሙያ ነው“ የሚለውን ግንዛቤ በሂደት ማስቀረት ። ከ 23 ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ የፕሮጀክት ቀን አሁን አሁን ጀርመን ውስጥ በሀገር አቀፍ ይካሄዳል። ለዚህም ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች ፤ የራሳቸው ፆታ በቁጥር አናሳ የሆኑባቸውን የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ይጎበኛሉ። ሴቶች በቴክኒክ ዘርፉ የተሰማሩ ወይም በማሽን የሚሰሩ ፋብሪካዎችን ይጎበኛሉ። ወንዶች በአንፃሩ ህፃናትን ወደሚንከባከቡ እንደ ህፃናት መዋያ ወይም የሴቶች የውበት ሳሎኖችን ይጎበኛሉ። 11 ሺህ የሚጠጉ ድርጅቶች እና ኢንዱስትሪዎች ለዚህ ቀን ፍቃደኝነታቸውን አሳይተዋል።
ልጆች ገና በለጋ እድሜያቸው ከተለያዩ በተለይም ከፆታ ጋር ከተገናኙ ሙያዎች ጋር መተዋወቃቸው ፤ ለዛ ሙያ ያላቸውን አመለካከት በተለይም ከፆታ ጋር በተያያዘ ይቀይር ይሆን?
በ ኢትዮጵያ ሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ደሴት ጌታቸው በሁለት ወንዶች በሚያመዘኑበት የስራ መስክ እስካሁን ተሰማርታለች። የመጀመሪያ ስራዋ የወንዶችን ፀጉር ቤት ውስጥ ፀጉር ማስተካከል ነበር። ሴት በመሆኗ የገጠማት ነገር ይኖር? ሃሳቧን አካፍላናለች። « ብዙ ሰዎች ያበረታታሉ። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሰው አትቆርጠንም ብለው ደስ የማይላቸው ሰዎች አሉ። ከባለቤቴ ጋር እሰራም ስለነበር። ትችላለች ጎበዝ ናት እያለ መስራት ጀመርኩኝ። ወደ ስምንት ዓመት አካባቢ ሰርቼያለሁ»
ደሴት የፀጉር ቤት ስራዋን የተወችው ብዙ ቆማ መስራት ስለነበረባት እና አድካሚ ሆኖ ስላገኘችው ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ ባጃጅ በመባል የሚታወቀውን ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ገዝታ ሰው ቀጥራ ስታሰራ በውጤቱ ባለመርካቷ ነው።
ብዙም ድፍረቱም አልነበረኝ ለመስራት እና ሹፌር ቀጥሬ እንዲሰራልኝ አደረኩ። ግን የሚያዋጣ አልነበረም። ከዛ ለምን ራሴ አልሞክረውም ብዬ ጀመርኩ። የሰው አቀባበል ጥሩ ነበር። በፊት ላይ በእኛ ሀገር ሴት ልጅ ወደ ጓዳ ነበር የሚባለው። ግን አሁን እኔን ሲያዩ ሰዎች ደስ ይላቸዋል። አሁን የሴቶች እኩልነት አለ። ብዙ ሰው ያበረታታኛል።
ደሴት ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዋ ላይ „ሻሎም“ ብላ ፅፋ ስለነበር ብዙዎች በሀዋሳ ከተማ በዚህ መጠሪያዋ እንደሚያውቋት ነግራናለች። ወጣቷ ዛሬ ከባለ ሶስት እግር ተሽከርካር ከፍ ብላ ሚኒ ባስ ትነዳለች። ስራው ላይ ብዙም ለውጥ እንደሌለው ነው የምትናገረው። "ባጃጅ ሲሆን የሰው ብዛት ያንሳል ፤ ሚኒ ባስ ሲሆን ደግሞ ይጨምራል። አገልግሎት አሰጣጡ ለህዝብ ስለሆነ ተመሳሳይ ነው።"
ደሴት መኪናዋ ሲበላሽባትም እራሷ እንደምትጠግን ነግራናለች። የወንድ ወይም የሴት የምትለው ስራ የላትም።"ለምሳሌ የሞተር ዘይት ራሴ ነው የምቀይረው። ጎማ መንገድ ላይ ይፈነዳል። ራሴ እቀይራለሁ። ከበድ ያለ ሰርቪስ ሲሆን ነው ሜካኒክ ጋር የምሄደው።"
ሌላው ያነጋገርነው ሄኖክ በሀዋሳ ከተማ አራት ወራት የፈጀ የሜካፕ (የማስዋብ) ስልጠና ወስዶ ከጨረሰ ገና አንድ ሳምንት ሆነው። በዚህ ሴቶች በሚያመዝኑበት ሙያ ለመሰማራት የተነሳሳው በፍላጎት ነው። ያለውን ችሎታ ተጠቅሞ ሴቶችን ማስዋብ መቻሉ ከስራው ያስደስተዋል። ስለሆነም የፀጉር ስራ እና ሜካፕ ላይ ትኩረቱን አድርጓል። እሱንስ ሰዎች ምን አይነት አስተያየት ይሰጡታል?
"ተዋራኒው ነው። እንዴት እንደዚህ አይነት ስራ ትሰራለህ የሚሉ ትችቶች። ግን እየተላመድኩት ስመጣ ፤ በፊት የሚሰማኝ ሀፍረት ቀረ። " የሚለው
ሄኖክ የ 20 ዓመት ወጣት እና የ12ኛ ክፍል ተማሪም ሲሆን ይህንን ስልጠና የወሰደው ከትምህርቱ ጎን ለጎን ነው።
"ግንቦት ላይ ፋይናል ፈተና እንፈተናለን። ያንን እንደጨረስኩ ወደ ስራው አለም በስነ ሥርዓት እገባለሁ"
ሄኖክ የዩንቨርስቲ መግቢያ ነጥብ ቢመጣለት እንኳን ሊገፋበት የሚፈልገው ስራ የሜካፕ አርት እና የፀጉር ስራ እንደሆነ ደጋግሞ ይናገራል። ወጣት ልጆች ወደፊት መስራት ከሚፈልጉት ስራ ጋር ቀድመው መተዋወቃቸው ጥሩ አስተዋፅዎ አለውም ይላል።"ሜካፕ መስራት ከበፊትም የማስበው ነገር ነው ። ሲቀጥል ደግሞ አዋጭ ይመስለኛል። "
ለሌሎች ወጣቶች ምን ይመክራሉ?
"ትኩረት መስጠት እና የሰውን ትችት አለመስማት ነው። እንዴት የሴት ስራ ትሰራለህ? ሴት ፍለጋ ነው የሚሉ ትችቶች አይጠፉም። ያንን አለመስማት ነው።ስራቸው ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ነው የምመክራቸው። ሰው ስራ ባይንቅ !" ይላል ሄኖክ።
ሚኒባስ በመንዳት የምትተዳደረው ደሴትስ ለሌሎች ሴቶች በፊናዋ ምን ትመክራለች? "ሁሉም እኩል ነው። አስተሳሰባችን ነው። በራስ መተማመናችን ነው! እችላለሁ ካለች ማንኛውንም ነገር መስራት ትችላለች። ግን እችላለሁ ብላ ደፍራ መውጣት አለባት። ስራው ላይ ደግሞ የሰው አመለካከት እኛ እንደምንፈራው አይደለም። ያበረታታሉ። " ትላለች ደሴት።